Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተፈተነው ሰላምና የዓለም የሰላም ቀን

የተፈተነው ሰላምና የዓለም የሰላም ቀን

ቀን:

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባታቸውን ለማረጋገጥ ዋስትና እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በነበረው ግጭት በርካታ ዜጎች በሰላም ዕጦት ተፈትነዋል፡፡

ከሁሉም በላይ የሰላም ዕጦትን ለመቅረፍ ወጣቶች ትልቅ ድርሻ ቢይዙም ወጣቶች ራሳቸው የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለማለፍና የሰላምን ለማስፈን የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች በተስፋፉበትና ሰላም በደፈረሰበት አጋጣሚ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በደነገገው መሠረት የዓለም ሰላም ቀን መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በየአገሩ ታስቦ ውሏል፡፡

ተመድ በየዓመቱ ‹‹ሴብቴምበር 21›› (መስከረም 11) ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ሆኖ እንዲከበር የደነገገው፣ ዓመፅንና ግጭቶችን በማስቆም ሰላምን ለማስፈን እንዲረዳ ነው፡፡ ለዚሁ ቀን ልዩ የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሪ ቃል በየዓመቱ ይመርጣል፡፡

የሰላም ቀን ምልክት ብዙውን ጊዜ ከርግብና ከወይራ ቀንበጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ርግብ ሰላምንና ነፃነትን የምትወክል ሲሆን፣ የወይራ ቀንበጥ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ የሰላም ትውፊታዊ ምልክት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤትም የዓለም የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ፣ ‹‹የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላምና ለዓለም አቀፍ ግቦች›› በሚል መሪ ቃል፣ ሐሙስ መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡

 ‹‹የሰላም ዕድሎች፣ ፈተናዎችና በሰላም ግንባታ የወጣቶች ሚና በኢትዮጵያ››  የሚል የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የአንትሮፖሎጂ መምህሩና ተመራማሪ ኬሬዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዓለም ላይ ከ600 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ግጭትና አለመረጋጋት ባለባቸው አገሮች ይኖራሉ፡፡

በዓለም ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማምጣት የግጭት መሠረታዊና መዋቅራዊ ምንጩን መለየት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ተመራማሪው፣ እነዚህንም ችግሮች በተገቢው መንገድ ማከም ከተቻለ፣ ሰላም ማምጣት ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሰላም ትምህርትና የባህል ልውውጦችን የሚያንፀባርቁ መድረኮችን በማዘጋጀት የሰላምን ትርጉም ለማኅበረሰቡ ማሳወቅ እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል፡፡

ሰላም የሚደፈርስበት አንደኛው ገጽታ ጦርነትም ሆነ ሁከት ሳይኖር መዋቅራዊ የሆነና ባህል ተኮር ይዘትን የያዘ መገለል ሲመጣ ነው፡፡ በዚህም ማንኛውም ሰው ሰላሙ ሊረበሽ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ አለመግባባቶች ቢፈጠሩ እንኳን ችግሩን በፍጥነት መፍታት የሚቻልበትን የሰላም መንገድን ያመጣል፡፡  

በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን የሰላም ግንባታን መፍጠር የሚቻለው የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ግጭት ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና ሐሳቦችን በማንሸራሸር እንደሆነም መምህሩ አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም. የተደረገው ጥናት፣ 73 በመቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው ሐሰተኛ መረጃ ሲያሠራጩና ለግጭትም ሆነ ላለመረጋጋት ምንጭ መሆን እንደቻሉ ያሳያል ብለዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥም 80 በመቶ የሚሆኑት ተጠቂና ተዋናይ የሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ወጣቶችንም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች በማሳተፍ በኢትዮጵያ የሚታየውን የሰላም ዕጦት መቅረፍ ይቻላል ብለዋል፡፡

ሰላም በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ በማጠናከር፣ ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል ትልቅ መሆኑን የገለጸው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገና ነው፡፡

በተለይ ግጭት በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ለሰላም ዕጦት በዋናነት የሚጋለጡት ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ወጣቶችን በተለያዩ ጉዳዮች ማሳተፍ ያስፈልጋል ሲል አስረድቷል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ የሰላም ዕጦትን ችግር ለመቅረፍ የውይይት መድረኮችን አዘጋጅቶ፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ውይይት በማድረግ ሰላም እንዲፈጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግሯል፡፡

ወጣቶች ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎችን በማለፍ፣ ከራሳቸው በዘለለ ለአገር የሚተርፍ የሰላም ትሩፋት ማበርከት እንደሚኖባቸውም ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እታገኝ አሰፋ በመድረኩ እንዳሳሰቡት፣ በኢትዮጵያ ለሰላምም ሆነ ለዕድገት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ውይይትን እንደ ዋነኛ መሣሪያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

የሰላም ዕጦትና ግጭት ሲከሰት በውጤቱ ኅብረተሰቡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ቢሆንም፣ በተለይ ወጣቶች ፊት ለፊት ስለሚጋፈጡ ውስብስብ ለሆኑ ችግሮች እንደሚጋለጡ የታለፉት ጊዜያት ምስክር ናቸው በማለት አብራርተዋል፡፡

ወጣቶች በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣና መልካም አስተዳደር እንዲሠፍን ጉልህ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ እነዚህንም መሠረታዊ ተግባሮች ወጥ በሆነ መንገድ በመጠቀም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶችን በሰላም ግንባታ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በሕገ መንግሥት የተረጋገጠ፣ በነፃነት የመደራጀት መርህና መብትን መሠረት በማድረግ በሚፈልጉት መንገድ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶችን እንዲላበሱ ጥረት ቢደረግም ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...