የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰየመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ከሰሞኑ ባቀረበው ሪፖርት የሰጠውን መረጃ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ተቃወመ፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ኢሰመኮ መረጃ ለማጋራት አዘግይቶብኛል ሲል መጥቀሱ አስቆጥቶታል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የባለሙያዎች ኮሚሽኑ መረጃ ለመስጠት ዘግይተዋል ብሎ ሪፖርት ማድረጉ፣ በተቋማቸው ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥርና ተገቢነት የሌለው መረጃ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት የባለሙያዎች ኮሚሽኑ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ሪፖርቱ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 54ኛ መደበኛ ጉባዔ 18ኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በዚሁ ዕለት የተቋማቸውን አቋም በመድረኩ ያንፀባረቁት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ኮሚሽኑ የመረጃ መጋራትን በሚመለከት የሰጠው መረጃ የተዛባ መሆኑን ሞግተዋል፡፡
‹‹ሪፖርቱ የእኛንና የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ሪፖርት አጋዥ ነው ብለን ወስደነዋል፡፡ ከባለሙያዎች ኮሚሽኑ ጋር መተማመን በመፍጠር በትብብር ስንሠራም ቆይተናል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃ ያጋሩን ከዘገየ በኋላ ነው ብለው በሪፖርታቸው ማቅረባቸው በእጅጉ አስገርሞናል፤›› ሲሉ ነው ዳንኤል (ዶ/ር) ቅሬታቸውን የገለጹት፡፡
ኮሚሽናቸው ለዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ኮሚሽን አስፈላጊውን ትብብር የማድረግ ግዴታ ስላለበት፣ ይህንንም ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
‹‹መረጃ ማግኘት የሚችሉበት የጊዜ ገደብ በደብዳቤ ሁለት ጊዜ ተጽፎ ተነግሯቸዋል፡፡ በዚህ የጊዜ ገደብ መረጃ ሳይጠይቁ መረጃ ያጋሩን ሪፖርቱን ማጠናቀር ከጀመርንና ከረፈደ በኋላ ነው ብለው እኛን መክሰሳቸው አግባብነት የሌለው ነው፤›› በማለትም ተቃውመዋል፡፡
ዳንኤል (ዶ/ር) አያይዘው ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ኮሚሽን፣ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት የተጣለበትና በሚሰጣቸው መረጃዎች እጅግ ጠንቃቃ ሊሆን የሚገባው አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባፈነገጠ መንገድ ኢሰመኮ መረጃ ለማጋራት አዘገየብኝ ብሎ መክሰሱ የተቋማቸውን መልካም ገጽታ የሚጎዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢሰመኮ ከተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጋራ በሠራው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትብብር ምሳሌ የሚሆን ሥራ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡ የባለሙያዎች ኮሚሽኑ፣ ‹‹መረጃ አዘገዩብኝ ማለቱ አንድን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም ገጽታ የሚያጠለሽ፣ እንዲሁም በተቋሙ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር የሚጋብዝ ተገቢነት የሌለው ድርጊት፤›› መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ከሰሞኑ ባቀረበው ሪፖርት ከኢሰመኮ ጋር መረጃ ለመለዋወጥ ግንኙነት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃ ያጋሩን ከረፈደና ሪፖርቱን ማጠናቀር ከጀመርን በኋላ ነበር ሲል ነበር ክስ ያቀረበው፡፡