Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዙሪት!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ከረማችሁ ውድ ወገኖቼ፡፡ በመስከረም ወር ህልም ይበዛል ሲባል እሰማ ነበር፡፡ አሁን ግን በእኔ ደረሰ መሰል የማላውቀውን ህልም ማለም ጀምሬያለሁ፡፡ በቀደም ዕለት በህልሜ ሰው ሁሉ ደላላ ሆኖ አያለሁ። ሕፃኑ፣ አዋቂው፣ የተማረው፣ ያልተማረው ምን አለፋችሁ የቀረ የለም። የክፋቱ ክፋት ደግሞ ህልም ውስጥ ሆኜ ህልም እንደሆነ ገብቶኛል። ባለራዕይ ብትሆን አልፈኸው ልትሄድ ነው አትሉኝም? ‹‹ለምንድነው የሥልጣንን ክፍፍል አለማወቃችን ሳያንስ ሰው ሁሉ ከአንድ ሌማት እንጀራ መሻማቱ?›› ብዬ አንዱን ልጠይቀው ስጎትተው ነቃሁ። ዕድገታችን ብቻ መሰላችሁ ፈጣን? ህልማችንም እኮ ነው ሳንጨብጠው ሽው እያለ ያስቸገረን። የምር ብቻ ለማንም ምንም ሳልል፣ ውዴ ማንጠግቦሽ ማልዳ የሠራችውን ሽሮ ቀማምሼ ከቤት ወጣሁ። ያው ሐሳቤ ያለው ግን የህልሜ ፍቺ ላይ ነው። አራት ኪሎ አካባቢ የቀጠረኝ ከባድ መኪና ሊገዛ የሚፈልግ ደንበኛ ስለነበረኝ የምሄደው ወደ እዚያው ነው። ስደርስ ዓይኔን ማመን አቃተኝ። ከኮሌጅ የተመረቀውም ያልተመረቀውም ጋዜጣ ይዞ እርስ በርሱ አይገለማመጥ፣ አይተያይ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ላይ አፍጧል። ወይ ሥራ ፍለጋ!

‹‹ምንድነው ይኼ ሁሉ ሰው?›› ስለው አንዱን አልፎ ሂያጅ፣ ‹‹እኔም መጀመሪያ ወዶ ዘማች መስሎኝ ነበር። ቆይቶ ነው እንጀራ ፈላጊ መሆኑን የገባኝ…›› ብሎኝ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ። ምናለበት እስኪ በቀጥታ ቢናገር እያልኩ በእሱ መናደድ ስጀምር የህልሜ ፍቺ አይከሰትልኝ መሰላችሁ? አገር ምድሩ ደላላ ሆኖ ያሳየኝ ለካ ፈላጊና ተፈላጊ እየተራራቁ የሄዱበት ዘመን ስለሆነ፣ ተንከራታች እንደሚበዛ ሲገልጽልኝ ነው። እሱ ሲገልጽ ደግሞ እስከ እንጥፍጣፊው አይደል? እኔ ራሴ የድለላ ሥራ ውስጥ የገባሁት የተዋጣለት ተንከራታች ከነበርኩ በኋላ መሆኑ ትዝ አለኝ። ሁሉም ነገር ወዲያው ገባኝ። ይኼ ሁሉ ወጣት ደላላ ሲሆን አሰብኩ። ያውም የተማረ ዲግሪ ያለው ደላላ፣ አስባችሁታል? እኔ በታክሲ ስዛክር ቤቱ ቁጭ ብሎ በቴሌግራምና በዋትስአፕ ሻጭና ገዥን፣ አከራይና ተከራይን ሲያገናኝ በምናቤ ሳልኩት። ደግሞ የዚህ አገር ዲግሪ አትበሉ እባካችሁ፡፡ እንኳን የተማረው ፊደል የማይለየው ማይም ሳይቀር ቴክኖሎጂውን በሚያቀላጥፍበት ዘመን እንዲህ ይባላል? አይባልም!

