Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትናንቱ ጠባሳ በአዲስ ተስፋ

የትናንቱ ጠባሳ በአዲስ ተስፋ

ቀን:

‹‹እኔ በሱስ ምክንያት ብዙ ነገሬን አጥቻለሁ፣ በወጣትነት ዘመኔ ላደርጋቸው የሚገቡና ላሳካቸው የምችላቸውን ውጥኖቼን አጥቻቸዋለሁ፡፡ መሄድ በሚገባኝ መንገድ እንዳልሄድ መንገዴን እንድስት አድርጎኛል፤›› ስትል የሱስን አስከፊነት ፀፀትና ስሜት በተቀላቀለበት ንግግር ታስረዳለች፡፡

ሱስ አንዱ የሕይወቷ አካል በመሆን አብሯት ተጉዟል፡፡ ከመንገድ አስወጥቷታል፡፡ መስመሯንም አስቷታል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አቋርጣ እስክትወጣ ድረስ ፈትኗታል፡፡

‹‹ፈተናው በዚህ አላበቃም፤›› ትላለች ባለታሪኳ ወጣት ጽዮን ደጀኔ፣ በሱስ ምክንያት ካልተፈለገ የፍቅር ግንኙነት በልጅነት ልጅ እስከ መውለድ ደርሳለች፡፡ ብዙ የሕይወት ምስቅልቅል እንደደረሰባት የምትናገረው ጽዮን፣ ካለማወቅና በጓደኛ ግፊትም ሆነ በተገኘው አጋጣሚ ወደ ሱስ የገባችሁ ወይም ለመግባት የተነሳሳችሁ ወጣቶች ‹‹በእኔ ይሁንባችሁ ሱስ ሕይወትን የሚያበላሽ አደገኛ ተግባር ነው፤›› ትላለች፡፡

ወደ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት በሄደችበት ወቅት ሳታውቅ ወደ ሱስ ዘው ብላ በመግባት፣ ነገር ግን የኋላ ኋላ መውጫው ቀዳዳው ጠፍቶባት፣ ቀኑ ጨልሞባት እንደነበር ታስረዳለች፡፡

በአንድ በኩል ልጅቷ ልጅ ወልዳ የምትሆነው መላ ቅጡ ሲጠፋባት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተምረሽ ራስሽን፣ ቤተሰብሽን፣ አገርሽን ትጠቅሚያለሽ ላስተማረሽ ሁሉ ብድር መላሽ ትሆኛለሽ ብለው ስንቅን ከትልቅ ኃላፊነት ጋር ቋጥረው፣ ተማሪ ብለው ለላኳት ወላጆቿ፣ ሳልውል ሳላድር የልጅ እናት ሆንኩላችሁ ብላ ለመናገር ከሞት በላይ ሆኖ ከበዳት፡፡

‹‹እርግዝና በተፈጠረበት ወቅት ቤተሰብ እንዴት ይቀበለኛል ብዬ አሰብኩኝ፡፡ እነሱስ ወልደዋልና ሊቀበሉኝ ቢችሉ እኔ ትምህርቴን አቋርጬ፣ ፅንስ በሆዴ ይዤ፣ የተላኩበትን ዓላማ ዘንግቼ እንዴትስ ከፊታቸው እቆማለሁ ብዬ ሌሎች አማራጮችን ማማተር ጀመርኩ የምትለው ጽዮን፣ የመጨረሻ አማራጯም ጎዳና ላይ መውጣት እንደነበር ታስረዳለች፡፡ ሕፃን ልጇን አቅፋ መድረሻዋን ከጎዳና አደረገች፡፡

‹‹ሕፃን ልጅ ይዞ ጎዳና መውጣት እንዲህ ነው ተብሎ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም፤›› የምትለው ወጣቷ፣ እንኳንስ ጨቅላ ይዞ ጎዳና መውጣት፣ ፍቅረኛን ፀሐይ ላይ መጠበቅና መቆም ከባድ ነው ትላለች፡፡

