Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንዲመቻችለት ጠየቀ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንዲመቻችለት ጠየቀ

ቀን:

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንዲያመቻችለት ለፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ የውይይት መድረክ እንዲመቻችለት የጠየቀው፣ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የተዋቀረው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ባዘጋጀው ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና በአጠቃላይ ሒደቱ ላይ ያለውን የልዩነት አቋም ለማስጨበጥና አማራጭ የሚለውን ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮች በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የከፍተኛ ኃላፊዎች የምክክር መድረክ›› የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተሳታፊ እንዲልክ ጥሪ አስተላልፎ እንደነበር ሪፖርተር ከምንጮቹ ለመረዳት ችሏል። 

ይሁን እንጂ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍትሕ ሚኒስቴር ለደረሰው ጥሪ በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹አስቀድሞ በተያዙ ተደራራቢ የሥራ ፕሮግራሞች ምክንያት ለመገኘት የማንችል መሆናችንን በአክብሮት እንገልጻለን፤›› ብሏል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፍትሕ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ አስቀድመው በተያዙ ተደራራቢ የሥራ ፕሮግራሞች ምክንያት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ለመወያየት በተጠራው የከፍተኛ ኃላፊዎች የምክክር መድረክ ላይ ለመገኝት ባይችሉም፣ በተረቀቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና በአጠቃላይ ሒደቱ ላይ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰፊ ልዩነቶች እንዳሉት አስታውቀዋል። 

እነዚህን ልዩነቶች በማሳወቅ መፍታት እንዲቻል ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ጥልቀት ያለው ወይይት ለማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍላጎት እንዳለው የጠቀሱት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ ለዚህም ሲባል የፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ የውይይት መድረክ እንዲያመቻችላቸው በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል። 

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ውይይት እንዲመቻች የጠየቁበት ለፍትሕ ሚኒስቴር የተጻፈ ደብዳቤያቸው፣ በሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲና በአጠቃላይ ሒደቱ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሠረታዊ የልዩነት ነጥቦች ናቸው ያሏቸውን ጠቅሰዋል።

ከጠቀሷቸው የልዩነት ነጥቦች መካከልም የተረቀቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሠረት ያላደረገ፣ የትግራይ ክልልን ልዩ ሁኔታ ከግንዛቤ ያላስገባና የትግራይ ክልልን ወሳኝ ተሳትፎ ያላካተተ የሚሉት ይገኙባቸዋል። ከላይ የተጠቀሱትን የልዩነት ሐሳቦችን በሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ ለተገኘውና በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ለተመራው የልዑካን ቡድን ማንሳታቸውን ገልጸዋል። በወቅቱም የትግራይ ክልል ሕዝብ ካለበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱን ከማፋጠን ይልቅ፣ በእርጋታ መምራት እንደሚያስፈልግ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማንሳቱን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የትግራይ ክልል ሕዝብን ጊዜ የማይሰጡ ጥያቄዎችና ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት መተማመንን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን (ዶ/ር) ባሉበት፣ በእሳቸው ለተመራው የልዑካን ቡድን ተነስቶ ውይይት እንደተደረገበት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በጻፉት ደብዳቤ ዘርዝረዋል።

ከዚህ ባለፈም፣ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፉን ያረቀቀው የባለሙያዎች ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ትግራይ ክልል በመምጣት ከተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በተወያየበት ወቅት፣ ተወካዩቹ ከላይ የተጠቀሱትን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የልዩነት ነጥቦች በማጠናከር ማንሳታቸውን እንደተረዱ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል። 

‹‹አሁን ያለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቀራረፅና አደረጃጀት ላይ የትግራይ ሕዝብ ዕምነት እንደሌለው›› የባለሙያዎቹ ቡድን በክልሉ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ መነሳቱን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከደረሰው መረጃ መገንዘቡን በደብዳቤያቸው ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ሆነ የማኅበረሰብ ተወካዮች ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችኧ ወይም የመፍትሔ አቅጣጫ የተቀመጠ ስለመሆኑ የሚያመላክት ነገር አለመገኘቱን አክለዋል። 

‹‹ስለሆነም በእኛ በኩል በሚነሱ ሐሳቦች ዙሪያ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሠረት ባደረገ መንገድ ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ጥልቀት ያለውና ግልጽ መፍትሔ ማስቀመጥ የሚያስችል ውይይት ለማድረግ ፍላጎት ያለን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። ይህ የሁለትዮሽ ውይይትም በእናንተ [በፍትሕ ሚኒስቴር] በኩል እንዲመቻችልን እንጠይቃለን፤›› ሲሉ ለፍትሕ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል። 

የፍትሕ ሚኒስቴር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ላቀረበው ጥያቄ የሰጠውን ምላሽ ወይም የያዘውን አቋም ለማወቅ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። 

ይሁን እንጂ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንዲመቻችለት ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ገልጸዋል።

በተረቀቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና እስካሁን ባለው ሒደት ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያነሳቸውን የልዩነት ነጥቦች በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የባለሙያዎች ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር)፣ ከየትኛውም ክልል በተለየ ሁኔታ ጥልቀት ያለው ውይይት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና በክልሉ ከሚገኙ ምሁራን ጋር መደረጉን ገልጸዋል። በውይይቱ ወቅትም አዎንታዊ ተሳትፎ እንደነበርና ሒደቱንም እንደሚደግፉት በግልጽ የተናገሩበት መድረክ እንጂ፣ ከላይ የተገለጸው ዓይነት አቋም ጨርሶ እንዳልተንፀባረቀ አስረድተዋል። አሁንም ቢሆን በረቂቅ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ከትግራይ ክልል የሚነሳ ሐሳብ ካለ የባለሙያዎች ቡድን ለማዳመጥ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሁሉም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ በተጠራው መድረክ ላይ የትግራይ ክልል አመራሮች ያልተገኙት በሥራ መደራረብ ምክንያት መሆኑን ብቻ እንደሚያውቁ የገለጹት ማርሸት (ዶ/ር)፣ የሽግግር ፍትሕ ሒደቱን የበለጠ አሳታፊ ለማድረግ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሙያ እንዲመድብላቸው ጭምር ተጠይቆ እንዳልተመደበ ተናግረዋል።

ማርሸት (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹እኛ ለአገር አስተዋጽኦ ለማበርከት ያሰብን ገለልተኛ ባለሙያዎች እንጂ ፖለቲከኞች አይደለንም፣ አሁንም ቢሆን የሚነሱ ጠቃሚ ሐሳቦች ካሉ ለማዳመጥ ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል።

የባለሙያዎች ቡድኑ ከአዲስ አበባ በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የሽግግር ፍትሕ አማራጭ ፖሊሲ ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ ማከናወኑን፣ ከሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል። 

ለመተግበር የታቀደው የሽግግር ፍትሕ በአገሪቱ የተፈጸሙ የቀደሙና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተፈጸሙ በደሎችን እውነታ መርምሮ በማውጣት፣ ከፍተኛ በደሎችን በፈጸሙት ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና በደል የተፈጸመባቸው ግለሰቦችና ማኅበረሰቦች በይቅርታ፣ በዕርቅና በመካስ እንዳይደገም ለማድረግ ያለመ ነው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...