በተያያዘ ጨዋታ ብዬ ልቀጥል አስቤ ሳቄ ቀደመ። ከአንድ ነገረኛ ወዳጄ ጋር እያወራን ልክ እንዳሁኑ በተያያዘ ጨዋታ ብዬ ልቀጥል ስል፣ ‹‹ምን ማያያዝ ያስፈልጋል? ከተያያዘ ዝም ብለህ አትቀጥልም? ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ጨዋታ የሚያያዘው አንበርብር? አንተም እንደ ዩቲዩበሮች ወጥ ታሪክ ከፋፍሎ በማያያዝ ማውራት ተጋባብህ?›› አለኝ። ነግሬያችሁ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ዜናን ልክ እንደ ሲሪየስ ፊልም በሲዝን የሚያዘጋጅ ብቸኛ ቦታ ዩቲዩብ ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ለምሳሌ አንድ ቦታ የተሰማ የግጭት ዜና ሲዘገብ አርዕስቱና ትንታኔው አይገናኝም። ‹ሰበር ዜና› ተብሎ ‹ተደመሰሰ›፣ ‹ጉዱ ተዘረገፈ›፣ ‹ተጋለጠ›፣ ወዘተ ተብሎ በርዕሱ በቀለማት ያሸበረቀ ዜና ምናምንቴው ሲወራበት ቆይቶ ‹በቅርቡ ጠብቁ› ተብሎ ሰዓቱ ሲያልቅ የብዙዎች ወሽመጥ ብጥስ ይላል፡፡ እናም ወዳጄ እንዲህ በእንዲህ ዓይነቱ ነገር ይቀልዳል። ራሱ ቀልዶም ራሱ ይስቃል። ቀልደው የሚስቁ ጤነኞች ናቸው ብለን እንለፈው። አንተላለፍ ብለን እኮ ነው እንጂ መንገዱም በጦር ጠማኝ ያዝ ተደርጓል አልሰማችሁም? ሰምተናል እንጂ!

ምን ላያይዝ ነበር ተያይዤ የቀረሁት እናንተ? አዎ… ውሎ አድሮ ህልሜንና ግጥምጥሞሹን ለአዛውንቱ ባሻዬ አጫወትኳቸው። ሥጋቴን አልተናገርኩም። ሁሉን ዝርግፍማ ባህላችን አይደለም። እሳቸው ምን አሉኝ ታዲያ፣ ‹‹አሁንስ ቢሆን ደላላ ያልሆነ ማን አለ?›› ብለው ጀመሩ። ‹‹እንዴት?›› ስላቸው ‹‹በከንፈር የማይደልለን፣ በፎቶ የማይደልለን፣ በአነጋገር፣ በቅስቀሳ፣ በምርጫ፣ በአመጋገብ፣ በአለባበስ፣ በአሾፋፈር፣ ኧረ ምኑ ቅጡ ምን የማንደለልበት ነገር አለ?›› ብለው አፈጠጡብኝ። እውነታቸውን እኮ ነው እያልኩ ፈዝዤ ቀረሁ። እኔ ቤቴ ወገብ የሚሰብር አልጋ ላይ እየተኛሁ እከሌ ተንቀባሮና ልጥጥ ብሎ መኪና የሚነዳው ማን ስለሆነ ነው? ብሎ አንዱ መጥቶ ኮሮላ ያጋዛሁት ደንበኛ አለ ለምሳሌ። በኋላ ሲጣራ ለካ ‘እከሌ’ ያለው ሰው መንግሥት መሥሪያ ቤት በሹፍርና ተቀጥሮ ‹‹V8›› ሲነዳ ዓይቶት ነው። አንዱ ደግሞ (ነዳጃችንን ስናወጣው እንደ ጉዳችን የማያልቅ ያድርግልንና) እንደዚሁ ፌስቡክ ላይ የተዋወቃት ልጅ ነበረች። ገና በአካል ሳይተያዩና ሳይጨባበጡ ሌት ተቀን እንጋባ እያለች አላስቀምጥ አለችው። በቃ ላገባ ነው ብሎ ሠፈሩን አተራመሰው። እሰይ ተባለ። ያው ከላይ እስከ ታች መበደር ነው የምናውቀው ቤተሰብ ተበዳድሮ ደገሰ። እንዲያው ግን ሙሽሪትን ይዘሃት መጥተህ አስተዋውቀን እንጂ ምናምን አይባልም? ለምንድነው ለድግስና ለጭፈራ የምንቸኩለው? ኧረ ያስተርጓሚ ያለህ!