ለስድስት ወራት ውሎና አዳሯን ከዚያው ስታደርግ፣ ባልዳበረ አዕምሮዋ ባልጠነከረ አካሏ ከአቅሟ በላይ የሆኑ ፈተናዎችን ተቀብላለች፡፡

ከውሾች ጋር እየተጋፋች የተደፋ ምግብን ተመግባለች፡፡ ከዚህ የከፋም አለ የምትለው ጽዮን፣ የሰዎችን አዕምሮ የሚነካ ንግግር መስማት በእጅጉ ያማል ትላለች፡፡ ‹‹ልጅሽን አምጪው እኛ እናሳድገው፡፡ አንቺ ገና ሕፃን ነሽ የራስሽን ሕይወት ኑሪ፤›› በማለት ይዘብቱባት እንደነበር ታስታውሳች፡፡

‹‹የምለውን ለመረዳትና ለማወቅ ማንም ሰው ግዴታ እዚያ ቦታ መኖር አይጠበቅበትም፤›› የምትለው ጽዮን፣ የእናቱን ጡት የማይጠባ አራስ ልጅ ይዞ ጎዳና ላይ መውጣት ምን ያህል አስከፊ ሕይወት እንደሆነ መገመትና መረዳት ቀላል ነው ትላለች፡፡

በመከራ ውስጥ እያለች ቀኑ አይመሽም ሌሊቱም አይነጋም፡፡  የደስታ ጊዜ ግን ዓመት፣ ሁለት ዓመትም ይህ ነው ተብሎ አይቆጠርም የምትለው ወጣቷ፣ አሁን ላይ ያቺን የመከራ ጊዜ፣ የጭንቅ ወራት ማሰብም ሆነ ማስታወስ በእጅጉ ይቀፈኛል፣ ካስታወስኩ ይጨንቀኛል ስትል ታስረዳለች፡፡

ነገር ግን እንደ ጨለመ አይቀርም፣ ጊዜውን ጠብቆ ሰዓቱን ቆጥሮ ጨለማም ለብርሃን ቦታውን ይለቃል፣ ወቅቱን ጠብቆ ያጣም ያገኛል፣ የተራበም ይጠግባል፣ የታረዘም መልበሱ አይቀርም፡፡ ፈተናው ሌሊቱ እስኪነጋና ጨለማው በብርሃን እስኪተካ ነው፣ ፅናቱ ከረሃብ እስከ ጥጋብ ያለው ውጣ ውረድ ነው፡፡

ሆኖም ወጣቷ እንደመሸ አልቀረባትም፣ እንዳጣች አልቀረችም፡፡ ጎዳና ላይ እንደለመነች አልኖረችም፣ ከወደቀችበት ጥሻ ተነስታለች፡፡ ቀድመው የተሰነካከሉ ዕርምጃዎቿን አስተካክላለች፣ የጠፋትን በሌላ ተክታለች፣ ጽዮን ዛሬ ላይ ቀደም ሲል የተበላሸውን መንገዷን በማስተካከል ላይ ናት፡፡ የማይመለሰውን በሌላ በመተካት፣ የጎበጠውን በማቅናት ትክክለኛ የሕይወት መንገዷን እየጠረገች እንደሆነችም ትናገራለች፡፡

የቀደመውን መጥፎ ሕይወት ማስታወስ ባልፈልግም፣ ነገር ግን በእኔ የደረሰው ይብቃ በማለት ለሌሎች ትምህርት ይሆን ዘንድ በየደረስኩበት እናገራለሁ ትላለች፡፡ በዚሁ አጋጣሚም መውደቅና መሰበር እንዳለ ሁሉ፣ መነሳትና መዳን እንዳለም ጭምር እያስተማረች እንደሆነ ታስረዳለች፡፡

‹‹አሁን እንደ ሰው ቆሜ እየሄድኩ ነው፡፡ ከእኩዮቼ ጋር ቀና ብዬ እኩል እያወራሁ ነው፤›› የምትለው ጽዮን፣ ከዚህም አልፋ ስላለፈችው ውስብስብ የመከራ ሕይወቷ ለሌሎች እያስተማረች ትገኛለች፡፡

ካለፈው አስከፊ ሕይወት አሁን ወዳለችበት በተስፋና በደስታ የታጀበ ሕይወት እንዴት እንደመጣች ባለታሪኳ ስትናገር፣ ቅን ልቦና ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም በሚቀድመው ‹‹ሰውነት›› አዛኝነትና ቅንነት በተሞሉ አስተሳሰቦች በተገኘ ሰውነት ነው፡፡

ሰውነትን ያስቀደመችው ሰው ደግሞ የመሠረት በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ መሠረት አዘገ ናቸው፡፡

‹‹ወ/ሮ መሠረት ከወደቅኩበት አንስታ ለክብር አብቅታኛለች፤›› የምትለው ጽዮን፣ እሷንና መሰሎቿን ከጎዳና ላይ ከእነ ልጇ አንስታ በሞቀ ቤትና በምቹ አልጋ በማስተኛት የላመና የጣመውን ምግብ ከማቅረብ ባሻገር፣ የትናንቱን የልጅነት ሕልሟ ይሳካ ዘንድ ማኅበሩ ለእሷና ለመሰሎቿ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሆነም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወደ መሠረት በጎ አድራጎት ማኅበር ስትቀላቀል ልጄ ምግብ ይበላልኛል፣ እኔም ከመንገድ ላይ ወደ አልጋ እሄዳለሁ በሚለው ሐሳብ እንጂ፣ ወደ ቀደመው ሕይወቴ እመለሳለሁ፣ ተምሬ እለወጣለሁ፣ ተረጋግቼ ስለነገዬ አስባለሁ የሚለውን ምኞት ረስቼው ነበር፡፡ ‹‹ሞቶ የተቀበረ ሐሳብ ነው ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበር፤›› የምትለው ጽዮን፣ ነገር ግን ከምግብ ከመጠጥም በላይ ለብሶ ከማጌጥም ባሻገር፣ ወ/ሮ መሠረት በእኛነታችን ላይ ሠርተው የትናንቱን ጠባሳችንን ረስተን፣ ይልቁንም የነገ ተስፋችን ላይ በርትተን እንድንሠራ፣ በእኔና በጓደኞቼ ላይ ሠርተው ለክብር አብቅተውናል ስትል ወ/ሮ መሠረትን አመሥግናለች፡፡

‹‹በዚህ ሁሉ የኑሮ ውጣ ውረድ ልነግራችሁ የፈለግኩት ነገር ቢኖር፣ ለሰው ልጅ አብሶ ለሴት ልጅ የሕይወት ምስቅልቅልና ውስብስብ ለሆኑ ፈተናዎች አጋልጦ ከሚሰጥ መጥፎ ሱስ ተቆጠቡ ብዬ ለማስረዳት፣ እንዲሁም ልጅ ይዞ ጎዳና ላይ መዋል ማደር በእኔ ይብቃ ለማለት ነው፤›› ብላለች፡፡

ወጣቷ በእኔ ይብቃ በሚለው መፈክር ብቻ እንዳልቆመችም ታስረዳለች፡፡ በመሠረት በጎ አድራጎት ማኅበር ውስጥ በመሆን እንደ እሷ በጎዳና በመሆን ሕይወታቸውን ለሚገፉ ሰዎች ለመድረስ፣ እየተጋች መሆኑን ለዚህም ትልቅ ተስፋን ሰንቃ እየተጓዘች መሆኑን አስረድታለች፡፡

ጽዮን በአሁኑ ወቅት ልጇን በጥሩ ሁኔታ እያሳደገች፣ በደስታና በፍቅር እየኖረች መሆኑንም ሳትገልጽ አላለፈችም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...