Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልለዓለም ቅርስነት የበቁት ሁለቱ የኢትዮጵያ ዕንቁዎች

ለዓለም ቅርስነት የበቁት ሁለቱ የኢትዮጵያ ዕንቁዎች

ቀን:

የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ መሰንበቻውን ባካሄደው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ስብሰባው በቅርስነት ከመዘገባቸው የየአገሮቹ ድንቆች መካከል ሁለቱ ከኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው፡፡

አንደኛውና መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ በተጀመረው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ 45ኛ ስብሰባ የተመረጠው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ሲሆን፣ በማግስቱ ደግሞ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተመዝግቧል፡፡

ለዓለም ቅርስነት የበቁት ሁለቱ የኢትዮጵያ ዕንቁዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ልዩ ልዩ መገለጫዎች

ባንድ ዓመት ባንድ መድረክ ኢትዮጵያ ሁለት ቅርሶች ስታስመዘግብ ከ45 ዓመት በኋላ የመጀመርያው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1978 (1971 ዓ.ም.) ላሊበላና ስሜን ብሔራዊ ፓርክ በተመሳሳይ ጊዜ የተመዘገቡበት ነበር፡፡ ላሊበላ ባህላዊ ሲሆን ስሜን ፓርክ ተፈጥሯዊ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የተመዘገቡት የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ባህላዊ ሲሆን፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ ተፈጥሯዊ ምዝግብ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከ12 ዓመት በፊት ያስመዘገበችው ኮንሶን ነበር፡፡

እስካለፈው ሳምንት ድረስ ከአፍሪካ 10 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራ ይዛ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ መሪነቱን ለኢትዮጵያ ለቃለች፡፡

የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ገጽታ

ዩኔስኮ ባሠራጨው ሰነድ እንደተጠቀሰው ባህላዊ ቅርሱ የሚገኘው በዋናው የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ምሥራቃዊ ጫፍ፣ ደጋማ ቦታዎች ላይ ነው። የአግሮ ደን ልማት አካባቢ፣ ቡናና ሌሎች ቁጥቋጦዎች የሚበቅሉበት ዋናው የምግብ ሰብል እንሰት፣ በደኑ ውስጥ የተሰበጣጠሩ ዛፎች ይገኙበታል። ጥብቅ ደኖች ሳይደፈሩ ጥምር እርሻ የሚካሄድበትም ቦታ ነው፡፡

ለዓለም ቅርስነት የበቁት ሁለቱ የኢትዮጵያ ዕንቁዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ልዩ ልዩ መገለጫዎች
ፎቶ ዩኔስኮ

በአካባቢው የሚኖሩት የጌዴኦ ተወላጆች በባህላዊ ዕውቀታቸው የአካባቢውን ደን ይጠብቁታል። በሸንተረሮች ውስጥ በአካባቢው ማኅበረሰቦች ከሥርዓተ አምልኮ ጋር የተያያዙ ሥርዓቶች የሚጠቀሙባቸው የተቀደሱ ዛፎች ይገኛሉ፡፡ በቦታው ያሉት የሜጋሊቲክ ሐውልቶች በጌዴኦዎች ዘንድ የተከበሩና አዛውንቶቻቸው የሚንከባከቧቸው ናቸው። ከጌዴኦ ኅብረተሰብ ጋር የተቆራኙት ሕይወቱም የሆኑት ደን፣ እንሰትና ቡና መሆናቸውም ይወሳል፡፡

በባህላዊ መልክዓ ምድሩ ማዕቀፍ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ትክል ድንጋዮች፣ የአለት ላይ ሥዕሎች፣ በባህላዊ መንገድ ብቻ የሚተዳደሩ ደኖች ይገኙበታል፡፡ በሰው ፊት ቅርፅና በወንድ ልጅ ብልት መልክ የተቀረፁት የትክል ድንጋዮቹ በጨልባ ቱቲቲ የአርኪኦሎጂካል መካነ ቅርስና በቱቱፈላ ሲገኙ፣ የድንጋይ ላይ ሥዕሎችን የያዘው ደግሞ ኦዶላ ገልማ ነው፡፡ ትክል ድንጋዮቹ ሰዎች የተቀበሩበት ለመሆኑ ማረጋገጫው በሥፍራው ሌሎች የመገልገያ መሣርያዎች በቁፋሮ መገኘታቸው ነው።

ለዓለም ቅርስነት የበቁት ሁለቱ የኢትዮጵያ ዕንቁዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ልዩ ልዩ መገለጫዎች
ፎቶ ዩኔስኮ

ዩኔስኮ ጌድኦን ለምን በዓለም ቅርስነት መዘገበ?

እንደ የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታው አቶ ስለሺ ግርማ አገላለጽ፣ አንድን ቅርስ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ፈተና አለው፣ ሰፊ ጥናት ይጠይቃል፡፡ በዓለም ካሉ ነገሮች ሁሉ ልዩና ከፍ ያለ እሴት ያለው መሆን አለበት፡፡ እንዲያም ሆኖ ለማስመዝገብ ረዥም ጊዜ ይወስዳል። የሚመዘገበው የተፈጥሮም ይሁን ባህላዊ ወይም ታሪካዊ ቅርስ ከማኅበረሰቡ ዘንድ የመጠበቅና ቀጣይነት ማረጋገጥ ይጠይቃል። ከምንም በላይ ቅርሱ ለሌሎች አገሮች ማስተማሪያ መሆን ይኖርበታል።

ከዚህ አንፃር ሚኒስትር ደኤታው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ፋይል ዓለም አቀፍ ፋይዳ በመረዳትና ለተጠየቀው መስፈርት ምሉዕ በመሆኑ በኮንቬሽኑ መሠረት መርምሮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አድርጓል ይላሉ።

