Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ላይ እያሳረፈ ካለው ተፅዕኖ ባሻገር፣ በክልሉ ያሉ እንደ አበባ እርሻ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ውድመት በማድረስ ሥራቸውን እንደተስተጓጎለ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአማራ ክልል የሚገኙ ስድስት የአበባ እርሻዎች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሥራ አቁመዋል፡፡

እንደ ማኅበሩ መረጃ በአማራ ክልል በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ሥራ ላይ ያሉ ስድስት እርሻዎች ሲሆኑ፣ በእነዚህ እርሻዎች ላይ በደረሰ ጥቃት የንብረት ውድመትና ስርቆት በመፈጸሙ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡  

በአማራ ክልል አለመረጋጋቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ፣ የአበባ እርሻዎች ተረጋግተው ሥራቸውን ለመሥራት አለመቻላቸውን መረጃው የሚጠቁም ሲሆን፣ ከጉዳቱ ባለፈም በአበባ እርሻዎቹ ንብረት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አመልክቷል፡፡ ከጥቃቱ ባሻገርም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ግብዓቶች ተዘርፈው መወሰዳቸው እርሻዎቹን አደጋ ላይ መጣሉን መረጃው ያመለክታል፡፡

በተለይ በባህር ዳር ዙሪያ የሚገኙ የአበባ እርሻዎች አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ማምረት በማቆማቸው ድርጅቶቹ ላይ እያስከተለ ካለው ኪሳራ ባሻገር በእርሻዎች ላይ ይሠሩ የነበሩ ከሦስት ሺሕ ያላነሱ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በክልሉ በሚገኙ የአበባ እርሻዎች የደረሰውን ጉዳትና አጠቃላይ ችግር የተመለከተ  መረጃ በማሰባሰብ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ እርሻዎቹን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት መወሰድ ይገባቸዋል የተባሉ ዕርምጃዎች በማኅበሩ በኩል መቅረቡንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የአበባ እርሻዎቹ በገጠማቸው ችግር አገልግሎት ካቆሙ ከሁለት ወራት በላይ መሆኑን የሚጠቁመው መረጃ፣ በዚህ ሁኔታ ሥራ በማቆማቸው ምክንያት ከእነዚህ የአበባ እርሻዎች ለውጭ ገበያ መቅረብ የነበረበት አበባ ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቢሆን የወደመውን ንብረትና የተሰረቀውን ዕቃ ተክቶ ወደ ሥራ ለማስገባት ጊዜ የሚወሰድ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚቸገሩም ተጠቁሟል፡፡ 

እነዚህ የአበባ እርሻዎች ሥራ ከማቆማቸው በፊትም ያመረቱትን አበባ ለገበያ ለማቅረብ ሳይችሉ በመቅረታቸው ለኪሳራ የተዳረጉ ጭምር መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

እርሻዎቹን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የደኅንነት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የገለጸው ማኅበሩ፣ የተፈጠረው ሁኔታ ማጣራት ሊደረግበት እንደሚገባም በማመልከት በጉዳዩ ላይ መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡

የእርሻዎቹ ሥራ ማቆም እያስከተለ ያለውን ጉዳት ከግምት በማስገባት በአፋጣኝ ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተገኘ የእርሻው ባለቤቶች ላይ ሊደርስ ከሚችለው ኪሳራ ባሻገር፣ አጠቃላይ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ላይ አሉታዊና ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችል ስለመሆኑም ካገኘነው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

‹‹በእርሻዎቹ ላይ የደረሰውን አደጋ የሚያጣራ አካል ተቋቁሞ መፍትሔ ሊሰጥበት ይገባል፤›› ሲል ያሳሰበው ማኅበሩ፣ በአበባ እርሻዎቹ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመተካትም መንግሥት ተጨማሪ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ እርሻዎቹ የወደሙ ንብረቶቻቸውን መልሶ ለመተካትና ወደ ሥራ ለማስገባት ደግሞ ከመንግሥት ከሚጠብቁ ማበረታቻዎች መካከል የወደሙ ንብረቶችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት ዕድል አንደኛው አማራጭ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በተከታታይ በእርሻዎቹ ላይ በደረሰው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ከወደሙ ንብረቶች መካከል ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ ማሽኖች፣ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች፣ ለመስኖ ልማት የሚውሉ ግብዓቶች የውኃ ፓምፖችና ሌሎች ዕቃዎች ይገኙበታል፡፡ ለአስተዳደርና ለሌሎች አገልግሎቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ግንባታዎችም ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ለእርሻዎቹ የተዘረጋው ኤሌክትሪክ ኃይል ጭምር የተቋረጠ ሲሆን፣ ለአበባ ማቆያ የሚገለገሉባቸው ማቀዝቀዣ ቤቶች (ኮልድ ሩም) በደረሰባቸው ጥቃት ዳግም ለአገልግሎት ሊውሉ የማይችሉ መሆኑም ታውቋል፡፡

ባገኘነው መረጃ መሠረት ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው ተብለው የተጠቀሱት የአበባ እርሻዎች ባዩ ፍሬሽ፣ ባህር ዳር ፍሬሽ፣ አልፋ ፍሎራ፣ ጣና ፍሎራ፣ አስፋ ራገስና ቆቃ ጌጅ የተባሉ እርሻዎች ናቸው፡፡ እነዚህ እርሻዎች ከ40 እስከ 100 ሔክታር ቦታ ተረክበው በተለያየ ደረጃ የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከስድስቱ እርሻዎች መካከል አራቱ የቤልጂየም፣ የቺሊ፣ የሆላንድና የእንግሊዝ ኩባንያዎች ሲሆኑ ሁለቱ በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ከወቅታዊ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ጉዳት ከደረሰባቸው የአበባ እርሻዎች በተጨማሪ ከሰባት በላይ የሚሆኑ ሌሎች የአበባ እርሻዎች ያሉ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ እነዚህ እርሻዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ሪፖርት እንዳልተደረገ ታውቋል፡፡ ሆኖም በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር እነዚህንም ያውካል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

በባህር ዳር ዙሪያ ከሚገኙ የአበባ እርሻዎች መካከል በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በብቸኝነት እየተመረተ የነበረ ብሉ ቤሪ የተባለ የምርት ዓይነትን ያመርት የነበረ እርሻ ጭምር ጉዳት እንደደረሰበት ታውቋል፡፡

ይህ የምርት ዓይነት በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ የሚባል ዋጋ የሚያወጣና የአገሪቱን የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ ከማሳደግ አንፃር በተለየ ሁኔታ የሚታይ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡  

ከማኅበሩ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ በባህር ዳር ዙሪያ ያሉ እርሻዎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ፣ ይህንን ጉዳት ሊያካክስ የሚችል ድጋፍ የሚያስፈልግ ስለመሆኑ ከማኅረቡ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ በተለይ ጉዳት የደረሰባቸውና የተሰረቁ ንብረቶች በአብዛኛው ከውጭ የገቡ ከመሆኑ አንፃር እነሱን መልሶ ለመተካት እንኳን ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጀምሮ ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ በቀላሉ ወደ ሥራ ለመግባት የሚፈትናቸው ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በእርሻዎቹ ላይ የተፈጠረው ውድመት ሳቢያ የብዙዎቹ ኩባንያዎች ሠራተኞች ደመወዝ ለማግኘት የሚቸገሩ በመሆኑ፣ ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት የሠራተኞችን ህልውና መታደግ ይሆናል ተብሏል፡፡ በእርሻዎቹ ላይ ጥቃት ያደረሰውን አካል ለማወቅ ካለመቻሉም በላይ፣ ቀሪ ንብረቶችን ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ ሥጋት መፈጠሩ ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ሰፊ የልማት ይዞታ የሚገኘው በአማራ ክልል እንደሆነ ታውቋል፡፡

አሁንም አበባና ተመሳሳይ ምርቶችን ለማምረት ምቹ የመሬት ይዞታና የአየር ንብረት ሁኔታ ያለው በአማራ ክልል በመሆኑ በክልሉ በተለይ በባህር ዳር ዙሪያ የአበባ እርሻ ለማስፋፋት ተመራጭ ነው፡፡ አሁን ጉዳት የደረሰባቸው አበባ እርሻ መካከል ብዙዎቹ አልሚዎች የምርት ቦታቸውን እያሰፋ ተጨማሪ ምርት ለማምረት ዝግጅት በማድረግ ላይ የነበሩ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ምርት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሲሆን፣ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢው ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች