Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቷ ዝቅተኛ የሆነባት አዲስ አበባ ምን አስባለች?

በአዲስ አበባ ከተማ የቆሻሻ ፍሳሽ ውኃ አወጋገድ ሥርዓቱ የዘመነ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይ ከኢንዱስትሪና ከመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚወጣውን ፍሳሽ በተገቢው መንገድ ሳይወገድ መቅረቱ የሰዎችን ጤና ከማወክም ባለፈ የከተማዋን ውበት ሲያጠፋ ይስተዋላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግም ለቆሻሻ ውኃ ፍሳሽ የተዘረጋው መሠረተ ልማት ዘመናዊነት አለመላበሱ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል፡፡ ይሁን እንጂ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ታደግ መንገሻ የድርጅቱ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ሱፐርቫይዘር ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቷ ዝቅተኛ የሆነባት አዲስ አበባ ምን አስባለች? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚከናወነው የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ምን ይመስላል?

አቶ ታደግ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከነዋሪዎች፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ ከሆቴሎችና ከሌሎች ቦታዎች የሚወጡ ፍሳሾች የሚወገዱበት ሥርዓት የተለያየ ነው፡፡ በተለይም ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣው ፍሳሽ ኬሚካል ያለውና የሚጎዳ ከመሆኑ የተነሳ፣ ፍሳሹን ለማስወገድ በጣም ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ዓይነት ተቋማት የሚወጣው ፍሳሽ ለጤናም ሆነ ለሌሎች ችግር ስለሚያጋልጥ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት በራሳቸው መንገድ ፍሳሹን እንዲያስወግዱ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ሲታይ በአዲስ አበባ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይም በየአካባቢው ሄዶ ፍሳሹን ለማስወገድ የሚደረገው አካሄድ ዘመናዊና የተሻለ የሚባል ባለመሆኑ፣ የከተማዋ መሠረተ ልማትም ሆነ የማኅበረሰቡ ጤና ሊታወክ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለማለፍ የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከየቤቱም ሆነ ከሆቴሎች የሚወጣውን ፍሳሽ በአንድ መስመር ለማስኬድ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡ ተቋሙም ፍሳሽ መሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ማጣራት፣ ማስወገድና መልሶ መጠቀም ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በየቤቱ በመሄድ በትቦ በመሰብሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ትቦም የማይደርስበት አጋጣሚ ሲፈጠር በመኪና በመምጠጥ ማጣሪያ ቦታ ድረስ እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ ማጣሪያ ቦታም ከሄደ በኋላ ደረቅ ቆሻሻን ከፍሳሹ የማጣራት ሒደት ይከናወናል፡፡ ይህም በሚከናወንበት ወቅት ሃይላንድ (ጠርሙስ)፣ ዳይፐርና ሌሎች ቆሻሻዎች ከፍሳሽ ለመለየት ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ በመጨረሻም የፍሳሽ ውኃው ከተጣራ በኋላ ሦስት ዓይነት ግብዓቶች ይፈጠራሉ፡፡ አንደኛ ውኃ፣ ሁለተኛ ዝቃጭ፣ ሦስተኛው ደግሞ ባዮጋዝ ይፈጠራል፡፡ እነዚህም ግብዓቶች ከተለዩ በኋላ ውኃውን ለግብርና መስኖ እንዲውል ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል የተጣራውን ዝቃጭ ለማዳበሪያነት እንዲውል ሲደረግ፣ ባዮጋዙን ደግሞ እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?

አቶ ታደግ፡- ከፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ተደራሽነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለፍሳሽነት አገልግሎት እንዲውሉ የተገነቡ መስመሮች የመደፈን ሁኔታ ስለሚገጥማቸው ሥራችን ላይ ችግር ሆኖብናል፡፡ እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ ዘመናዊ አሠራርን ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት የተዘረጉ የፍሳሽ መስመሮችን ለመክፈት ሲባል በሌሎች የመሠረተ ልማት ግብዓቶች ላይ ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ተቋሙ ዘመናዊ የሆነ አሠራርን በመከተል ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስ የተዘጉ የፍሳሽ ውኃ መስመሮችን እየከፈተ ይገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ በወንዝ ዳርቻ የሠፈሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከውኃ ፍሳሽ ለመታደግ ችግር ሆኖብናል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ የፍሳሽ ተሽከርካሪዎች በብዛት በመግዛት፣ እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመቀናጀት ተደራሽነቱን ለማስፋት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም በወንዝ ዳርቻ የሠፈሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተመቻቸ የመሠረተ ልማት ላይ የሚገኙ ስላልሆኑ፣ የተቋሙ ተሽከርካሪዎች ቦታው ድረስ ሄደው ለመሥራት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለመሆን ተቋሙ የማጣሪያ ጣቢያ ለመገንባት ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች ያለውን የፍሳሽ ውኃ አወጋገድ ሥርዓት እንዴት ይታያል?

አቶ ታደግ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የፍሳሽ ውኃን የሚያጣሩ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የማጣሪያ ጣቢያዎች በቀን ከአምስት ሺሕ ሜትር ኪዩብ በማጣራት በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኘውን የፍሳሽ ውኃ በአግባቡ እንደመራ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህም የማጣሪያ ጣቢያዎች ከፍሳሽ ውኃ ጀምሮ እስከ ደረቅ ቆሻሻ ድረስ በመለየት የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚታየው የፍሳሽ ውኃ በተገቢው መንገድ ከተጣራ በኋላ፣ የተጣራውን ውኃ ለግብርና፣ ለመኪና ማጠቢያ (ላቢያጆ) እና ለኮንትራክሽን አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ የሚገኙ የፍሳሽ ውኃ መስመር ዝርጋታዎች ሲዘጋጉ መስመሩን ለማስከፈት ሲባል የሌሎች ተቋሞች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ይጎዳሉ፡፡ ይህንን ችግር ተቋማችሁ በምን መልኩ ይቀርፈዋል?

አቶ ታደግ፡- እንዳልከው ከዚህ በፊት በከተማዋ የሚገኙ የፍሳሽ ውኃ መስመሮች ሲዘጋጉ የበርታ ተቋማት የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ለአብነት እንኳን ኢትዮ ቴሌኮም፣ የመንገዶች ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የዘረጓቸው የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ጉዳት ያጋጥማቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋሙ በመቅረፍ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ከመጀመርያ ጀምሮ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲገጥመው ለእነዚህ ተቋማት ሪፖርት በማድረግ ጉዳዩን በፍጥነት እንዲፈታ ይደረጋል፡፡   

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ ታደግ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገውን የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘመን ተቋሙ ሰፊ የሆነ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎችም የፍሳሽ ውኃ የሚያጣሩ ጣቢያዎች በመገንባት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍሳሽ ውኃ የተጣሩ ግብዓቶችን ለተለያዩ አገልግሎቶች ለማዋል ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በቀጣይ የከተማ የፍሳሽ ውኃ የማጣራት ተደራሽነት 50 በመቶ እንዲሆን የበኩላችንን ድርሻ የምንወጣ ይሆናል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ የፍሳሽ ውኃ አወጋገድ ሥርዓትን ማዘመን ይቻላል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሠራተኛ ስቀጥር ካለመሠልጠናቸውም በላይ ስንት ይከፈለኛል ብለው ሲጠይቁ እደነግጥ ነበር›› ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው፣ የሶጋ ትሬዲንግና ፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ ሀብ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉት የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሥራ ፈላጊው ብቃት በብዛት አይጣጣምም፡፡ በዚህም ቀጣሪዎች ብቁ የሰው ኃይል አለማግኘታቸውን፣ ሠራተኞችም የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት አጥተው...

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...