ባለፉት 50 ዓመታት ከድህነት የወጡ ብዙ ሕዝቦች አሉ፡፡ ነገር ግን ከድህነት ለመውጣት የተማረና የሚያነብ ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ አዲስ ሐሳብ የሚገኘው ከመጻሕፍት ነውና፡፡
ከድህነት ስለመውጣት ጉዳይ ሳስብ በቅርቡ ደቡብ ኮሪያ ሄጄ ብዙ ትምህርት ወስጄ ተመለስኩ፡፡ አንድ ጊዜ ከባለሥልጣናት ጋር ሄድኩኝ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ብቻዬን ተጋብዤ ሄድኩ፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ወደ ገጠሪቱ ደቡብ ኮሪያ ወስዶኝ ተራራ ላይ ወጣን፡፡ ተራራውን ያካለለውን ደን አሳየኝ፡፡ ይህ የራሴ መሬት ነው አለኝ፡፡ መሬት በደቡብ ኮሪያ የግል ነው እንዴ? አልኩት፡፡ አዎ የግል ነው አለኝ፡፡
ቀጠልኩና እናንተ በ50 ዓመታት ብቻ እንዴት እንደዚህ ሀብታም ሆናችሁ አልኩት፡ እሱም ደቡብ ኮሪያ ከአሣና ወደብ ሌላ ምንም የተፈጥሮ ሀብት የላትም፣ ነገር ግን የተማረና በጣም የሚያነብ ሕዝብ ነበራት፡፡ ዕውቀታችንን ተጠቅመን አሁን ያለችውን የመኪና፣ የመርከብና የኤሌክትሮኒክስ ፋብሪካዎች ፈጠርን፡፡ የተማረና የሚያነብ ሕዝብ ለማደግ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ የማያነብና ያልተማረ ከሆነ ለውጥ በጣም ይከብዳል አለኝ፡፡
ለሕዝብ ክፍት ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች ሁሉ 49 ከመቶ የሕዝብ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ከትርፉ ይቋደሳል፡፡ መንግሥት አይነግድም፣ ንግዱን ያስተዳድራል እንጂ ብሎ በሰፊው አብራራልኝ፡፡
ፖለቲካው እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያን የትምህርት ሁኔታ ስናይ 51 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ መጻፍና ማንበብ አይችልም፡፡ የቀረው 49 ከመቶ መጽሐፍ አያነብም፡፡ ጥቂት ሰዎች ያነባሉ፡፡ አሁን ያለው ትውልድ እንዳለ በሚባል መልኩ ‹‹የመዕልክት አንባቢ›› ሆኗል፡፡ የፌስቡክ እስረኛ ነው፡፡ ሁሉም በሚባል መልኩ የችግሮች ሁሉ ምንጭ መንግሥት እንደሆነ ያስባል፡፡ በእርግጥ መንግሥት ሥልጣን ስላለው ብዙ ነገሮች ይጠበቅበታል፡፡ በአዋጅ በአንድ ሌሊት ነገሮችን ሊለውጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ከመንግሥት በበለጠ ከሕዝብ አብዛኛው ነገር ይጠበቃል፡፡
ትልቁ ችግር ፍሬ ቢስ የትምህርት ፖሊሲውና የፈጠረው የትምህርት ሥነ ልቦና ነው፡፡ ትምህርት ፍሬ ቢስ መሆኑን ዱሮውንም ሕዝቡ የማንበብ ባህል የሌለው በመሆኑ በኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣት እጅግ ከባድ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በሳይንስ ከማመን ይልቅ አሁንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመናፍስት ያምናል፣ ይህ ሃይማኖትን ይጨምራል፡፡
‹‹በመናፍስት ኃይል ይገኛል›› የሚሉ የድንጋይ ዘመን ሰዎች በአገራችን አሉ፡፡ ዓይን ያወጡ ህሊናቢስ ሙሰኞችን በዚህች ጽሑፍ መግለጽ ከባድ ስለሆነ ማለፍ ይሻላል፡፡
ለውጥ ለማምጣት የትምህርት ፖሊሲውን መቀየር፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን አሳታፊ ማድረግ፣ ሙሰኞችን አደብ ማስያዝና የሚያነብ ትውልድ መፍጠር አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ ይህቺም ጽሑፍ ረዥም ሆና ብዙ የማያነብ ስልቹ ሕዝብ ይኖራል፡፡ እርስዎ እዚህች መስመር ላይ ከደረሱ ታላቅ አንባቢ ነዎት፡፡
- ሀብቴ ጀቤሳ ደበላ (ዶ/ር) በሊንክደን ማኅበራዊ ገጻቸው የከተቡት