የሠርጉ ቀን ደረሰና (ሁለተኛ ሚዜ እኔ ነበርኩ) ሙሽሪት ቤት ፌስቡክ ላይ በተለጠፈልን የጉዞ መመሪያ (GPS መሆኑ ነው) እየተመራን ደረስን። የወጉን ‘እንግባ አናስገባም’ ተጋፍተን ስንገባ ሙሽራው በቆመበት የእንግርግሪት ወደቀ። ይቅርታ ለካ ‘ፌንት በላ’ ነው የሚባለው። ‘ሶሪ!’ ሽብር ሆነ። ‹‹ምንድነው?›› ሲባል የሚናገር የለም። ገሚሶቻችን ቀዝቃዛ ውኃ ስንቸልስበት ገሚሶቻችን የሳትነው መመርያ እንዳለ የሙሽሪትን ‘ፌስቡክ አካውንት’ እንጎረጉራለን። ለካ አጅሪት ሌላ፣ መከረኛው ፌስቡክ ላይ የተሰቀለው ፎቶዋ እንቁ የመሰለች ሞዴል ሆኖ ነው። በአጭሩ አልተገናኝቶም ሆኖ ነው። እንኳን ሙሽራው እኛም ‘ፌንት’ መብላት አማረን። ደግሞ ይኼን ሰምተው ነገር ጠምዛዦች ሕዝቡ በረሃብ እየረገፈ ነው ብለው እንዳያወሩ እንጂ ‘ፌንት’ መብላቱስ ግድ የለም ይደርሳል!

ይኼን ይኼን ሳስታውስ ስማችን እንዳይበላሽ ፈራሁ። ለነገሩ ምን ያልተበላሸ ስም አለን? የዚያን ደንበኛዬን ጉዳይ ዳር ለማድረስ እየተጣደፍኩ ከባሻዬ ልጅ ጋር ጥቂት ሰዓት ሳገኝ ፍርኃቴን ነገርኩት። እሱ ደግሞ ያው ቆርጦ ቀጥል ነው እንደምታውቁት። በተማረና ባልተማረ መሀል ያለ የቆርጦ አቀጣጠል ልዩነት ያን ያህል ቢሆንም የምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግን ለየት ያለ ነው። ‹‹አንተ ደላላ የሚለው ስም ተበላሸ ብለህ ትጨነቃለህ? ምን ያልተበላሸ ስም፣ ምን ያልተወላገደ ትርጓሜ ያልያዘ ስም አለ? ነጋዴ ብትል መንግሥት፣ ፍትሕ ብትል ዴሞክራሲ፣ ምርጫ ብትል ኮሚቴ፣ ስብሰባ ብትል ቢሮክራሲ ምን ትርጉሙን ያልሳተ ስም አለ?›› ሲለኝ የት ልግባ? ‹‹ኧረ እባክህ ሰው እንዳይሰማ ድምፅህን ቀነስ አድርግ…›› ስለው፣ ‹‹አለቃ ብትል ጭፍራ፣ ወንድ ብትል ሴት፣ ባል ብትል ሚስት…›› እያለ ቀጠለ። ‘ምን ዓይነት ጣጣ ነው በገዛ እጄ እስኪ አሁን’ አልኩና ጥዬው ላጥ። ደሳሳ ጎጆዬን አቀና ብዬ ጠማማ ስያሜ ስቆጥር ለጥያቄ ብጠራ ለማን አቤት እላለሁ? የ50 ሆነ የ500 መቶ ብር ጥያቄ አለ ብልስ ማን አቤት ሊለኝ? አይደል እንዴ? እናም ባገኘው ቦታ ሁሉ ነገር እየዘረገፈ ያስቸገረኝን የባሻዬን ልጅ ምን እንደማደርገው እያሰብኩ ስጓዝ አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ምነው ገንዘብ በዝቶ ነው ሐሳብ በሐሳብ ያደረገህ…›› እያለ ለከፋ ሲጀምረኝ ችግሩ የራሴ መሆኑ ገብቶኝ እንዳልሰማ ሆኜ ታጠፍኩበት፡፡ ዘንድሮ በቀኝ እያሳዩ በግራ ካልታጠፉ አያዛልቅም፡፡ እንዲያ ነው ለማለት ያህል ነው!

እናላችሁ እንዲያም እንዲህ ብሎ ሥራ ሳልሠራ አላድርም። ደንበኛዬን የሚፈልገውን መኪና አጋዝቼው ኮሚሽኔን ስቀበል ደግሞ ሌላ መጣ። ይኼኛው ዳያስፖራ ነው፡፡ በማውቀው ሰው ተነግሮት ነው የደወለልኝ፡፡ ተቀጣጥረን ስንገናኝ ዳያስፖራም አይመስል፡፡ እዚሁ ከዳር አገር የመጣ አርሶ አደር መሰለኝ፡፡ ስፈራ ስቸር ከየት እንደመጣ ጠየቅኩት፡፡ ከዚያችው ከፈረደባት አሜሪካ ቴክሳስ ከሚባል ገጠራማ ሥፍራ መምጣቱን ነገረኝ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ የቴክሳስ ገጠር እኮ ለአዲስ አበባ ቅልጥ ያለ ከተማ መሆኑን ባናየውም በምናብ መሳላችን አይቀርም፡፡ አንዳንዶቻችን ከአውሮፓ ወይም ከአሜሪካ ገጠራማ ሥፍራ መጡ ሲባል ከእኛ ገጠሮች ጋር ለማነፃፀር ስንሞክር ግርም ይለኛል፡፡ ሰውየው በዘመናዊ እርሻ የጠገበ ሀብታም ኖሮ እዚህ ዘመናዊ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመክፈት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እያማረጠ መሆኑን ነግሮኝ፣ ለጊዜው የሚያርፍበት አፓርታማ እንድፈልግለት ነው የቀጠረኝ፡፡ ንፁህ ዘመናዊ አፓርታማ ከሁለት የመኝታ ክፍሎች፣ በቂ ሳሎን፣ መፀዳጃና መታጠቢያ፣ ንፁህ አየር የሚያገኝበት ባልኮኒ፣ እንዲሁም ዋይፋይ ያለው እንዲሆን ነው ያሳሰበኝ፡፡ ዕድሜ ለቦሌ ወስጄ ዘመናዊ አፓርታማ አከራይቼው ሞቅ ያለ ኮሚሽን ሰጥቶ አሰናበተኝ፡፡ ሌላም ሥራ ይኖርሃል ብሎ በተስፋ ሲያሰናብተኝ ከእነዛ የናይት ክለብ አጋፋሪ ዳያስፖራዎች ጋር ማወዳደር ተሳነኝ፡፡ አቦ ይመቸው!

በሉ እንሰነባበት። የባንክ አካውንቴ በዚያ ምሥጉን ኢንቨስተር ዳያስፖራ ሞቅ ያለ ኮሚሽን ተወጣጥሮ ከመጨናነቁ በፊት ለተወሰኑ የጠርሙስ ቢራዎች የሚሆነኝን ቆንጥሬ፣ የቀረውን ደግሞ ለውዴ ማንጠግቦሽ የቤት ወጪ ሰጥቼ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። እንደገባሁ በሩቁ ያየሁት ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ነው። ቀን ስላናደደኝ ለንቦጬን ጥዬ ሄጄ አጠገቡ ተቀመጥኩ። መናገር ሲጀምር አቋረጥኩትና ያማረለት ከመሰለው እንደተሳሳተ አስረዳሁት። ‹‹ምንም ቢሆን ያለኸው ሦስተኛው ዓለም ነው…›› ሲል አንዱ ከሩቅ ልክ ውሎ ገባችን እንደሚያውቅ ሁሉ ሲናገር ሁለታችንም ክው አልን። ለካስ ሰውዬው ሌላ ጨዋታ ይዞ ነው። ዕፎይ ከማለታችን የባሻዬ ልጅ በጥሞና አንድ የግሪክ አፈ ታሪክ አጫወተኝ። ‹‹ሲሲፈስ ይባላል። በግሪክ አፈ ታሪክ የኦሎምፒያ አማልዕክት ዋና አለቃ በሚባለው ዚውስ የተፈረደበት ግዞተኛ ነው። ዚውስ የፈረደበት የባህር አምላክን ሴት ልጅ ጠልፎ ሲያስወስዳት ሲሲፈስ ዓይቶ ለባህር አምላክ ስለነገረው ነው። ፍርዱ ምን ይመስልሃል ታዲያ? አንበርብር?›› አለኝ። እንዲህ በተረትና በምሳሌ ሲያጫውተኝ ደስ ስለሚለኝ ‹‹ምኑን አውቄ?›› አልኩት ፈታ እያልኩ። ብዙ ጊዜ በራሳችንም ሆነ በአገራችን ላይ ችግር የምንቀፈቅፈው ሰከን ማለት ስለሚያቅተን ነው፡፡ እኔ አኩርፌ ስመጣ እሱ ይህንን ተገንዝቦ ልብ አረስራሽ ታሪክ ከቢራ ጋር እንዳወራርድ ሲያደርግ፣ መማር ምን ያህል በረከት እንደሆነ በእሱ እረዳለሁ፡፡ ተምረናል ብለው የሚመፃደቁ የጥራት አልባ ትምህርት ውጤቶች ምን እየሠሩን እንደሆነ እናውቅ የለ እንዴ፡፡ በሚገባ አትሉም ታዲያ!

ምሁሩ ወዳጄ ደስ በሚለው አንደበቱ ሲቀጥል፣ ‹‹ፍርዱ አንድ ረጅም ተራራ ጫፍ ላይ እንደ ኳስ የሚንከባለል ግዙፍ ቋጥኝ እየገፋ ማድረስ ነው። አደረስኩት ሲል ቋጥኙ ተመልሶ ይንከባለላል። በአጠቃላይ የእኛም ነገር እንደ ሲሲፈስ ሲሆንብኝ እየተናነቀኝ ነው…›› ሲለኝ በከፍተኛ ጉጉት ነበር ያዳመጥኩት። በተለይ በተለይ የተበላሹ ስሞቻችን ካልተስተካከሉ ትውልድ የሲሲፈስን ታሪክ ሲቀባበል እንደሚኖር ተገለጸልኝ። የተማረ ይግደለኝ እንዳልል ያልተማረ ነው የሚቀብረኝ። እስኪ ከመሞታችን በፊት የተበላሹ ስሞቻችንን ይስተካከሉ። ‘የተማረ እየገደለ ያልተማረ ይቀብረናል’ የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? ቆይ ግን በሰከነ መንፈስ ስናይ እኮ አባባሉ ከበድ ይላል፡፡ ሰከን ስንልና ሰከር ስንል ልዩነቱ ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ሰከን ያሉት አስተውሎት አላቸው፡፡ የሰከሩት ደግሞ ጌሾ ወስዷቸዋል፡፡ ስለዚህ የሰከነና የሰከረ ይለይ ስንል ብዙ ችግሮቻችን ፍንትው ብለው ይታያሉ፡፡ በዚህ ዘመን እንደ ምሁሩ የባሻዬ ልጆች የመሳሰሉ ምሁራንና ልሂቃን ያስፈልጉናል፡፡ ፍሬውን ከገለባ መለየት የሚቻለው ስክነት ሲኖር ነው፡፡ ያለበለዚያ አዙሪቱ አይለቀንም፡፡ ለዓመታት ከገባንበት አዙሪት ለመውጣት ግን ጥራት ባለው ትምህርት ተኮትኩተው ያደጉና የሰከኑ ምሁራን ያስፈልጉናል፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት