Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ትሩፋቶች

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ትሩፋቶች

ቀን:

ቀደምት ኢትዮጵያውያን እጅግ ተጠራጣሪ የራሳቸው የሆነን ነገር አሳልፈው የማይሰጡ የሌሎችንም ለመቀበል ጊዜ የሚፈጅባቸው እንደነበሩ ይነገራል፡፡

ለአገራቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ፣ ለሃይማኖታቸውና ለክብራቸው በብርቱ የሚጨነቁ እልፍ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ትሩፋቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ስለ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ገለጻ ሲያደርጉ ከተገኙት አንዱ ልዑል ራስ
መንገሻ ሥዩም ናቸው

አገራቸውን እንደ ዓይን ብሌናቸው ይንከባከቧት ስለነበር ‹‹ዳሯን እሳት መሀሏን ገነት›› አድርግላት ብለው ወደ ፈጣሪያቸው በየዕለቱ ይማፀናሉ፡፡ በድፍረት ድንበሯን ጥሶ አጥሯን አፍርሶ ለመግባት የሞከረን ጠላት ሁሉ በታላቅ ድልና በአሸናፊነት ወደመጣበት መልሰዋል፡፡ ለዚች አገር ብዙ ደም ፈሶባታል፣ አጥንት ተከስክሶባታል፡፡

ብዙዎች በየዘመኑ የየራሳቸውን ማንነት፣ ሃይማኖትና ባህል ለማልበስ ብዙ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴን ያደርጉ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

‹‹ከሞኝ ጓሮ ሞፈር ይቆርጣል›› እንዲሉ በቀደመው ጊዜ አውሮፓውያን መላው አፍሪካን በመቆጣጠር ሀብትና ንብረታቸውን የከበሩ ማዕድናትን ከመበዝበዝ ባሻገር ባህልና ማንነታቸውን ቋንቋና ሃይማኖታቸውን ጭነውባቸው የሄዱ አያሌ የአፍሪካ አገሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በወቅቱ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁሮች እንደ ሰው አይቆጠሩም ነበር፡፡ ምግብና መጠጣቸው ቀርቶ መንገዳቸው የተለየ፣ አልፎ ተርፎ መሸጥና መለወጥ ዕጣ ፈንታቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ 

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ትሩፋቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ከእነዚህ መሰል አገዛዞች አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍሰው ሊጫንባቸው የነበረውን የቅኝ ግዛት ቀንበር በመተባበርና በጀግንነት  ሰብረው ጠላትን አሳፍረው  በመመለስ ለብዙዎች በር ከፋች ሆነው ነፃነትን  አሳይተዋል፡፡

ከባዕድ አገር ማንኛውንም ነገር ከመዋስና አስመስሎ ከመሥራት ይልቅ በራሳቸው ምርምርና ፈጠራ በማተኮር ላይ የተጠመዱ እንደነበሩ ብዙ ማሳያዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ማንኛውም በውጭ አገር የተሠራ ቴክኖሎጂን በቀጥታ ከመቀበል ይልቅ ስለአሠራሩና አጠቃቀሙ እንዲያስተምሯቸው ይወተውቱ እንደነበር ይወሳል፡፡

ባዕዳኑ ደግሞ ይህንን አስተሳሰብ በእጅጉ ይጠሉታል፡፡ ምክንያቱም እነሱ ሠርተው ምርታቸውን መሸጥ እንጂ ጥበባቸውን አሳይተው መውጣት አይፈልጉም ነበር፡፡

የሆነ ሆኖ አዲስ ቴክኖሎጂን ወደ አፍሪካውያን ለማስገባትና ለማስተዋወቅ ግን በርካታ ውጣ ውረዶች እንደነበሩት ይነገራል፡፡

በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈረንጅ ፈጠራን ተቀብሎ ለመተግበር በእጅጉ ፈታኝና አስቸጋሪ ነበር፡፡ በአሁን ወቅት ለአገልግሎት የዋሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲህ በቀላሉ ወደ አገር ውስጥ እንዳልገቡና ለኅብረተሰቡ እንዳልደረሱ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ስልክ በወቅቱ ወደ አገር ሲገባ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ሆቴልም፣ የእህል ወፍጮም፣ ሬዲዮና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች በብዙ ጥረትና ልፋት የተለመዱ ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ በወቅቱ ከነበሩት ለየት ብለው ስለቴክኖሎጂ የተረዱ፣ ስለዓለም ሥልጣኔ ያወቁ፣ የተማሩና የተመራመሩ ሌሎችን በማስተማር፣ ያመኑበትን ለአገርና ለወገን ይጠቀማል ብለው የተረዱትን ሆነው በማሳየት ሕዝቡን ያነቁና ያበቁ በርካታ ስመጥር ኢትዮጵያውያን  ነበሩ፡፡

ቴክኖሎጂን ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና በማስተዋወቅ ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ አገር ቤት አስገብተው ቢያስተዋውቁም በወቅቱ የነበረው ኅብረተሰብ ግን አሜን ብሎ ለመቀበል በእጅጉ ይቸገር እንደነበር ይነገራል፡፡

ከዚህ ባሻገር ሕዝቡ ከወትሮው የተሻለ ኑሮን ይኖር ዘንድ የተሻለ ለብሶ ጥሩ ምግብን በልቶ ከአጉል ልማድ ራሱን እንዲያላቅቅ በትጋት የጣሩ የአገር ባለውለታዎች በርካታ ናቸው፡፡

የማኅበረሰቡ ንቃተ ህሊና ይጎለብት ዘንድ ጥረት ያደርጉ የነበሩ ሰዎች የኋላ ታሪካቸው ሲታይ ትምህርት ቤት ገብተው የተማሩ፣ አለፍ ሲል ወደ ውጭ አገር የመሄድ ዕድሉን አግኝተው የፈረንጅን ኑሮና ሥልጣኔ የተመለከቱ እንደሆኑ ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ይቻላል፡፡

በወቅቱ የተማሩ ሰዎች ኅብረተሰቡን ለማሠልጠን የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ከዚህ መካከልም ሥነ ጽሑፍ ይጠቀሳል፡፡ በልብ ወለድ፣ በግጥምና በዝርው፣ ተረትና ምሳሌ በማጣቀስ ስለሚመጣው ነገር ሁሉ ያስረዱ እንደነበር ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቀድሞው የተሻለ ኑሮን ይኖር ዘንድ የበኩላቸውን ትልቅ ሚና ከተጫወቱት መካከል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ አንዱ ናቸው፡፡

ብላቴን ጌታ ኅሩይ በተለይ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመርያ ሩብ  በሥነ ጽሑፍና በሌሎች የአስተዳደር ጉዳዮች ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ ከአዲስ አበባ ከንቲባነት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በብቃት እንዳገለገሉ ይነገርላቸዋል፡፡

በሸዋ መርሐ ቤቴ ጊቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ በ1871 ዓ.ም. የተወለዱት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከሃያ ያላነሱ መጻሕፍትን በመጻፍ ለአገራቸው አበርክተዋል፡፡ ከሥራዎቻቸው መካከል ‹‹ኢትዮጵያና መተማ (የአፄ ዮሐንስ ታሪክ ባጭሩ)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል፣ ‹‹ወዳጄ ልቤ፤ የሰውን ጠባይና ኑሮ በምሳሌ የሚገልጽ፣ ‹‹የልዕልት ወይዘሮ መነን መንገድ በኢየሩሳሌምና በምስር፣ ‹‹በኢትዮጵያ የሚገኙ በግዕዝና በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የመጻሕፍት ካታሎግ፣ ‹‹ማኅደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን፣ ‹‹ለልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ፣ ‹‹የልብ አሳብ፤ የብርሃኔና የጽዮን ሞገስ ጋብቻ፣ ‹‹ጎሀ ጽባሕ፣ ‹‹አዲስ ዓለም፤ የቅኖችና የደግ አድራጊዎች መኖሪያ ይገኙበታል፡፡

ባለፈው ሳምንት መስከረም 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የቀድሞ መኖሪያ ቤት፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ በእሳቸው የሥነ ጽሑፍ አበርክቶትና ይዘት ላይ ያተኮረ ጥናት ቀመስ ትንታኔ በእንዳለ ጌታ ከበደ (ዶ/ር) ቀርቦ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡

‹‹ለአገርና ለሥነ ጽሑፍ የነበራቸው ፍቅር በጣም የታወቀ ነበር›› ያሉት እንዳለ ጌታ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች የንጉሡንና የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን ቅርበት ለመግለጽ፣ 

‹‹ንጉሡ ተፈሪ ጳጳሱ ኅሩይ

የሃይማኖት ነገር ቀረ አይደለም ወይ›› በማለት የሁለቱን ቅርበት ለማስረዳት ተሞክሯል።

 በዘመናቸው ዕውቀትን ለመሸመት አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ ሰዎች የተለያዩ ፍረጃዎችንና ትችቶችን ይሰጧቸው ነበር፡፡ ለአብነትም ዓረብኛ ቋንቋን ለመማር ሲሞክሩ ‹‹ይኼ ሰው ሊሰልምነው  እንዴ›› ሲሏቸው እንደነበር የጠቀሱት እንዳለ ጌታ፣  ‹‹ፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ ለመማር ሲጥሩ ደግሞ ካቶሊክ ሊሆኑ ነው›› በማለት ያሟቸው  ነበር ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው የጉዞ ማስታወሻ በሚጽፉበት ወቅት ጃፓን፣ ኢየሩሳሌም፣ ግሪክ፣ ፈረንሣይና ለንደን ሲሄዱ ያጋጠማቸውን ሲጽፉ፣ ልክ እንደ መዕዋለ ዜና ዘጋቢ የገጠማቸውን ገጠመኝ፣ የተደረገላቸውን አቀባበል፣ ያዩትንና የሰሙትን ይከትቡ ነበር ይላሉ፡፡

የጠቅላላ ዕውቀት መጻሕፍትን በሚያዘጋጁበት ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ አገር በሚሄዱበት ወቅት በዕውቀት ጉድለት ምክንያት አገርን እንዳያሰድቡ አስቀድመው ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሳይተዋል ያሉት እንዳለ ጌታ (ዶ/ር)፣ በዚህም አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ ውጭ አገር በሚሄድበት ወቅት ከዚህ ቀድሞ ያላየውን አዲስ ነገር ሲመለከት ትልልቅ ሕንፃዎችን፣ ትልልቅ የምግብ ገበታዎችን በሚመለከትበት ወቅት አንድ ጊዜ ካየ በኋላ ዝም ማለት ወይም ደግሞ ደጋግሞ አለማፍጠጥ እንዳለበት ምክር ይሰጡ እንደነበር አብርርተዋል፡፡

ይህም ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ስህተት ሠርተው የአገርን ክብር እንዳያበላሹ በማሰብ የፃፉት ምክር አዘል ጽሑፍ ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ፈረንጆች የጻፉት መጽሐፍ እንዳለ የጠቀሱት እንዳለ (ዶ/ር)፣ የሁለቱን ጸሐፊዎች ሐሳብ ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) በአንድ መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የጻፉት አንድ ኢትዮጵያዊ በዕውቀት ጉድለት ምክንያት ስህተት እንዳይፈጥር›› ሲሆን፣ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ደግሞ ፈረንጆች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ነገሮችን የአገርን ገመና ከመደበቅ አኳያ እንደሆነ በማሰብ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ብዙ ጊዜ ወደውጭ ሲመላለሱ የነበረው ለጉብኝት ነበር የሚሉት እንዳለ፣ ጃፓንን ለመጀመርያ ጊዜ የረገጡት እሳቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አዲስ ዓለም የተባለው መጽሐፋቸው በ1925 ዓ.ም.  የታተመው ጎሐ ጽባህ ባሉት የራሳቸው ማተሚያ ቤት ሲሆን፣ መጀመሪያ ታትሞ ሲወጣ በስማቸው አልነበረም የሚሉት አቅራቢው፣ ‹‹በደራሲው ስም መጻፊያ ላይ ‹‹የአገሩን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን መታደስ ከሚወድ ከአንድ ሰው የተጻፈ›› የሚል ነው፡፡

የደራሲው ስም ለምን እንዳልተጠቀሰም  ‹‹በእኔ ግምት›› ብለው ሲገልጹ፣ በአንድ በኩል ለትህትና ነበር፣ ቀደምት ኢትዮጵያውያን መጽሐፍ በሚጽፉበት ወቅት ስማቸውን አይጽፉምና  ያሉ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ያነሱት ሐሳብ አንዳንድ የሃይማኖት ሰዎችንና የባህል ተቆርቋሪ ነን ብለው ከሚያስቡ ሰዎች ጋር ያጋጨኝ ይሆን የሚል ፍርኃት አድሮባቸው ይሆን ብሎ መገመት ይቻላል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ኅሩይ ወደ አገር ቤት የሚመጡ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር የሚቀድማቸው አልነበረም፡፡ ስልክ አዲስ አበባ በገባበት ወቅት በግላቸው (በቤታቸው) አስገብተው ሲጠቀሙ ከነበሩ አራት ሰዎች መካከል እሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ሴት ልጆቻቸውን ወደ ውጭ አገር ልከው ማስተማር ከቻሉ የመጀመርያዎቹ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩም ተገልጿል፡፡ በወቅቱ የነበሩ ሰዎችም ሴት ልጅ አግብታ መውለድ፣ ሙያም መማር እንጂ እንዴት ለትምህርት ተብሎ ወደ ውጭ አገር ይልካሉ በማለት ሲተቹ እንደነበር አክለዋል፡፡ 

በፋሺስት ጣሊያን የወረራ ዘመን (1928-1933) ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር በእንግሊዝ በስደት ሳሉ በ1931 ዓ.ም. ያረፉት ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ቀብራቸው በባዝ ከተማ ሉግዘምበርግ ሲፈጸም፣ በሥርዓተ ቀብር ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባሰሙት ዲስኩር እንዲህ ብለው ነበር፡-

‹‹ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ፡፡ ይህ የአዳም ልጆችን ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በሀገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ፣ ከኢትዮጵያም ከፍ ከአሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው፡፡ ብልኃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ ችሏል፡፡ በጊዜውም የጻፋቸው መጻሕፍት ከፍተኛ ባህሪውን የሚገልጹ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ ዕውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት፡፡ ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡››

 በኋላም ጣሊያን ሲወገድ በ1940 ዓ.ም. አፅማቸው ፈልሶ በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ ያረፉበትን 85ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ  በመካነ መቃብራቸው ላይ የታነጸው አዲስ ሐውልት መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡

የሳይንስ አካዴሚው በትስስር ገጹ እንደገለጸው፣ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት አንጋፋው የታሪክ ተመራማሪ ባህሩ ዘውዴ (ኤምሬተስ ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ገለጻ መሠረት፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነት፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ በቀይ መስቀል፣ የውጭ ዜጎችን በሚዳኝ ልዩ ፍርድ ቤት፣ በኢትዮጵያ ባንክ አስተዳደር ምክር ቤት ውስጥ በፕሬዚዳንትነት፣ ከሃያ በላይ መጻሕፍትንም በማሳተም ለአገር ልማት አገልግለዋል፡፡

ኅሩይ ኢትዮጵያ ወደ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ስትቀላቀል ልዑክ በመሆን፣ በመጨረሻም በጣሊያን ስትወረር አቤቱታዋን ለማሰማት ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ሰፊ ጥረት ያደረጉ የአገር ባለውለታ መሆናቸውን፣ በጥንታዊ የአገር በቀል ዕውቀቶችና በዓለም አቀፋዊ ጉዞና ንባብ የተቀረጹ እንደነበሩም ባህሩ አውስተዋል።

የአካዴሚው ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር  ተከተል ዮሐንስ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ አካዴሚው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የሚገኘውን የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ስመጥር ጸሐፊ፣ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መኖሪያ ቤትና ግቢን ተረክቦ የቀድሞው ይዞታውን ሳይለቅ እያለማ እየተገለገለበት እንዳለና በዚህ ታሪካዊ ሕንፃ ውስጥም በስማቸው የሥነ ጥበባት ማዕከልን በማቋቋም የተለያዩ የሥነ ጥበባት ዘርፎችን በሳይንሳዊ መንገድ የማዘመን ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኅሩይ የልጅ ልጃቸው ወ/ሮ እምዬ ተክለ ማርያም በመታሰቢያ ሐውልቱ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አያታቸው ለአገራቸው ሁለንተናዊ ሥልጣኔና ዕድገት መሻሻል ጥለው ያለፉት አሻራ፣ በትውልድ ዘንድ አበርክቷቸው ሲታወሱ እንዲኖሩ ለስማቸው ማስታወሻ የሚሆኑ ተግባራትን እያከናወኑ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚና ሌሎች አካላትንም አመስግነዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...