በአማራ ክልል በተለይም በጎጃም፣ በሰሜን ወሎ፣ በሸዋና ኦሮሚያ ዞን አካባቢዎች በአገር መከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን በተለይም በላሊበላ አካባቢ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ከተማው ጫፍ ላይ የተጠመደ መድፍ ወደ ገጠራማው አካባቢ ሲተኮስ ማደሩን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በከተማው ቁጥሩ ሰፋ ያለ የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዳለ የገለጹት የላሊበላ ነዋሪ፣ በከተማው ውስጥ ሰዎች ታፍነው ወደ ሌላ ቦታ መወሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነቸው ወልዲያ ከተማ በተመሳሳይ ተከታታይ የተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ ከቦታው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ የገለጹ ሲሆን፣ የተኩስ ልውውጡ ድንገተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከሰሞኑ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ የሞቱ ሰዎች መኖራውን፣ ከምንጃር አካባቢ የተፈናቀሉና ወደ አዋሽ አካባቢ መሄዳቸውን የገለጹ አንድ በዕድሜ የገፉ ግለሰብ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም የፌዴራል ፖሊስና የአገር መከላከያ ሠራዊት የነበሩ ቢሆንም፣ የፀጥታ አካላቱ ውጡ ተብለናል በሚል አካባቢውን ለቀው በወጡ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ታጣቂዎች ገብተው አካባቢውን እንዳልነበረ እንዳደረጉት አስረድተዋል፡፡
ለተኩሱ መነሻ የሆነው በአካባቢው ፋኖ አለ የሚል መረጃ ቢሆንም፣ የወረዳው ሕዝብ ያለ ምንም መረጃ በተከፈተ ተኩስ እንዲፈናቀል ተደርጓል ብለዋል፡፡
በምንጃር ሸንኮራ በነበረው የተኩስ ልውውጥ በርካታ ዜጎች መሞታቸውን የተናገሩትና ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉት ግለሰብ፣ የሞቱ ሰዎችንም ለማንሳት ዕድል አለመገኘቱን ተናግረው ወደ ነበሩበት ቀዬ ለመመለስ የሚመለከታቸው አካላት ዕገዛ ሊያደርጉልን ይገባል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል በሚካሄደው ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አካባቢም ስለመቀጠሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
በጎጃም በተለይም ከደጀን መርጦ ለማርያም፣ ሞጣ፣ ቢቸና፣ ደጀን፣ ሉማሜ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደምበጫና መርሐቤቴ አድርጎ ወደ ባህር ዳር በሚያዋስነው መስመር በተለያዩ የገጠራማ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጡ መቀጠሉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰቦች ተናግረዋል፡፡ በደምበጫ፣ ፍኖተ ሰላም፣ አማኑኤልና ደብረ ማርቆስ የስልክ ኔትወርክ አገልግሎት እንደማይሠራም ተገልጿል፡፡ በጎንደር አካባቢ በአብዛኛው ሰላማዊ እንቅሰቃሴ ስለመኖሩ ከቦታው የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