ባህላዊው የአካባቢ አጠባበቅ ትውፊታቸው፣ የጥምር እርሻ ሥርዓታቸው፣ ጥንታዊ የቱቱ-ፈላ ትክል ድንጋዮችና የድንጋይ ላይ ጥንታዊ ሥዕሎች መካነ ቅርሱ በዩኔስኮ እንዲመረጥ አስችሎታል፡፡

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

በልዩ ልዩ ሰው ሠራሽና አካባቢያው ችግር ምክንያት መሥፈርቱን ባለማሟላቱ፣ በጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2009 ሠፍሮ የነበረው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለቅርስነት የበቃው ከ15 ዓመት ደጅ ጥናት በኋላ ነው፡፡ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ሁሉ መልክ በመያዛቸው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ በቅርስነት እንዲመዘገብ ወስኗል፡፡

‹‹የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ – አንድ ፓርክ ብዙ ዓለም›› የሚሉት የቱሪዝም ባለሙያውና ሚኒስትር ደኤታው አቶ ስለሺ፣ – ፓርኩን እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡

የበርካታ ብርቅዬ ዕፀዋት (ለምሳሌ ጅብራ) እና የዱር እንስሳት መገኛ፣ (ለምሳሌ ኒያላ፣ ቀይ ቀበሮ)፣ የብዝኃ ሕይወት መናኸሪያ፣ የኢትዮጵያ ሁለተኛው ከፍተኛ ቦታ ቱሉ ዲምቱ መታያ፣ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሕዝቦች የውኃ ማማ፣ የእነ ራፋ ተፈጥሮ፣ የሀረና ጫካ መታያ ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣  የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ፋይልን መርምሮ ከዓለም አቀፍ ፋይዳው አንጻር  መመዝገቡን አወድሰዋል፡፡

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያልተለመደና ውበት ያለው የመሬት ገጽታ ሞዛይክ የሆነ መካነ ቅርስ ነው፡፡ በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ጫፎችና ሸንተረሮችን፣ አስደናቂ ተዳፋቶችን፣ ሸለቆዎችን፣ በረዶ የሚመስሉ ሐይቆችን፣ ለምለም ደኖችን፣ ጥልቅ ገደሎችና በርካታ ፏፏቴዎችን በመያዙ ልዩ የተፈጥሮ ውበት ይፈጥራል። ቦታው በሥነ ምኅዳር፣ በዝርያና በጄኔቲክ ደረጃ የተለያየና ልዩ የሆነ የብዝኃ ሕይወት ባለቤት ሲሆን፣ አምስት ዋና ዋና ወንዞች ከፓርኩ ውስጥ ይመነጩበታል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በጎረቤት አገሮች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ድጋፍ በመስጠትም ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

ፓርኩ ሲገለጽ

ሪፖርተር ከስምንት ዓመት በፊት ‹‹የባሌ ተራራዎች ሲፈተኑ›› በሚል ርዕስ በጻፈው መጣጥፉ እንደገለጸው፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ላይ በብዝኃ ሕይወት ሀብት ከበለፀጉ 34 አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ በ1962 ዓ.ም. የተቋቋመው ፓርኩ፣ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ያሉ አምስት ወረዳዎችና 26 ቀበሌዎች ያዋስኑታል፡፡ ፓርኩ 2,200 ስኲየር ካሬ ሜትር ስፋት የሳር ምድርና የደን መሬት (ከአደባ እስከ ዲንሾ ተራራ)፣ የፓርኩ ማዕከላዊ ክፍል (ሳነቴ ተራራና በዙሪያው ያለው የአሰጣ ቁጥቋጦ ደን) እና ሐረና ደንን ይሸፍናል፡፡ በፓርኩ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳት አሉ፡፡ ከነዚህ መሃከል 20ው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው ከእንስሳቱ ኒያላ፣ ቀይ ቀበሮና የደጋ አጋዘን ይጠቀሳሉ፡፡

 200 የሚጠጉ አዕዋፋት በባሌ ተራሮች የሚኖሩ ሲሆን፣ ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አሥራ አንዱ ደግሞ በኢትዮጵያና ኤርትራ የሚገኙ ናቸው፡፡ በክረምት ወቅት ከተለያየ የዓለም ክፍል አእዋፋት ለመጠለል ወደ ፓርኩ ይሄዳሉ፡፡ ፓርኩ በወፍ ቱሪዝም ከአፍሪካ አራተኛ ነው፡፡  

በጫካ ቡና፣ መድኃኒትነት ባላቸው ዕፀዋትና ተራሮች የተከበበው ፓርኩ፣ ከኢትዮጵያ በከፍታ ሁለተኛው ቱሉ ዲምቱ (4377 ሜትር) ይገኝበታል፡፡ ከፓርኩ 1600 የዕፀዋት ዝርያዎች 32ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ፓርኩ የጎብኚዎች መዳረሻ ከመሆኑ ባሻገር ጥናትና ምርምር ይካሄድበታል፡፡ በቅርቡ የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ወደ 22 የሚሆኑ የቢራቢሮ ዝርያዎች አግኝተዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የባሌ ተራሮች ለ40 የኢትዮጵያ ወንዞች መነሻና በሶድየም፣ ፖታሺየም፣ ማግኒዥየም፣ ዚንክና ካልሽየም የበለፀገ የሚኒራል (የከርሰምድር) ውኃ መገኛ ናቸው፡፡ በአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹ሖራ›› ተብሎ የሚጠራው ውኃ፣ የእንስሳትን ጤና እንደሚጠብቅና የወተት ምርታቸውን እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...