Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

ቀን:

በያሲን ባህሩ

አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ራስ ወዳድነት፣ ለእኔ ለእኔ ማለት፣ አለመተሳሳብና ጥላቻን የሚፀየፍም ዕሴት ነው፡፡ ከምንገኝበት ጊዜ አንፃር ደግሞ ከጉልበትና ከኃይል ይልቅ፣ የሐሳብ ትግልና የሰላም መድረክን እንደሚሻ የሚስተው የለም፡፡ ለዚህም ነገሮችን በሆደ ሰፊነት እያስተዋሉ የታሪክ ስህተትንም ሆነ ጥንካሬን ለአሁን መማሪያ እንጂ፣  ሒሳብ ማወራረጃ ሳያደርጉ በጀግንነት መቆም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም ጠቅልዬ ልብላ ወይም ልትፋው የሚል ሥሌት ውስጥ ገብቶ ከመዋተት ይልቅ፣ የሰጥቶ መቀበል መርህን መከተል የፀና አገር ለማቆም ያግዛል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት አገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጣ ውረድ፣ ግጭትና አለመግባባትን ስታስተናግድ ነበር የከረመችው፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው የንፁኃንና አቅመ ደካሞች ሞትና መንገላታት፣ የሕዝብና የግለሰቦች ሀብት ውድመት፣ የማኅበረሰብ የሥነ ልቦና መቃወስና ተስፋ መቁረጥ፣ በሒደትም ከፍተኛ የማንነት ተኮር ግጭትና ጦርነት ወደ ማስተናገድ እየገባች መሆኗ ብዚዎችን እያሳዘነ ይገኛል፣ ኧረ ያስጨንቃልም፡፡

ትናንት በትግራይ አሁን ደግሞ በአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ልዩ ልዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ጦርነትና ግጭቶች እያደረሱ ያሉት፣ የሰከነ የፖለቲካ ምክክርና የሰላም መፍትሔ ድርቅ በመንሰራፋቱ ነው፡፡ ውረድ እንውረድ መባባሉ ተባብሶ፣ ተው ባይ ጠፍቶ ተያያዞ ለመስጠም እንደሚደረግ ጥድፊያም እየታየ ነው፡፡ ቢያድለን ግን መንግሥትም ሆነ ተፋላሚዎች ቆም ብለው፣ የጋራ ኪሳራን ተገንዝበው ችግራችንን እንዴት እንፍታ ማለት ነበር የሚበጀው፡፡ ከቂም በቀልና ጥላቻ የሚያተርፈውም እሱ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አውዳሚ የነበረውን ጦርነት  በማቆም የትግራይ ኃይሎችና መንግሥት ወደ ድርድር ሲመጡ እፎይ ያላለ አልነበረም፡፡ ዕርቅና ሰላምን በደፈናው የሚጠላው ይኖራል ብሎ የሚያስብም የለም፡፡ ምክንያቱም ከግጭት፣ ከጦርነትም ሆነ ከትርምስ ጥቂት ስግብግቦች እንጂ አገር ልታተርፍ አትችልምና፡፡ የሰላሙ አየር በወጉ እንኳን በአገራችን ሰማይ ሥር ሳይነፍስ ግን ሌላ ጦርነት ሊቀሰቀስ የቻለው የሰጥቶ መቀበልና የግልጽነት መርህ በመሸርሸሩ፣ የዴሞክራሲና የሐሳብ ገበያ በመጨንገፉ ብሎም በግብታዊ ውሳኔዎች ጋጋታ ነው የሚሉ ተቺዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ማንኛውም ሕጋዊና የሚበጅ ሐሳብ በሁሉም ወገኖች በኩል ቅቡልነት ሊያገኝ የሚችለው መተማመን ሲኖር ነው፡፡ መሠረታዊ ቀውሶችና የአገራዊ ጉዞው እንቅፋቶች እንዲቀረፉ አስቦ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ የሚቻለውም የመነጋገር ባህል ሲዳብር ነው፡፡

ለአብነት ያህል በሁሉም ኃይሎች በኩል ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመደበኛው መከላከያ ኃይልና ፖሊስ በስተቀር ሌላ የተደራጀ ሕገወጥ የታጠቀ ኃይል አለመኖሩ መረጋጋጥ እንዳለበት ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ምናልባት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ይኑሩ ቢባል እንኳን በክልል መንግሥታትና በማዕከላዊው የፀጥታ ኃይል ሥር፣ የአካባቢ ደኅንነት ለማስጠበቅ ብቻ ታጥቆና ተደራጅቶ ሊሠራ ይገባል መባሉም አሳማኝ ሐሳብ ነው፡፡ ችግሩ ያለው ግን አገራችን ከዳር እስከ ዳር በማንነት ተኮር ፌደራሊዝም መተዳደሯና በርካታ የወሰን፣ የማንነት፣ የመሬትና የጥቅም ግጭቶችና ፍጥጫዎች የተከማመሩበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የዜጎች በመላው አገሪቱ ተንቀሳቅሰው የመሥራትና የመኖር መብት ሊጠበቅ አልቻለም፡፡ እንዲያውም በየቦታው በመንጋ ፍርድ ውጣልኝና አትድረስብኝ የሚል ትውልድ አገራዊ አንድነቱን እየተገዳደረ ነው የቆየው፡፡ ከዚህም አልፎ ለጦርነቱ መነሻ የነበሩ ምክንያቶች ሳይቀሩ እንዴትና በምን መንገድ እንደተፈቱ እንኳን ሳይገለጽ፣ በደመ ነፍስ ብድግ ብሎ ትጥቅህን ፍታ መባሉ ሥጋት ያሳደረባቸው ወገኖች (እንደ አማራ ክልል ያሉቱ) እንዲበራከቱ አድርጓል፣ ነገሩን ወደ ግጭትም ገፍቶታል፡፡

እንደሚታወቀው አሁን ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት ከሞላ ጎደል አሳታፊና ሰላማዊ በተባለ ምርጫ ሥልጣን የጨበጠ (አንዳንድ ትግራይን የመሰሉ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም) እንደመሆኑ፣ ለሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ኃላፊነት የሚወስድበትና ተጠያቂነት ያለበት መሆኑ ቅቡልነት ሊያገኝ ይገባ ነበር፡፡ የጎደለውን ሞልቶ ይህንኑ መተግበርም ነው ለሕዝቡ ዋስትና የሚሰጠው፡፡ በተግባር የሚታየው እንቅስቃሴና በከፍተኛ ማዕበል የሚመሰለው የማኅበራዊ ድረ ገጽ ፕሮፓጋንዳ እንደሚያስረዳው ግን፣ ሕዝብና መንግሥት ተማምነው እየተጓዙ አለመሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ ከፍተኛ ሥራ የሚፈልግ ምክክርና መተማመን ሊፈጠር የሚገባውም በዚሁ መነሻ ነው፡፡

በሌላ በኩል በአገራችን የማንነት፣ የወሰን፣ የፖለቲካና የአስተዳደር አከላለል መዘበራረቅና ንትርክን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከወዲሁ በድፍረትና በግልጽነት መነጋገር ካልተቻለም፣ ጦርነትና ግጭት በምንም መንገድ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ይህ አጀንዳ በቀላል የሚታይ ባይሆንም በተለይ የትግራይ ኃይል ከአማራና ከአፋር ክልሎች፣ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ያፋጣጠው አንዱ ምክንያት እንደመሆኑ በሰላም ድርድሩ መነሳቱ አይቀሬ ነበር፡፡ ምን እንደተባለና እንዴትና መቼ፣ መፍትሔስ ሊሰጠው እንዴት ታሰበ፣ ተሞክሮው በሌላ አካባቢ ሊስፋፋ የሚችለውስ እንዴት ነው ብሎ መነጋገር በተገባ ነበር፡፡ ግን አልሆነምና ሌላ ትርምስ ነው የጋበዝው፡፡

አጀንዳው ሰላማዊ በነበረው ደቡብ ክልል ውስጥ ሳይቀር የሰላም ማጣት ምክንያት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አሁን በረድ ያለ ቢመስልም በአፋርና በሶማሌያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች፣ በኦሮሚያና በርከት ባሉ አካባቢዎች፣ ወዘተ ጉዳይ የጋራ መግባባት የተያዘበት ስምምነት አልተጨበጠም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ፈጠን ብሎ የአገራዊ ምክክርን ኮሚሽኑን ወደ ሥራ አስገብቶ የሕዝብ ውሳኔ ከማዳመጥ ይልቅ፣ በራሱ ዕቅድ አንዳንድ ውሳኔዎችን እያሳለፈ (ለምሳሌ የሸገር ከተማ አስተዳዳር ምሥረታ) በአገር ላይ ወደ መጫን ነው የገባው፡፡ ይህም መታረም ያለበትና የተቃርኖ መንስዔ የመሆን ዕድል ያለው አካሄድ ነው፡፡

እነዚህና መሰል መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በማስተካከልና በመግባባት ጎዶሎዋቸውን ለመሙላትና የአገረ መንግሥት ግንባታውን ለማጠናከር ደግሞ፣ ከሁሉ በፊት ሕገ መንግሥቱን መፈተሽና ሁሉን አቀፍ ምክክር መጀመር አስፈላጊ ነበር፡፡ አሁን ከምንገኝበት ፈተናና አጣዳፊ ሁኔታ አንፃር ግጭት የሚያስቆሙ ተግባራትን ማስቀደም ብልህነት ነበር፡፡ ግን እንዲነካ ባልተፈለገ ተመሳሳይ ዕሳቤና የዴሞክራሲ ፍርኃት ውስጥ ሆኖ ለውጥ ለማምጣት ሲሞከር ነው የታየው፡፡ አሁንም ፈጥኖ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በነፃና በገለልተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲተገበር ካልተደረገ መፍትሔው መራቁ አይቀርም፡፡

በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ባሉ ሁሉም ወገኖች በኩል መቀጠል ያለበት ፀብና ግጭት ሳይሆን፣ ምክክርና መቀራረብ ብሎም በሰጥቶ መቀበል መርህ መተማመንን መፍጠር ሊሆን የግድ ነው፡፡ መጠናከር ያለበትም በልዩነት መነታረክና በታሪክ መወናበድ ሳይሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን በማጠናከር አብሮነትና ሁለንተናዊ ትብብርን ማሳደግ፣ እንዲሁም በፍትሐዊነት አገራችንን መገንባት ላይ ማተኮር ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ በአጭር ጊዜ ከኖርንበት ፅንፈኝነት፣ የጥላቻ ትርክትና የእልህ ፖለቲካ ተላቅቆ ወደ ክብ ጠረጴዛ መሰባሰብ ነው፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎንና ግልጽነትን ይበልጥ ማሳደግ፡፡

በአዲስ ትውልድና በተቀየረ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ትናንት በነበረ ትርክት ላይ ተመሥርቶ የተዘራን የተሳሳተ የጥላቻ ፖለቲካ እያጋነኑና እያመነዥኩ መኖር አይቻልም፡፡ የተሠራጨውን ሕዝቦች አብረው የማይኖሩበትን ሴራ ማምከን ያስፈልጋል፡፡ ለዓመታት የተዘራውን ቂም በቀል ዘር ከሥሩ ለመንቀልም ከፖለቲከኞችና ምሁራን ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም የሚጠበቁ ተግባራት አሉ፡፡ እንደ የእምነት፣ የትምህርትና የሚዲያ ተቋማት ያሉ አካላትም ከቀውስና ከፀብ ጫሪ ድርጊቶች በመታቀብ ለአገር ግንባታ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ አለመተማመንና ጫፍ ረገጥነትን ማስወገድ፣ የፖለቲካ አስተሳሳብን በሕዝቦች ላይ በግድ ከመጫን መታቀብ፣ እንዲሁም ገለልተኛና የወል ተቋማትን ማጠናከር ይኖርብናል፡፡

በዚያው ልክ  እንደ አገር ከተንሰራፋው የእኔ እበልጥ፣ የእኔ ይበልጥ ፉክክርና የእኛና የእነሱ ጭቅጭቅም መላቀቅ ይኖርብናል። ትናንት በሴራ ሕዝቦችን ለማቃቃር የተዘጋጀ የወሰንና የማንነት ወይም ጥላሸት የተቀባን ታሪክ ተብዬ ትርክት ሁሉ ሳያላምጡ ውጦ፣ ወይም የተፈጸመ በደልንም ክዶ በጋራ የሚቆም አገር የለም፡፡ ትናንትን ብቻ ሳይሆን አሁንም ቢሆን ድክመትና ጥንካሬያቸውን በሕግና በሥርዓት ከማስተካከል ይልቅ፣ በፀብና በግጭት ለመፍታት መሞከርም እያስከፈለ ያለውን ዋጋ ብቻ ሳይሆን፣ ነገን እንደሚያጨልም ተደማምጦ መረዳት ይገባል።

ስለሆነም በየትም አገር ሁሉም ጉዳዮች ከአገርና ከሕግ በታች እንደ መሆናቸው እውነታውን እየተጋፈጡ፣ የሕዝቡን ውሳኔ እያዳመጡ በመነጋገር ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገር ነው የሚጠበቅብን። ፖለቲከኛውም ሆነ ሕዝቡ ምክንያታዊነቱንና መደጋገፉን ማዳበር ይኖርበታል፡፡ አሁን እየታየ እዳለው ነገሮችን በኃይል ለመፍታት መሞከር ያውም ግጭቶችን የሕዝብና ሕዝብ ጦርነቶች በሚያስመስል ቅስቀሳ በማጀብ ግፋ በለው ማለት ግን አገር እንደ ማፍረስ ነው የሚቆጠረው፡፡ በአፋጣኝ መቆምም አለበት፡፡ በትናንቱ ስሌት እየተፎካከሩ፣ በውስብስብና አወዛጋቢ የታሪክ ትርክት እየተጠማመዱ፣ እንዲሁም በእምነት፣ በብሔር፣ በታሪክና በቋንቋ ለዘመናት የተሰባጠረ ብዝኃነትን ለአደጋ በሚያጋልጥ ጥላቻ እየተራኮቱ ብሔራዊ ዕርቅንም ሆነ መግባባትን ዕውን ማድረግ ደግሞ ፈፅሞ ሊታሰብ አይችልም፡፡ ዴሞክራሲና የሰላም አማራጮችም መደብዘዛቸው አይቀሬ ነው፡፡ እናም ወደ ኖረው የኃይልና የመበላላት የድንጋይ ዘመን መመለስ ይከተላል፡፡ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ይኸው እንዳይሆንም ያሠጋል፡፡

በምንገኝበት ዓለም እንኳንስ የአንድ አገር ሕዝቦች ይቅሩና የአኅጉርና የዓለም ሕዝቦችም እየተነጋገሩና፣ ሳይስማሙ ጭምር እየተስማሙ አብረው ለመኖርና በጋራ ለመጠቃቀምም ረዥም ርቀቶችን ይጓዛሉ፡፡ ችግሮችን በኃይልና በግጭት ለመፍታት ከመሽቀዳደምም በፊትም በሰላምና በውይይት የመፍታት ባህላቸው የዳበረ አገሮች ቁጥራቸው ትንሽ አይደሉም፡፡ እኛ ግን የአንድ ምድር ሰዎች ሆነን ስናበቃ ከአንዴ ሁለት ሦስት ጊዜ እየተዳማንና እየተገዳደልን መቀጠላቸን በምንም መለኪያ ትርፋማ ሊያደርገን አይችልም፡፡

በእስካሁኑ ሁኔታ በእኛ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትግል ውስጥ የመፈራረጅ ክፍተቱ የጎላው፣ ገዥ መደቦችንና የሥርዓቱ ቀንደኛ መሪዎችን ከጭቁን ዜጎች ጋር በመቀላቀል ለማየት በመሞከሩ ነው የሚሉ ወገኖች መደመጥ አለባቸው፡፡ የቀድሞ ጨቋኝና ኋላቀር የነበሩ ሥርዓቶች መሪዎች በታሪክ አጋጣሚ አማርኛ ተናጋሪ ስለነበሩ፣ ከአማራ ጭቁን ሕዝብ ጋር የሚያስተሳስራቸው ክር እንደሌለ የጋራ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ ሰዎችን በማንነታቸው እየፈረጁ ማንገላታትና በጠላትነት መቁጠር የሚቆመውም አስተሳሰቡ ሲታረም ነው፡፡

በተመሳሳይ ሕወሓትን ከትግራይ ሕዝብ፣ ብልፅግናን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር እያደባለቁ በደጉ ተግባር ሳያመሠግኑ በተሠራው የአስተዳደር ጥፋት ማጥላላትና መኮነንም ፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡ የትኛውም ገዥ መደብ በሕዝብ ስም እየነገደ ይጠቀም እንደሆን እንጂ፣ ለወጣበት ማኅበረሰብ የተለየ ትርፍ እንዳላስገኛ በእኛ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም የታወቀ ዕውነት ነው፡፡

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጭብጥ በጀብደኝነት ራሱን በቀድሞ ሥርዓቶች ስም እየጠራ ‹‹ነፍጠኛ ነኝ››፣ ‹‹ትምክህተኛ ነኝ››፣ ወይም ‹‹ወያኔ ነኝ›› የሚለውም ሆነ፣ በመላው ሕዝብ ስም ሥልጣን ላይ ተቆናጦ ለአንድ ብሔር እንደቆመ በማስመሰል ‹‹ተረኛ ነኝ›› እያሉ መኮፈስ ሊኮነን የሚገባው ተግባር ነው፡፡ አብሮነትን እንደሚንድ ተግባር ሊቆጠርም ይገባል፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱም ሆነ መሪው ፓርቲ በታሪክ አጋጣሚ የአገራችንን ዕጣ ፋንታ የተረከበና ዘመኑን የሚዋጅ ኃይል እንጂ፣ ሕዝብን ከሕዝብ እያናቆረ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የሚኳትን ከንቱ አለመሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ካልሆነ ግን የምናዋልደው ሶሪያና የመንን የመሰለች አገር ነው፣ ይታሰብበት፡፡

በተለይ አማራና  የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዩን (ቀላል ግምት የማይሰጠው ሕዝብ ከእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተዋልዷል፣ ተዋህዷልና) ወገን የቀድሞ አገዛዞች መሣሪያና አስተሳሰብ አራማጅ አድርጎ የመሣሉ አካሄድ የጠላትና የወዳጅ ፍረጃ ፈጠራ ቅራኔ እያሰደገ መምጣቱ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ‹‹ለዘመናት ተረስተን ኖርን›› የሚለው የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍልና ‹‹የብሔር ጭቆናን›› የፖለቲካዊ ትግሉ ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ የዘለቀው ልሂቅ በየፊናው ሲጻፍለት የነበረውን ይህ ዓይነቱ የተዛባ ትርክት ሲያመነዥክ ቢቆይም፣ ወደ ቀልቡ ተመልሶ ነገሮችን በሚዛን መመልከትና አብሮ የመኖር እሴት ለመገንባት መነሳትም ይኖርበታል፡፡

በመሠረቱ እንኳንስ የትናንት የዛሬውም የትኛውም ጉዳይ ከአገር አንድነትና ከሕዝቦች ጥቅም አኳያ ብቻ እየተመዘነ መቅረቡ ነው የሚበጀው፡፡ የማንነትና የእምነት ተከታይ ውዝግቡ ከዕለት ወደ ዕለት እየተካረረ መምጣቱም የሚገራበት ሥርዓትና አስተሳሰብ መዳበር አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያለውና በየዋና ዋና ከተማው የሚኖረውን ወገን የት እናሳርፈው ብሎ መጨነቅም ግድ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ከከረመው ዕይታ ወጣ ብሎ አዲስ ፈለግና አታያይ ዕውን ማድረግን ይፈልጋል፡፡ ጦርነትና ትርምስን ሊያስቀር የሚችለውም ይህ ዓይነቱ የሰጥቶ መቀበልና መተሳሰብ ሰላማዊ የትግል መድረክ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ውጣልኝና በለው በለው መፍትሔ አይሆንም፡፡

እንደ አገር ከእነ ጉድለቱም ቢሆን ባለፉት 33 ዓመታት የተጀመሩትን የአገር ልማትና ተስፋዎች ላለማጨለም ከሰላምና ከመነጋገር ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ መተማመንና መቀራረብ ብቻ ሳይሆን፣ አንዱ በሌላው ጫማ ውስጥ መቆም፣ መተሳሰብና በሰጥቶ መቀበል መንፈስ መደጋገፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ፍትሐዊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ብሎም የነቃ የሕዝብ ተሳትፎ ዕውን ሊሆን የሚችለውም በብሔራዊ መግባባት አገራዊ እሴቶችን መገንባት ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ እናም በፍጥነት ወደ ግጭት ማቆም፣ መደራደርና ብሔራዊ ምክክር መግባትን ማስቀደም የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

ድህነትን ለመቀነስም ሆነ የግል ባለሀብቱን ሰፊ እንቅስቃሴ ለማጠናከርም  እየገደበ የሚገኘውን የመነጣጣል አስተሳብ በየትኛውም መንገድ ለማስተካከል መዘጋጀት  የሚቻለው ሰላም፣ የተሻለ ዴሞክራሲና የተጠናከረ አንድነት ሲገነባ ነው፡፡ በዚህ ረገድ  በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ዓለም ሠርተው፣ ተበድረውና አሰባስበው ሀብት ያመጡ ባለሀብቶች፣ ብሎም የውጭ ኢንቨስተሮች ጭምር በዋና ከተማዋና በአንዳንድ ክልሎች እንደፈለጉ እንዳያለሙና አገር እንዳይቀይሩ የሚያውኩ ያልተጻፉ ሕግጋትና መገፋፋቶች መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ችግርና ድህነቱም ቢሆን ሊበላን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡

በታሪክ አጋጣሚ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተበትነው፣ ተዋልደውና ተጋብተው ኑሯቸውን የመሠረቱ ዜጎችና ወገኖች፣ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች፣ አማኞችና የየእምነቱ መሪዎች፣ ወዘተ ሁሉ በዘርና በእምነታቸው ምክንያት ብቻ የሚጠቁበትና ዋስትና የሚያጡበት አካሄድ የሚገታው ይህንኑ እውነታ የምክክሩ ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ነው፡፡ መንግሥትም ዋነኛው የመፍትሔ አካል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በለውጥ ስም በተለያዩ አካባቢዎች፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በኢትዮጵያዊ ላይ ይህን ሁሉ ግፍና ጥፋት እስከማድረስ የሚያስጨክነውን በሽታ ለይቶ ማከም የሚቻለውም፣ የፖለቲካውን ብልሽት ከማረም በመጀመር ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን  እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...