Monday, December 11, 2023

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ ከተማ ነዋሪ፣ ከቅዳሜ ጀምሮ ከባድ ውጊያ በአካባቢው መኖሩን ተናግረዋል፡፡ እሑድ ዕለት የድሮን ጥቃት መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ በድሮን መፈጸሙን በምን ሊያውቁ እንደቻሉ ነዋሪው ተጠይቀው ነበር፡፡ ጋሸና ሄደው ስለነበር የድሮኑን ድምፅ እንደሚለዩት በመጥቀስ፣ የድሮኑን ጥቃትና አጣጣሉንም በተመለከተ በድምፁ አቅጣጫውን እንደሚለዩ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በአማራ ክልል ተፋፍሞ በቀጠለው ውጊያ ድሮን እየተጠቀመ ይገኛል ነው ቅሬታ በተደጋጋሚ ቢሰማም፣ ነገር ግን ለዚህ ማረጋገጫ በመንግሥት በኩል ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ያም ቢሆን ግን መከላከያ በከባድ መሣሪያ በመታገዝ ከፋኖ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ መሆኑ በውጊያው ቀጣና ካሉ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ይፋ እንዳደረገው ደግሞ፣ መንግሥት በአማራ ክልል ቢያንስ አንድ ጊዜ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በትግራይና በአሮሚያ ክልሎች ጭምር የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአሳሳቢ ሁኔታ መቀጠላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተለው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የባለሙያዎች ኮሚሽን፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለመቋጨት የሰላም ስምምነት ቢፈረምም ነገር ግን የኢትዮጵያ ቀውስ ተባብሶ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ መሐመድ ቻንድ ኦዝማን ባቀረቡት ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል ጦርነቱ ከፈነዳ ጀምሮ ኢትዮጵያ ያየችውን የሰብዓዊ ድቀት በቃላት ለመግለጽ ከባድ ነው ብለዋል፡፡

‹‹Despite the signing of cessation of hostilities agreement in Pretoria last November more than ten months later the situation in Ethiopian remains grave. The signing of the agreement neither resolve the conflict nor brought about comprehensive peace in Ethiopia››.

‹‹ግጭት የማቆም ስምምነት በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ቢፈረምም፣ ከአሥር ወራት በላይ ግን የኢትዮጵያ የቀውስ ሁኔታ ተባብሷል፡፡ የሰላም ስምምነቱ መፈረም ግጭቶችን አልቋጨም፣ የተሟላ ሰላምም አላስገኘም፤›› በማለት ነበር ቃል በቃል የተናገሩት፡፡

ኮሚሽኑ ይፋ እንዳዳረገው በኢትዮጵያ የጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማስራብ፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትን ማውደም፣ ከቤት ንብረት ማፈናቀል፣ አሻሚ የሆኑ የጅምላ እስራቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈጸሙ ነው ብሏል፡፡

እነዚህ ኮሚሽኑ የመዘገባቸው ጥሰቶች ደግሞ የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ የተቃጡ ወንጀሎች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ የፌደራል መንግሥቱ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶችና ደኅንነት ማስጠበቅ አቅቶታል ይላል፡፡ በሌላ በኩል በሰላም ስምምነቱ ለመፈጸም የገባውን ቃል መወጣት እንደተሳነው ያስረዳል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር ተሻግሮ የኢትዮጵያ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ማስቆም አልቻለም በማለት ነው ኮሚሽኑ ጠንካራ ወቀሳ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያቀረበው፡፡

ለአንድ ዓመት ኃላፊነት ተሰጥቶት የተመሠረተው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተባለው ይህ ኮሚሽን፣ የትግራይ ጦርነት ከፈነዳበት ጊዜ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን መርምሮና አጣርቶ ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ ኮሚሽኑ የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ ገደቡ እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚራዘምም ነው የተነገረው፡፡

ከሰሞኑ ሒዩማን ራይትስዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማትና የሲቪክ ማኅበራት፣ ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜው እንዲራዘም በይፋ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡

የፊታችን ሐሙስ ለተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ቀርቦ ተጨማሪ ውይይት የሚካሄድበት የኮሚሽኑ ሪፖርት ብዙ ግጭቶችን ይዞ መጥቷል፡፡ ኮሚሽኑ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2022 የተመሠረተ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ሸፈንኩት ያለውን ከትግራይ ክልል ጦርነት መፈንዳት ጀምሮ በአገሪቱ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓይነት በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ብሎ በተለያዩ ረድፎች ዘርዝሮ ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡

በሰብዓዊ መብቶች ካውንስሉ ውሳኔ ቁጥር S-33/1 እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 2021  የተመሠረተው የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽኑ፣ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ የመከታተል ኃላፊነት እንደተሰጠው ነው የሚናገረው፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕጎችና ጥሰቶች፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብቶች ሕጎችና ጥሰቶቻቸውን በኢትዮጵያ እንደሚከታተልም ገልጿል፡፡ ይህም የትግራይ ክልል ጦርነት ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የቀጠለውን ሁኔታ እንደሚያካትት ነው የኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያብራራው፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት የተጠናቀረበት ሒደት 545 ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ እንዲሁም 570 አጋዥ ሰነዶችንና የመረጃ ምንጮችን በመመርመር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርቱን በማጠናቀር ሒደት የመንግሥት ትብብር መጓደል ትልቁ እንቅፋት እንደሆነበት ነው ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው፡፡ የኤርትራ መንግሥትንም በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሚያደርገው ሪፖርቱ፣ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ምላሽ እንዲሰጥ ለኤርትራ መንግሥት ቢጽፍም አንዳችም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ነው ያስታወቀው፡፡    

በዚህ ሪፖርት ከኤርትራ ሠራዊትና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመወንጀል በተደጋጋሚ ስማቸው ተነስቷል፡፡

በትግራይ ክልል የጅምላ ግድያዎች በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 12 ቀን 2020 በዛላምበሳ፣ ኖቬምበር 20 ቀን በዓድዋ  በኤርትራ ሠራዊት ጅምላ ግድያ ተካሂዷል ይላል፡፡ በተመሳሳይ በኤርትራ ሠራዊት ኖቬምበር 30 ቀን 2020 በማሪያም ድንገላት አካባቢ፣ እንዲሁም ኦክቶበር 25 ቀን 2022 በማሪያም ሸዊቶ ጅምላ ግድያዎች ተካሂደዋል በማለት ያስረዳል፡፡

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደግሞ ጃኑዋሪ 8 ቀን 2021 በቦራ ግድያ መካሄዱን ሪፖርቱ ያክላል፡፡

የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን የሚመለከት በትግራይ ክልል ከዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ጀምሮ እስከ 60 ዓመት አረጋዊያን ድረስ የመደፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል ይላል፡፡ ነፍሰ ጡሮች ጭምር የመደፈር አደጋ እንደገጠማቸው የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ አንዲት ሴት የተገደሉ ቤተሰቦቿ አጠገብ የመደፈር ዕጣ ገጥሟታል ሲል ያትታል፡፡

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀበት እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 2 2021 ጀምሮ ደግሞ፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የትግራይ ተወላጆችን ዒላማ ያደረገ የጅምላ እስራት መፈጸሙን ነው ሪፖርቱ ያካተተው፡፡

በአማራና በአፋር ክልሎችም ተከታታይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያትተው ሪፖርቱ፣ በተለይ የሕወሓት ኃይሎች በከፈቱት ጥቃት ብዙ ጉዳት መድረሱን ይጠቁማል፡፡ የትግራይ ኃይሎች እ.ኤ.አ. ከጁላይ እስከ ዲሴምበር አማራ ክልል በገቡባቸው ወራት ከ11 ዓመት ታዳጊ ጀምሮ የመደፈር ጥቃት በክልሉ መፈጸሙን ይገልጻል፡፡ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ በሚገኙ በ11 ከተሞችና አካባቢዎች አሰቃቂ ጥቃቶችን አድርሰዋልም ይላል፡፡ በዋግ ህምራ፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን በሸዋ አካባቢዎች ይኼው ጥቃት መከሰቱን ይገልጻል፡፡

በቆቦ ከተማ ሰሜን ወሎ ዞን፣ በጭና ሰማን ጎንደር ዞን፣ እንዲሁም በሸዋ ሮቢት ከተማ የደረሱ የሲቪሎች ግድያዎችን በተለየ ሁኔታ ሪፖርቱ ይጠቃቅሳል፡፡ ከግድያና ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች በተጨማሪም በጭና፣ በደሴ፣ በቆቦ፣ በላሊበላ፣ በሰቆጣ፣ በሸዋ ሮቢትና በሌሎች አካባቢዎችም ትምህርት ቤቶች፣ የሕክምና ተቋማት፣ የፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከባድ ዘረፋ እንዳጋጠማቸው ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

በአፋር ክልልም ቢሆን የሕወሓት ኃይሎች በዘመቱባቸው በበርሀሌ፣ አባላ፣ ካሳጊታ፣ ኢረብቲና ኮነባ አካባቢዎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት መደረጉን በዚሁ ሪፖርት ተካቶ ቀርቧል፡፡ የመኖሪያ ቤቶች ዘረፋን ጨምሮ የዜጎች ምግብና መጠጥ ሳይቀር መዘረፉን ይገልጻል፡፡ ግመል፣ ከብትና ሌሎች የቤት እንስሳት ዘረፋም በሰፊው መካሄዱን አብራርቷል፡፡ ከ2020 እ.ኤ.አ. ወዲህ በአፋር ክልል በጦርነቱ በተቀበሩ ፈንጂዎች ወደ 185 ሰዎች መሞታቸውንም ነው ሪፖርቱ ያመላከተው፡፡

ሌላው የሪፖርቱ ግኝት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን የተመለከተ ሲሆን፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ካጋጠመው የከረዩ አባገዳዎች ግድያ ጀምሮ በወለጋና በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች የደረሱ ቀውሶችን ለመዘርዘር ይሞክራል፡፡

በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ እ.ኤ.አ. ሜይ 11 ቀን 2021 የኦነግ ሸኔ አባል ነው በሚል አንድ ወጣት በአደባባይ መገደሉን ሪፖርቱ ያወሳል፡፡ በመንግሥት ኃይሎች በተለይ የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው በተባሉ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ጨከን ያለ መሆኑን የሚያስረዳው ሪፖርቱ፣ በመንግሥትና በኦነግ ሸኔ ኃይሎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች መፈጠራቸውን ይገልጻል፡፡ በተለይም የምዕራብ ኦሮሚያ አብዛኞቹ አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴ የሌላቸውና የማይደረስባቸው ሆነው መቅረታቸውን ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡

ከዚህ ውጪም የኤርትራ ሠራዊት ዛሬም ድረስ ከኢትዮጵያ (ከትግራይ) ድንበር ሙሉ ለሙሉ ለቆ አለመውጣቱን አሳሳቢ ችግር ስለመሆኑ ሪፖርቱ ያወሳል፡፡ የአማራ ኃይሎች የትግራይ ክልልን ሙሉ በሙሉ ለቀው አልወጡም የሚል ሐሳብንም አብሮ ያክላል፡፡ በኢትዮጵያ ከጦርነት በተጨማሪ ድርቅና የአንበጣ ወረርሽኝ ሌላ የቀውስ ምንጭ መሆናቸውን፣ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን የአገሪቱ ሕዝብ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂነት መዳረጉንም ይገልጻል፡፡

ሪፖርቱ በርካታ ምክረ ሐሳቦችንም ያቀረበ ሲሆን፣ በተለይ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችና ስምምነቶች የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት ተገዥ እንዲሆኑ ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ቀውሶችን የማስቆም ኃላፊነት እንዳለበትም ሪፖርቱ ያሰምርበታል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም የግጭት ተሳታፊ ኃይሎች መንግሥትን ጨምሮ ጠመንጃቸውን በመጣል ወደ ብሔራዊ ምክክር መድረክ እንዲመጡም ይጠይቃል፡፡ ሪፖርቱ አያይዞም የሽግግር ጊዜ ፍትሕ በኢትዮጵያ በገለልተኝነት መካሄዱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የሚያሳስበው፡፡

ይሁን እንጂ ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል በኦነግ ሸኔ ኃይሎች በተደጋጋሚ መፈጸሙ የሚነገረውን በወለጋና በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግድያዎችን በተመለከተ ምንም ዓይነት ነጥብ አላነሳም፡፡ ሪፖርቱ በትግራይ ክልል ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሰጠውን ያህል ሰፊ ሽፋን፣ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ላጋጠሙ ችግሮች ብዙም ትኩረት አለመስጠቱም ተስተውሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -