Saturday, July 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመውሊድ በዓል

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

‹‹መውሊድ አል-ነቢ›› ወይም ‹‹መውሊድ አን-ነቢ›› በአጭሩ ‹‹መውሊድ›› ማለት የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን ነው፡፡ ቱርካውያን ደግሞ «መውሊዲ ሸሪፍ» ይሉታል፡፡ ትርጉሙም ‹‹የተቀደሰው ልደት›› እንደማለት ነው፡፡ ፋርሳውያንም ‹‹ሚላድ ፓየምባረ ኢክራም›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የታላቁ/የቅዱሱ ነቢይ ልደት እንደማለት ነው፡፡ አልጀሪያውያን በበኩላቸው ‹‹መውሊደ ነቢ ሸሪፍ›› ሲሉት የቅዱሱ ነቢይ ልደት ቀን ማለታቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹የውም አነቢ›› ማለትም የነቢዩ ቀን ብለው የሚጠሩትና በየቋንቋቸው የሚጠሩት አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን ማለት ነው፡፡

ሱኒዎች ይህን በዓል በወርኃ ረቢዓል አወል 12ኛው ቀን ሲያከብሩት ሺዓዎች ደግሞ በወርኃ ረቢዓል አወል 17ኛው ቀን ከኢማም ጃዕፈር አል-ሳዲቅ ልደት ጋር አብረው ያከብሩታል፡፡

መውሊድ በወርኃ ረቢዓል አወል ይውላል፡፡ የዓረብኛው የቀን አቆጣጠር በጨረቃ የመሬት ዑደትን መሠረት ያደረገ ስለሆነ፣ ከኢትዮጵያም ሆነ ከአውሮፓውያን የፀሐይ አቆጣጠር ጋር ይለያያል፡፡ መውሊድ ከሳዑዲ ዓረቢያ በስተቀር በሁሉም የሙስሊም አገሮች ብሔራዊ ክብረ በዓል እንደሆነ ይነገራል፡፡

የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን በብዙ አገሮች መከበር ከመጀመሩ በፊት ሰዎች  ነቢዩ ሙሐመድ ወደ ተወለዱበት ቤት በመሄድ ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡ ይህም ነቢዩ ሙሐመድ የተወለዱበት ቤት የኸሊፋ ማህዲ ሚስት በነበረችውና የሐሩን አል-ረሺድ (145/756-169/785) እናት በሆነችው፣ በአል-ኸይዙራን  ወደ መስጊድነት ተቀየረና ብዙ ምእመናን ተሰብስበው ጸሎታቸውን የሚያደርሱበት ሥፍራ ሆነ የልደት ቀናቸው መከበር የጀመረው በግለሰቦች ተነሳሽነት እንደሆነም አንዳንድ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ በራቢዓል አወል በ12ኛ ቀን ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ባለው በዕለተ ሰኞ ይከበራል፡፡  ቀዳሚ ነው የሚባለው የነቢዩ ሙሐመድ መውሊድ ሱፊዎች የከብት መስዋዕት እያቀረቡ፣ ችቦ እያበሩ፣ እየበሉና እየጠጡ ያከብሩት እንደነበረ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢስላም እና ኢንሳይክሎዲዲያ ብሪታኒካ የተባሉት ዓውደ ጥበባት ይገልጻሉ፡፡ በተለይም ኮንሳይንስ ኢንሳይክሎፒዲያ ፊ-ኢስላም በሚል ርዕስ፣ ጎርዶን ዲ. ኒውባይ በ2006 ባሳተሙት ዓውደ ጥበብ (ገጽ 146-147) እንደሚገልጡት ‹‹የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን የውዳሴ ግጥሞችን በማቅረብ፣ ማርን ጨምሮ ጣፋጭ ምግቦችን በመብላት ያከብሩታል፡፡ አህለል በይት የሚባሉት ሙስሊሞች ደግሞ ቁርዓን በመቅራት፣ ስጦታ በመለዋወጥ ያስታውሱታል፡፡ በግብፅ ውስጥ መውሊድ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት መከበር የተጀመረው በ12ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

እዚህ ላይ መውሊድን የሚያከብሩ ሙስሊሞች እንዳሉ ሁሉ የማያከብሩ ሰለፊዎች ወይም የሸኽ አብዱልውሀብ ተከታዮች ወይም አህለል ሐዲስ ተብለው የሚጠሩ ሙስሊሞች እንዳሉ ማስታወስ ይገባል፡፡ የነቢዩ ሙሐመድን የልደት ቀን ከሚያነውሩ ሰለፊዎች መካከል የሳዑዲ ዓረቢያ ታላቁ ሙፍቲ ዓብዱል ዓዚዝ ኢብን ዓብደላ ኢብን በዓዝ፣ የመስጅድ አል-ሐረም ኢማም የሆኑት ዓብዱራሕማን አል-ሱዳይሲ፣ ዛኪር ናይክ ይገኙበታል፡፡ 

በብዙ አገሮች የነቢዩ ሙሐመድ ልደት በሚከበርበት ጊዜ ‹‹ቃሲዳ አል-ቡርዳ›› በሚል ርዕስ በ13ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈው የግጥም መጽሐፍ የሚነበብ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያና ሱዳን ያሉ አገሮች ደግሞ በራሳቸው ሊቃውንት የተገጠሙትን የውዳሴ ግጥሞች በዜማ  ያቀርባሉ፡፡ በግጥሞቹም ውስጥ የነቢዩ አወላለድ፣ የእናታቸው፣ የአባታቸውና የቤተሰቦቻቸው ታሪክ፣ የነቢዩ ሙሐመድ የልጅነት፣ የወጣትነትና የአዋቂነት ዕድሜ ክንውኖች፣ ስለደግነታቸው፣ ስለ አርቆ አስተዋይነታቸው፣ ስለነቢይነታቸው፣ ስለመጀመሪያው ራዕይ፣ በመጀመሪያ ሙስሊም ስለሆኑ ተከታዮቻቸው፣ ስለገጠማቸው ፈተና ወዘተ ይካተታሉ፡፡  ስለሆነም በፓኪስታን በተለይም በዑርዱ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ይከበራል፡፡ በፓኪስታን ዋና ከተማ በኢስላማባድም 31 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል፡፡ በክልል ዋና ከተማዎች ደግሞ 21 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል፡፡ በፊልም ቤት የሚታዩት ፊልሞች እንኳን መንፈሳዊ እንጂ ዓለማዊ አይሆኑም፡፡ በተለይም ላሆር በሚገኘው ሚናሬ-ኢ- ፓኪስታን በሚባለው መስጂድ በራቢዓል አወል 11ኛ እና 12ኛ ቀን ሌሊት ላይ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ያከብሩታል፡፡ ይህንን አከባበር ከሕዝብ ብዛት አኳያ በዓለም አንደኛ እንደሆነ የሚመሰክሩ አሉ፡፡ በኢንዶኔዥያ፣ በባንግላዴሽና በሕንድም እንደዚሁ፡፡ በዚህ ጊዜ የታላላቅ የእስልምና እምነት አባቶች መቃብሮችም ይጎበኛሉ፡፡ በአፍሪካም በኬንያ በታንዛኒያ፣ በቱኒዝያ፣ በግብፅ፣ በማሊ፣ በሱዳን ወዘተ በከፍተኛ ደረጃ ይከበራሉ፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓመት ውስጥ 3000 ጊዜ ያህል ይከበራል፡፡ ይኸውም በአገራችን በዳና፣ በንጉሥ፣ በገታ፣ በነጃሺ፣ በድሬ ሸኽ ሑሴን ወዘተ እንደሚከበረው መሆኑ ነው፡፡   

የነቢዩ ተከታዮች የመውሊድን በዓል አክብረዋል?

‹‹አዎን አክብረዋል፣ የነቢዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ልደትን እንደነቢዩ ራሳቸው ‹የተወለድኩበት ቀን ስለሆነ እጾማለሁ› በማለት በዕለተ ሰኞ እየጾሙ ያከብሩ ነበር፤›› በማለት የሚያረጋግጡ ሰነዶች አሉ፡፡ ጾም ክብረ በዓል አይደለም ብሎ የሚከራከር ሙስሊም ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ በዚያው ዕለት እርሳቸውን የሚያወድሱ፣ ፈጣሪን የሚያስታውሱና የሚያመሰግኑ ግጥሞች እያቀረቡ ያከብሩ እንደነበሩም ካዒብ ኢብን ዙቤር፣ ዓብዱላህ ኢብን ረዋህ፣ ሐሰን ኢብን ታቢት፣ ቁራ ኢብን ሐባይር እና ሌሎችም ያረጋግጣሉ፡፡ ኢብን ሰይድ አን-ናስ፣ ‹‹ሚናህ አል-መድሕ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው 180 ያህል የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮችን ስም በመዘርዘር እርሳቸውን የሚያወድሱ ግጥሞችን እንዳቀረቡ ያስረዳሉ፡፡ ይህ አይደለም፣ የነቢዩ ተከታዮች የልደት በዓላቸውን አያከብሩም ብሎ የሚከራከር ቢኖር ደግሞ ለተጨማሪ መረጃም ድ-ዳሩ ኡል ሙነዛም ፊ መውሊድ አን ነቢ አል-አዛምን መመልከት ይቻላል፡፡ ሌሎች ማስረጃዎችም እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡ 

የነቢዩ አጎት አል-ዓባስ ኢብን ዓንድ አል-ሙጠለብ ‹‹ስንወለድ ብርሃን አድማስ ከዳር እስከዳር ይበራል፡፡ እኛም በዚህ ብርሃን ውስጥ እንገኛለን፡፡ የተፈጥሮ የብርሃንና መሪ ጎዳና ምሥጋና ይግባቸውና በእርሱ አቋርጠን ለማለፍ እንችላለን፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ትንቢት ነቢዩ ሙሐመድ የራሳቸው ልደት ሲያብራሩ ትክክል መሆኑን ገልጠዋል፡፡ ኢርባድ ኢብን ሳሪድ እና አቡ ኡማምነቢዩ ‹‹በተወለድኩ ዕለት እናቴ የደማስቆን ቤተመንግሥት የሚያበራ መብራት በርቶባቸው አይታለች፤›› በማለት መናገራቸውን ጽፈዋል፡፡

ኢብን ሒሻም በሲራው መጨረሻ መስመር ላይ ሐሰን ኢብን ታቢት ‹‹አንዲትም ሴት ብትሆን የፈጣሪ መልዕክተኛ እንደሆኑት ነቢይ ያለ አልወለደችም፤›› ፈጣሪ የብርሃን ምንጭ የሆኑትን ነቢይ መፍጠሩን በአድናቆት ይገልጻል፡፡ 

ሐሰን ኢብን ታቢት፣ ነቢዩ ሲሞቱ ባቀረበው የሐዘን እንጉርጉሮ ‹‹እንዲህም እላለሁ፣ ከኔ አንዳችም ስህተት አይገኝም፣ አንድ ግን ከሁሉም ስሜት ጠፋ ርቆም እንዲቀመጥ ተደረገ፣ ፍቅሬ ግን እርሱን ማሞገሱን አላቆመም፣ ገነት ለዘላለም የምኖረውም እንዲህ በማድረጌ ይሆናል (ሲራቸው)፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሰዎች የነቢዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) የልደት ቀን ሲከበር አምባ ጓሮ ስለሚነሳ ይቅር ሲሉ ይሰማሉ፡፡ አምባጓሮ በተነሳ ቁጥር በዓል የሚቀር ከሆነ በሠርግም በሌላ በዓላትም ይነሳልና ይህንን ሁሉ ይቅር ማለት ይገባል፡፡

እንግዲህ ነቢዩ ሙሐመድ ራሳቸው የልደት ቀናቸውን በጾም ካከበሩት፣ ከርሳቸው ጋር የነበሩ ተከታዮቻቸው በጾም፣ በማሞገስና በማወደስ ካከበሩት፣ ከእሳቸው በኋላ የነበሩ ሊቃውንትም ይህንን መንገድ ተከትለው ለዓመታት ካከበሩ፣ በተለይም አህሉል ሱና የተባሉት በዚህ ረገድ ከፍተኛ ማስረጃ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ ግብፃውያን ከ11ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደ አንድ የሙስሊም በዓል አድርገው ከተቀበሉት፣ ኢብን ኸቲር አል-ሲራ አል-ነበዊ (4፡51)፤ ዓሊ አል-ቀራኒ ‹‹ሸርህ አል-ሺፋ›› በሚል ርዕስ በ1364፣ በአቡበከር አልሻፊ እና ታባሪኒ ከተደገፈ፣ ዓብ አል-ባርአል-ኢስቲዓብ በሚል ሥራቸው፣ ኢብን አል-ቃዪም በዛድ አል-መዓድ ከተነተኑት፣ ከሁለት መቶ ዓመታት በመጣና በነቢዩ ሙሐመድ ጥላቻ ላይ በተመሠረተ አመለካከት ለምን ልደታቸው እንዳይከበር ይከለከላል?

ይህ አልበቃ ካለ ኢብን መጃ (ቁጥር 3940)፣ ሱዮጢ ጃሚዕ ሳቒር ቁጥር 2221፣ ቲርሚዚ (ከ ፊታን ቁጥር 2093) አቡዳውድ ቁጥር 3711፣ ናሳዒ (ሱናነ ኩበራ ቁጥር 3483) ባይሐቅ አሥማዕ ወ ሲፋት (ገጽ 322)፣ ሹዓብአል ኢማን 6፡67 (ቁጥር 322)፣ አቡ ኑዓይም (ሒልያም 3፡37 እና 9፡238)፣ ሐኪም (1፡115-16 እና 4፡556-የተረጋገጠ)፣ አቡ ኢብን ሐማይድ (ሙስናድ ቁጥር 25966)፣ ዳሪሚቁጥር 54 (ያልተረጋገጠ)፣ ዲያዓ አል መቅዲሲ (7፡129)፣ ቁዳዒ (1፡167 ቁጥር 239)፣ ዳርቁትኒ በሱናቸው ውስጥ (4፡245)፣ ኢብን አቢ ሻይባ (8፡604፣ 672፣ 683) ታባሪኒ ሙዓጀም አል-ከቢር በተሰኘ ሥራቸው (1፡153፣ 1፡186፣ 3፡209፣ 12፡447፣ እና 17፡239-40)፤ ሳሒሕ-ሐይታኒ መጅሙዓ በተባለ ሥራቸው (5፡218-19) እንዲሁም ሙዓጀም አል-አውሳጥ (5፡122፣ 6፡277፣ 7፡193)፣ ኢብን ዓሲም ኪታብ አሱና በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 39-41 ከቁጥር 80-85፣ ገጽ 44 በቁጥር 92 የጻፉትን መመልከት ይቻላል፡፡ 

ከሁሉም የላቀ ዕድሜ ያለው ኢማም አቡዱራሕማን ሸሪፍ 156 ዓመተ ሒጅራ (ዓሊ) ‹‹ሚላድ ሸሪፍ›› በሚል ርዕስ የጻፉ ሲሆን፣ ሰይድ ሱለይማን ነድዊ ‹‹ ሲራት ናቢ›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ፣ በተለይም በሦስተኛው ቅጽ ከሦስተኛውና ከአራተኛው ምዕት ዓመት (ዓሒ) እንደሚከበር አውስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመውሊድ በዓል አከባበር

በኢትዮጵያ የመውሊድ በዓል አከባበር ከአካባቢው የሙስሊም አገሮች በተለይም ከሱዳን፣ ከግብፅ፣ ከሶማሊያና ከጅቡቲ ጋር በአብዛኛው ይመሳሰላል፡፡ 

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በኢትዮጵያ የነቢዩ ሙሐመድ ልደት ቀን ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች መካከል በትግራይ ነጋሺና በሆጂራ ፎቂሳ (ራያ)፣ በሰሜን ወሎ ዳና፣ በደቡብ ወሎ በጃማ ንጉሥ፣ በባሌ በድሬ ሸኽ ኹሼን በሚከበርበት ጊዜ ከሥፍራው ተገኝቶ የመመልከት ዕድል ገጥሞታል፡፡ በሁሉም ሥፍራዎች ሙስሊሞች ከአገሪቱ አራት ማዕዘናት ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምሮ ይመጣሉ፡፡ በመስጊዶችና በመስጊዶች ዙሪያም ይሰፍራሉ፡፡ በዕለቱም በጎች፣ ፍየሎች፣ ሠንጋዎችና ግመሎች ሊታረዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች እንዳይቸገሩ ውኃና እንጨት ይዘጋጃል፡፡ ከየአቅጣጫው የሚመጡት እንግዶችም ችግሩን አስቀድመው ስለሚገነዘቡ ከሚያቋርጡት ወንዝ ውኃ፣ ከደን ደግሞ ደረቅ እንጨት ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በዕለቱ የሚመቱ ድቤዎች በፀሐይ ብርሃን ሲመቱ ይሰነብቱና ከብረት እንደተሠራ ብረት ወይም የብረት ድምፅ ያለው በሃ ድንጋይ «ኪው፣ ኪው» የሚል ድምፅ እንዲያመጡ ይደረጋል፡፡  የታወቁ የሃይማኖት አባቶች ከተከታዮቻቸው ጋር በመስጊዱ ወይም በመስጊዱ ዙርያ ይቀመጣሉ፡፡ ምርጥ ጫት እስከሚያምር ዛላው መታደል ይጀመራል፡፡ ፈጣሪንና ነቢዩ ሙሐመድን የሚያወድሱ ዜማዎች መውረድ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከዚች ዝባዝንኬ የበዛባት ዓለም ቀስ በቀስ በመንፈስ የሚወጡ ሰዎች አድናቆታቸውን በከፍተኛ ድምፅ ማሰማት ይጀምራሉ፡፡ ስለፈጣሪያቸው ፍቅር፣ ስለነቢዩ ፍቅር ሲወዘወዙ ለብ ያለ ነፋስ የሚጓዝበት የጤፍ ምርት ይመስላሉ፡፡ በአምስቱ የሰላት ሰዓቶችና በምግብ ሰዓት ካልሆነ ዕረፍት የለም፡፡ የደወል ድምፅ ያላቸው ድቤዎች በቅርቡ ያለውን ሰው ልብ በደስታ ሲማርኩ በሩቁ ያለን ደግሞ «ና ወዲህ» በማለት ይጣራሉ፡፡ ቦታው ሁሉ ፍቅር በፍቅር ይሆናል፡፡ ቀኑና ሌሊቱን በጸሎትና በምህላ፣ ቁርዓን በመቅራትና ሐዲሶችን በማንበብ ያሰለፉት ምዕመናን በዕለቱ ወዳለፉ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ሙስሊሞች መቃብሮች በመሄድ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት እንድታስቀምጥ ጸሎት አድርገው ይመለሳሉ፡፡ ረፋድ ላይ የነቢዩ መሐመድ ልደት ማክበር የተፈለገበት ምክንያት ገለጻ ይደረግና አገሪቱና ሕዝቧ በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ በመጸለይና በመመረቅ ይለያያሉ፡፡ በእግሩም፣ በአጋሰስም፣ በመኪናም የመጣው ምዕመን በተመኘው ሥፍራ ጸሎት አድርሶ በመመለሱ መንፈሱ በደስታ ይሞላል፡፡

የነቢዩ መውሊድ ከሱፊዝም ጋር ስለመያያዙ

ቀደም ባለው የመውሊድ አከባባር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ወደ አንዱ መስጊድ ሄደው እንደሚያከብሩ ተገልጿል፡፡ በመሠረቱ እንዲህ ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በአገራችን እጅግ ቀላል ይሁን እንጂ በሌሎቹ አገሮች የሚናፈቅ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ግን የራሱ የሆነ ታሪካዊ ምክንያት አለው፡፡ ስለሆነም ይህንን አኩሪ ታሪካችን ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ተስማምተንና ተግባብተን እንድንኖር ያደረገ ስለሆነ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ መታወቅ ሲኖርበት ሙስሊሙን ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኑና ሃይማኖት የሌለውን ጭምር በመርዳት የሚታወቁት ሱፊ አባቶቻችን በዚች አገር ላይ ሰላምና መቻቻል እንዲሰፍን አስችለዋልና እነርሱንም ለማወደስና ለማሞገስም በግድ ሱፊ መሆን እንደማያስፈልግ ጸሐፊው ያምናል፡፡ ስለዚህ እኒያ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች ምን አደረጉ? እንደምንስ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች የመቻቻል፣ አብሮ የመኖርና የፍቅር መንገዶች ሆኑ? ብለን እንጠይቅ፡፡ አንድ በአንድም እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

በመሠረቱ፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከጥንት ጀምሮ ከጂቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን፣ ከግብፅ፣ ከየመንና ከሳዑዲ ዓረቢያ ሙስሊሞች ጋር መልካም ግንኙነት ሲኖራቸው በተለይም ወደ ግብፅና ሱዳን ሄደው የእስልምና ትምህርት የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከአጎራባች ሙስሊም አገሮች የሚጋሯቸው ኢስላማዊ እሴቶች በስምምነትና በመተሳሰብ እንዲኖሩ ያደረጓቸው ሲሆን፣ በተለይም ተመሳሳይ የሱፊ ስርዓት በመቀበላቸው አንደኛው ተማሪ ወደ ሌላው ሄዶ ትምህርት እንዲቀስም አስችሎታል፡፡

በአገር ውስጥም ቢሆን የአንዱ ክልል ሙስሊም ተማሪ (ደረሳ) ወደሌላው ክልል ሸኽ ሔዶ መማር የተለመደ ሲሆን፣ በሶማሌ ውስጥ የቃዲሪያ፣ የአሕመዲያ-ኢድሪስያ፣ የሳሊሕያ፣ የራፊዒያ፣ ጦሪቃ የነበረ ከመሆኑም በላይ ወደነ ሸኽ አብዱራሕማን አል-ዘይላዊ፣ የሸኽ ኢብራሂም ሐሰን ጀብሮ ከሐረርጌ፣ ከባሌ፣ ከዓፋር ሄደው ይማሩ እንደነበረ ሁሉ ከሶማሌም ወደ ሐረር መጥተው ይማሩ ነበር፡፡  ከነዚህም መካከል የአሕመዲያ-ኢድሪስያ ጦሪቃ የተመሠረተው በአህመድ ኢብን ኢድሪስ ሲሆን፣ ይህም ከ1760-1837 እንደዘለቀ ይታወቃል፡፡ የአሕመድያ ኢድሪስያን ጦሪቃ የማይከተሉት የሳሊሐን ጦሪቃ በ1887 አካባቢ የመሠረቱ ሲሆን፣ ይህም ጠሪቃ በተለይ በኦጋዴን ተስፋፍቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የታወቁት የሶማሌ ሸኽ ዓዌስ ሙሐመድ ባራዊ (1909 አረፉ.)፣ የሳሊሕያና የአሕመዲያ-ኢድሪስያ ጠሪቃ በሸበሌና በጁባ ወንዞች አካባቢ ጀምዓት ፈጥረው እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ሸኽ ዓብዱራሕማን ዓብዱላህ (ሞቃዲሹ) የኡጋዴን በተለይም የሙስታሂል፣ የፈርፌር፣ የጎዴ ደረሶች እየሄዱ ትምህርት ይቀስሙባቸው ነበር፡፡ 

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በተለይም በሶማሊያ አካባቢ የነበረውን ትሥሥር ለመጥቀስ ያህል እንጂ በወሎ የነበረው የሸኾች መደድም (የሸኾች መንደር-ሰፈር) ቢሆን፣ ከአገሪቱ አራት ማዕዘናት ከአጎራባች አገሮች የሚመጡትን ደረሶች ጭምር እየተቀበለ ያስተናግድ ነበር፡፡ ይኸው ከ18ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን በወሎ ተንሰራፍቶ የነበረው መደድ እስከ ሰሜናዊ የአገሪቱ ግዛት የተንሰራፋ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ዛሬ በወሎ ያሉት ዶሪሆች ከጭቃም ይሠሩ ከአጣና ታዛም ይሁኑ ጎጆዎች የእነዚያ ታላላቅ ሸኾች መኖሪያዎች ነበሩ፡፡

የሱፊ ወንድማማችነት ሥርዓት በአገራችን በኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጊዜ በሰፊው የገባ ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት የሰይድ አብዱልቃድር ጀላኒ ተከታዮች በሐረር፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በኤርትራ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በኦሮሚያ ክልል በብዛት ይገኛሉ፡፡ ስለሱፊያ የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን ስለከራማቸው የሚያውቅ እንደሚበዛ ግን ጥርጥር የለውም፡፡ በአገራችን የውጭ ወራሪ ብዙም ስላልነበረ የተለያዩ ጠሪቃዎች (የሱፊ ሥርዓቶች) በተለያዩ ጊዜያት ቢገቡም እንኳ የቱ በምን ጊዜና ምክንያት እንደገባ ማወቅ ሰፊ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ዳሩ ግን ከጥንታውያኑ የኢትዮጵያ ግዛቶችና ከአሁኖቹ ከአጎራባች አገሮች ጋር በማገናዘብ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከጂቡቲ፣ ከኤርትራ በኩል ምን ጠሪቃ እንደገባ በጥቅሉ ማየት ይቻላል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሱፊ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች አሰተሳሰብና እምነት ከሌሎች አገሮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እነሱም ከሁሉ አስቀድሞ መሠረታዊ የእስልምና እምነትን የተቀበሉ ሲሆን፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቁርዓኑና ሐዲሱን ጠንቅቀው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ብዙዎቹም ሐፊዞች (ቁርዓኑን በቃላቸው የያዙ) እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አራቱንም ማለትም የሐነፊ፣ የማሊኪ፣ የሻፊዒና የሐንበሊ መዝሀቦች ልዩነታቸውንና አንድነታቸውን ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ዕውቀቶች ከጨበጡ በኋላ ያሉትን የጦሪቃ ስሞችና ዓይነቶች ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሱፊ አባቶች ስለ ጠሪቃ መሪዎች ሲጠየቁ ትክክለኛ መልሶችን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጠሪቃውን ለመቀበል የሚያስችሉ ደረጃዎችን ማጥናት አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ በዚክር፣ በተፈኩር፣ በኻልዋ፣ በሸኾች ዕርዳታ ጦሪቃውን ይቀበላሉ፡፡ 

ይህም ሆኖ ደግሞ የኢትዮጵያ ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች ታሪኹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በግለሰቦች እጅ ታምቆ ቆይቷል፡፡ ግለሰቦችም በቃል፣ በእጅ ጽሑፍ፣ በእንጉርጎሮና በመንዙማቸው ከትውልድ ትውልድ ሲያስተላልፉት ቆይተዋል፡፡ የነዚህ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ በኅትመት ጽሑፍ፣ በድምፅና በፊልም መቀረፅ የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ከነዚህም ሥራዎች ውስጥ 1) የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክን በካሌት ያስቀረፁት ሸህ መሐመድ ወሌ፣ 2) የአውሊያዎችንና ሙሻኢኮችን የሚያወድሱት ሸህ ሙሐመድ አወልና አብዱል ወሃብ ሸህ በድሪዲን፡፡ 3) ‹‹አራት ዓይኖቹ›› በሚል ርእስ ስለ አውሊያዎች መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ፣ 4) በወለኔ ሸህ ዑመር ሸህ በሺር የተጻፈ የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ (ጥሮነ) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 5) የሸኽ ሁሴን ጅብሪልን ትንቢት  ያሳተሙት አቶ ቦጋለ ተፈሪ  6) ከነዚህም ሌላ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በዓረብኛ ወዘተ. የተጻፉትና በግለሰቦች እጅ የሚገኙ ትልልቅ መጻሕፍትም አሉ፡፡ ከነዚህ ሁሉ መረጃዎች ውስጥ ለታሪክ ቀረቤታ ያለው ሸህ ሙሐመድ ወሌ በቴፕ ያስቀረፁት ትንታኔና በወለኔ ሸህ ዑመር ሸህ በሺር የተጻፈ ‹‹የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ (ጥሮነ)›› እጅግ ጠቃሚ መረጃዎች ሲሆኑ፣ ሸኽ ሙሐመድ አወል መንዙማዎችና እንጉርጉሮችም ለምርምር በር የሚከፍቱ ናቸው፡፡ 

ምንም እንኳን ሌሎች መረጃዎችን ማጥናት የሚገባ ቢሆንም በአገራችን የነቢዩ መሐመድ መውሊድ መከበር ከጀመረ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ነው የሚሉ ቢኖሩም ይኸው በዓል በተወሰኑ ሥፍራዎች ተወስኖ ይኖር እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዓሉ የመንግሥትን ይሁንታ አግኝቶ በብሔራዊ ደረጃ መከበር ከተጀመረ ደግሞ 50 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ በዓል ከያዘው መንፈሳዊ ፋይዳ በተጨማሪ የሕዝብን በዚያ አጋጣሚ ስለአገሩ እንዲያውቅ፣ በዝቅተኛ ደረጃ የሚነግዱትን የሚረዳ፣ እርስ በርስ የሚያስተዋውቅና በአጭሩም ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ሕዝቡና መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ የሕዝብ በዓል ነው፡፡ 

በመጨረሻም አንድ ነጥብ፣ ያከበረንም ያላከበረንም ፈጣሪ ያየዋል፣ ይሰማዋል፡፡ የራሱንም ፍርድ ይሰጣል፡፡ የሰው ልጅ አንድን ነገር የሚያየው በተለያየ መንገድ ነው፡፡ ቀለምንና ድምፅን እንኳን እኩል አያይም፣ እኩል አይሰማም፡፡ በአጭሩ በፈጣሪ ሥራ ገብቶ መጣላት አያስፈልግም፡፡ ይልቅ ሌላ ለአገር የሚጠቅም ሥራ በአንድ ላይ እንሥራ፡፡ 

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles