Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ ዓመትን በተስፋና በጥንካሬ የጀመረ ካሰበበት መድረሱ አይቀርም…›› ይባል ነበር ድሮ፣ ድሮን አትናቁ፡፡ የድሮን ነገር ሲነሳ ሌላ ነገር ውስጥ እንዳንገባ አደራ፡፡ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ ልንጓዝ ነው። ጎዳናው ፖለቲካን አካቶ ከፋሽን ጀምሮ ብዙ ነገር ይባልበታል። ‹‹ታያታለህ እንዴት እንደለበሰች? አሁን ቢጫ ኮት በቀይ ሱሪ ይደረጋል?›› ይላል ከተሠለፍነው መሀል አንዱ። በሩቅ አውቶሞቢሏን በንቃት እየዘወረች ውበት የለቀቀባትን ቀዘባ እየጠቆመ። ‹‹ኮቱንስ ይሁን፣ ሱሪዋን እንዴት ከዚህ ሆነህ ልታየው ቻልክ?‹‹ ይላል ያኛው። ‹‹ቀላል ነው፣ እንደ እኔ ተደራጅተህ የቦንዳ ሱቅ ስትከፍት ይገልጽልሃል…›› ይላል ያኛው። ‹‹ለቦንዳ ንግድም ተደራጁ ተባለ እንዴ?›› ቦርሳ ያንጠለጠለ ጎልማሳ ጠየቀ። ‹‹አቤት? ማናቸው እነሱ?›› ዓይኑ ከዚያች ባለቢጫ ኮት ወጣት አልነቀል ያለው ጠየቀ። ጎልማሳው በኮባ እንደተጠቀለለ ያልበሰለ ሊጥ መልሱ በጥያቄ ተሸፍኖ ተመለሰለት መሰል ዝም አለ። ‹‹ሰው በቃ በተውላጠ ስም እነሱ እኛ እያለ ማነካካቱን ‘ሙድ’ አደረገው አይደል?›› ይለኛል ከኋላ የተሠለፈ ከሲታ ወጣት። ነገር ማቀሳሰር ይሉታል!

‹‹ቆይ ለምን አንደኛውን መሀል ገብቶ አስቁሟት ‘ሊፍት’ አይጠይቃትም?›› ይላል አንዱ። ያ የቅርብ ሩቅ አዳሪው ሰምቶት ኖሮ፣ ‹‹ማን በሠራው መንገድ ነው መሀል ገብቶ የሚገጨው?›› ብሎ ዞረበት። ከጀርባ የቆመው ደፋር፣ ‹‹አየህ? ወይ ማጥመድ አይችሉ ወይ መጥለፍ አይሳካላቸው፣ ዝም ብለው ዳር ቆመው ቄንጥ ሲያወጡ ሰው ይመስላሉ…›› ብሎ ጎሸመኝ። “እኮ እነ ማን?” ብሎ ያኛው ሲያፈጥ፣ ‹‹ስለማን ነው የምናወራው? ስለእኛና ስለእነሱ ነዋ…›› ብሎት ደረቱን ነፋ። ባለቦርሳው ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹አቤት… አቤት… እንዴት ተናግረህ ሞተሃል እባክህ። እኛና እነሱ እየተባባልን መሰለን ሰላም አጥተን ግራ የተጋባነው…›› አለ። በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ሰሞን ሰላም ትልቁ ጥያቄ እንደሆነ ልብ አላችሁ? እንዲያው እኮ!

አሁን ታክሲ ተሳፍረናል። ያ ከጀርባ ተሠልፎ ጆሮአችን ሥር ሲተነፍስብን የነበረው ደፋር መሀል መቀመጫ ላይ ከአንዲት ወይዘሮ ጋር ተሰይሟል። ወይዘሮዋ ደርባባነታቸው ልዩ፣ አለባበሳቸው ደግሞ ማራኪ ጥንቅቅ ያሉ ሴት ናቸው። ‹‹እማማ እባክዎ ይኼን ግርማ ሰው ሁሉ እንዲያየው ይዘውት እንዳይወርዱ አደራ…›› ይላል ወጣቱ። ‹‹ምን ላድርገው ታዲያ? ልስቀልልህ?›› ይሉታል እያሾፉ፣ ተጫዋች ናቸው። ‹‹የለም ይፍቀዱልኝና ፎቶ ላንሳው…›› ዓይን አውጣው ፊት ሲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ነው። ‹‹እንዴ? እናንተ ልጆች የፎቶ አብዮት ነው የያዛችሁት የዕድገት? ጊዜው ሥሩብኝ ይላል እናንተ ደግሞ ቴክኖሎጂ አገዘን ብላችሁ ‹ቀጭ! ቋ!› ያለችውን ሁሉ እንደ ፓፓራዚ በፎቶ ምች ስታሳድዱ መዋል ሆኗል ሥራችሁ። ምን ይሻላችኋል?›› ከናፍራቸውን አጣመው ጥርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ ያዩታል። ‹‹ምን ይሻለናል እማማ። እንደሚሰሙት ስንትና ስንት ዓመት ተምሮ ስፔሻሊስት የሆነ ዶክተር ሳይቀር በችጋር የሚኖርባት አገር ውስጥ እኮ ነው ያለነው…›› አላቸው። ሐኪም ተቸገረ ሲባል ማን ያምናል አሁን!

‹‹አይ አንተ ልጅ አሁን ገና ቁምነገር አመጣህ፡፡ በቀደም ዕለት ድንገት የትዊተር ገጼ ላይ የአንድ ወጣት ሐኪም ብሶት ገጭ አለ፡፡ ወጣቱ ሐኪም ስሜን ደብቁልኝ ብሎ በሐኪሞች ገጽ ላይ ያወጣው ብሶት ነው ልቤን የነካው፡፡ ወጣቱ ሐኪም በሚያገኛት 11 ሺሕ ብር የቤት ኪራይ መክፈል እንዳልቻለና ኑሮ እንዳዳገተው የገለጸበት መንገድ አስለቀሰኝ፡፡ ልጆች እባካችሁ ፈጣሪ በመራችሁ መንገድ ተምራችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ በትርፍ ሰዓት ጭምር እየሠራችሁ ሕይወታችሁን ቀይሩ፡፡ እናንተ ለራሳችሁ ካልበረታችሁ በስተቀር ማንም ሕይወታችሁን አይቀይርም፡፡ የሄደውና የመጣው ሁሉ ሊጠቀምባችሁ እንጂ ምንም ቁምነገር ስለማይፈይድላችሁ ራሳችሁ ለራሳችሁ ለመድረስ ታገሉ…›› እያሉ ምሁራዊ ትንታኔ አቅርበውልን፣ ‹‹ማነህ ወጣቱ በል አሪፍ የፕሮፋይል ፎቶ አንሳኝና በዋትስአፕ ወይም በቴሌግራም ትልክልኛለህ፡፡ አብረህም የባንክ አካውንት ቁጥርህን አያይዘህ እኔም ተገቢውን ክፍያ እፈጽማለሁ…›› ብለው ፈገግ ሲሉ አስደመሙን፡፡ ለመሆኑ ይኼ ታክሲ የሚሉት ጉድ ልክ እንደ ዓለማችን ሁሉንም ሰው ነው እንዴ አሰባጥሮ ይዞ የሚጓዘው? አጃኢብ ነው ይሉ ነበር የድሬ ልጆች!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት ሴቶች ሲያወሩ ቀሪዎቻችን አዳማጮች ነን። ‹‹ገና ለገና ብራንድ ቱሶን ተገዛልኝ ብላ እንዲህ ፀባዩዋ ይቀየር?›› ትላለች ወደ መስኮቱ ጥግ የተቀመጠችው። ‹‹አትገርምሽም? ብርቅ ነው እንዴ ዘመናዊ መኪና መንዳት? እነ እንቶኒት እኮ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ነው የያዙት፡፡ እሷ ዘመን አፈራሽ ሀብታም ተብዬ አሁን ገና ጠብሳ እንዲህ የሆነች፣ ዋናዎቹን ቱባ ቱጃሮች ላይ ብትወድቅ ምን ልትሆን ነበር…›› ትላለች ጫፍ ላይ የተቀመጠችው። ‹‹ውይ ሰው… ሰው ግን…››  ስታማትብ ቆይታ፣ ‹‹ሳገኝ ከምከዳ አምላኬ ሆይ መጀመርያውኑም አትስጠኝ…›› ብላ አጉል ቃል ገባች። ይኼን ጊዜ ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ምንድነው የምትለው ልጅቷ? በቃ ጓደኛቸው ሀብት አግኝታ ወይም ከሀብታም ተጣብሳ መደቧ ቢቀየር ምን ይደንቃል አይደለም እንዴ?›› ይለኛል። ጎበዝ እንኳን ከንፋስ አመጣሽ ሀብታም ተጠግተን አይደለም፣ ራሳችን ባፈራነው እንደ ተራራ የተቆለለ ንብረትና ገንዘብ እንዲህ ወዳጅ ላይ ትከሻ ማሳየት ተገቢ ነው? አይደለም ነው መልሱ!

‹‹እንዲያው ለመሆኑ ሥልጣንና ሀብት በአቋራጭ የያዙ ሰዎች ከመቼ ወዲህ ነው በአፍቅሮተ ነዋይ ታውረው የአገር ፍቅርና ሰብዓዊነት ከውስጣቸው የነጠፈው?›› ብለው ወይዘሮዋ ድንገተኛ ጥያቄ ሲያቀርቡ ወያላው ጥልቅ ብሎ፣ ‹‹ማዘር ችግሩ የሁላችንም መሰለኝ፡፡ ድንገት ከች ብለው የምንወደውንና የምንፈልገውን እያነበነቡልን ሲጎዘጎዙ፣ እንዴትና ለምን ብለን ጥያቄ የማቅረብ ልምድ ስለሌለንና በመንጋ ስለምንነዳ መጫወቻ ሆነን ቀረን…›› ሲላቸው፣ ‹‹አንተ እዚያው ራስህን ቻል፡፡ ለምሳሌ እኔ የፈለገ ነገር ቢባል መጀመሪያ የማነሳው ጥያቄ ነው፡፡ ያልገባኝ ወይም ያጠራጠረኝ ነገር ሲኖር ጥያቄ ማንሳት ልማዴ ነው፡፡ በዚህ ልማዴ ግን ብዙ ሰዎች ደስተኛ ስላልሆኑ ክርክር ይገጥመኛል፡፡ ባለሥልጣን ሲያዩ ቁጭ ብድግ የሚሉ፣ ሀብታም ሲመጣ እንደ ምንጣፍ የሚነጠፉ ሞልተው ነው የሰው አምላኪ ሆነን የቀረነው ብትል ይሻልሃል…›› ብሎ አንድ ወጣት ቱግ ሲል አስደነገጠን፡፡ ወይዘሮዋ እየሳቁ፣ ‹‹ልጄ አንተ መልካሙን ጎዳና ተያይዘኸዋል በርታ፡፡ አንተ ወያላውም ጥሩ ምልከታ ስላሳየኸን ተበረታታ…›› ብለው ገላገሉን፡፡ መልካም ተናጋሪ አይጥፋ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋ በራሳቸው ሐሳብ እየተብሰለሰሉ፣ ፎቶግራፍ ያነሳቸው ወጣት ድምፁን አጥፍቶ፣ አንድ ጎልማሳ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ የሚታዘበውን እያወራ፣ እነዚያ ሴት ጓደኛማቾች ወደፊት መግዛት ስለሚፈልጉት የመኪና ሞዴል እየተወያዩ፣ ከአጠገባቸው ደግሞ በዝምታ የተዋጡት ባልና ሚስት እንዳቀረቀሩ መጨረሻችን ቀረበ። ጋቢና ከተቀመጡት አንዱ የአውሮፓ ቡድን ደጋፊ ነኝ እያለ አጠገቡ ከተቀመጠው ሌላ ደጋፊ ጋር ደርቢ ገጥሟል። ‹‹እናንተ ምን አለባችሁ? እኛ እዚህ በጠራራ ፀሐይ በረባ ባረባው እንጋጣለን፣ እናንተ ህልውናችሁን እንኳ ዕውቅና ለማይቸሩ ተራጋጮች ታሸበሽባላችሁ…›› አሉ ወይዘሮዋ። ‹‹ምን እናድርግ? ‘ለራሳችሁ አልቅሱ’ ተብሎ ተጽፏል…›› ይላቸዋል ከጎናቸው የተቀመጠው። ‹‹ታዲያ እዚህ ማርገጃ መሬት ጠፋ? ምን ሩቅ ያስኬዳችኋል?›› ወይዘሮዋ በአነጋገሩ ከፍቷቸዋል። ‹‹ስለመሬት ነክ ጉዳይ ባይወራ ደስ ይለኛል…›› ይለኛል ጎልማሳው። ‹‹ዳይፐር’ አልቆበታል እኮ ማሙሽ…›› ትላለች ደግሞ ከኋላ ሚስት ለባሏ። ባል ደግሞ፣ ‹‹ምናለበት ብትገዥለት? ከትናንት ወዲያ የሰጠሁሽን ገንዘብ ምን አደረግሽው?›› ብሎ ያፈጣል። ‹‹ይኼ መፋጠጥ ከቤት ከጀመረ ደግ አይደለም…›› የሚለው መሀል ወንበር የተቀመጠው ነው፡፡ ድንቅ ነው!

 ‹‹አይደብረውም እንዴ ሰውዬው? በሰው መሀል ‘ሼም’ ያስይዛታል እንዴ?›› ይባባላሉ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙት ወጣት ሴቶች። የባልና ሚስቱን ንግግር ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠው ሲያዳምቅ፣ ‹‹ኳስ እኮ ነጋ ጠባ የሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ የለው፣ ፖለቲካ ተኮር ዘገባ አያውቅ፣ የራሱን ድምፅ ለማሰማት ሲል የሰው ድምፅ አያፍን፣ በቃ ምን ልበልዎ ኳስ ንፁህ መዝናኛ ነው። ደግሞ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ልዩ ነው…›› ብሎ ሳይጨርስ ወይዘሮዋ፣ ‹‹የአገርህስ?›› ብለው ዞሩበት። ይኼኔ ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን በረገደው። ‹‹የአገርህስ ነው እኮ የምልህ?›› ወይዘሮዋ አጥብቀው ይጠይቃሉ። ‹‹ነገርኩዎ እኮ…›› ወጣቱ ተወዛገበ። ተሳፋሪዎች አንድ በአንድ መውረድ ጀመሩ። ኑሮው ፖለቲካ፣ መዝናኛው ፖለቲካ፣ ማዘኛው ፖለቲካ፣ ኳሱ ፖለቲካ በሆነባት ምድር እግር እርሙን በልቶ መርገጡን ቀጠለ። ችግሩን መዘርዘር ቢቀጥል ማቆሚያ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ገና አዲስ ዓመት ከመግባቱ የአምናው ተደምሮ ስንቱ ችግር ተነግሮ ይዘለቃል? አምናና ዘንድሮ እንበል እንዴ? መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት