Monday, December 11, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የትምህርት ዓመቱ ሲጀመር፣ በሌሎች አካባቢዎችም ተማሪዎች ሰሞኑን የትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በምሽትና በርቀት የሚከናወኑ ትምህርቶችም ይጀመራሉ፡፡ ዘንድሮ ለተማሪዎች የግብረ ገብነት ትምህርት መስጠት እንደሚጀመር ተሰምቷል፡፡ ይህ በእጅጉ ሊያስደስት የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ትምህርት ሲጀመር በአገር አቀፍ ደረጃ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም መነሳት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ያጋጠመው ስብራት ተጠግኖ ፍትሐዊ ተደራሽነት ከጥራት ጋር እንዲገኝ፣ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ በባለቤትነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ሐዲዱን በመሳት በአገር ላይ ያደረሰው ኪሳራ ይታወቃል፡፡ ሕዝባችንን ለከፋ ድህነት፣ ለዕልቂትና ለውድመት የዳረጉ ግጭቶች በሙሉ የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ውጤት ናቸው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ያገኘ ዜጋ ይነጋገራል እንጂ፣ በየምክንያቱ ነገር እየተፈላለገ እርስ በርሱ አይፋጅም፡፡

ትምህርት ጥራቱ ተጠብቆ በምርምር እየታገዘ አገር ለምትፈልገው ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲውል፣ በተለይ የአገሪቱ ምሁራንና ልሂቃን ከማናቸውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ የትምህርት ጉዳይ ዘርፉን ለሚመራው የትምህርት ሚኒስቴርና አመራሮቹ ብቻ የሚተው ሳይሆን፣ ከማናቸውም ፖለቲካዊ ውግንና በፀዳ መንገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሊሆን ይገባል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ተስተካክሎ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ይተኮር፡፡ ትምህርት ቤቶች የአገር አቅም በፈቀደ መጠን ደረጃቸውን ጠብቀው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችና ተጓዳኝ አቅርቦቶች በሥርዓት እንዲደራጁ፣ ብቃት ያላቸው መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እንዲሰማሩ፣ የመማር ማስተማሩን ሒደት ከሚያግዙ ጉዳዮች በስተቀር አዋኪ ነገሮች እንዳይኖሩ፣ በአጠቃላይ ተማሪዎችን ለማብቃትና ለማነፅ የሚያስችል ምኅዳር መፍጠርና የመሳሰሉት አዎንታዊ ቁምነገሮች ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ ትምህርት ቤቶችን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መድረክ ለማድረግ የሚፈልጉ ካሉም ገለል ማድረግ ይገባል፡፡ ተማሪዎች ተረጋግተው ተምረው ለፈተና ብቁ የሚሆኑት ከአክሳሪ ድርጊቶች መራቅ ሲቻል ብቻ ነው፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ለትምህርት ትኩረት መስጠት የሚያስፈልገው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ በድንቁርና ምክንያት መራብ ስለሌለበት፣ በሥልጣኔ ዕጦት ወገን ለወገኑ እንደ ጠላት እየተያየ መፋጀት ስለሌለበት ነው፡፡ ትምህርት የሁሉም ችግሮች መፍቻ ዋነኛው ቁልፍ እንዲሆን ካልተደረገ ረሃብም ሆነ ፍጅት ሊቆሙ አይችሉም፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ሲኖር ግብርናው ይዘምናል፡፡ ግብርናው ሲዘምን ለብዙ ሺሕ ዓመታት ከተንሰራፋው ኋላቀር አስተራረስ በመላቀቅ ዘመናዊ እርሻዎች ይስፋፋሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተበጣጠሰ እርሻ በአማካይ በዓመት የሚታረሰው 15 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በሁለትና በሦስት እጥፍ ያድጋል፡፡ ክረምት ከበጋ በዝናብና በመስኖ የሚታረሰው መሬት መጠን ሲጨምር ምርት ይትረፈረፋል፡፡ የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ምርት መጠን በጣም ይጨምራል፡፡ እንደ ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ፣ ዓይብና የመሳሰሉ ተዋፅኦዎች ዋጋ አቅም አይፈትንም፡፡ ተመጣጣኝ ምግብ በብዛትና በጥራት ማግኘት ሲቻል መቀንጨር አይኖርም፡፡ ጥራት የሌለው ትምህርት በመጥፋቱ ብቻ ኢትዮጵያውያን ዳቦ ማግኘት ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኗቸው በቁማቸው ጎብጠዋል፡፡

ጥራት ያለው ትምህርት ሌላው ፀጋው በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ማስቻሉ ነው፡፡ በማናቸውም ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መነጋገር ያስችላል፡፡ በኢትዮጵያ ዓውድ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ትልቁ ተግዳሮት ለሁሉም ግላዊም ሆነ አገራዊ ጉዳዮች፣ አማካይ ሥፍራ ይዞ ለመነጋገር አሻፈረኝ ማለት ባህል መሆኑ ነው፡፡ ለልዩነቶች ዕውቅና መስጠት ዴሞክራሲያዊ ባህል እንደሆነ ለብዙ ጊዜ ብዙ የተባለበት ቢሆንም፣ በተለይ የአገሪቱ ምሁራንና ልሂቃን የሚበዙበት የፖለቲካ መንደር ተግባራዊ ማድረግ ተስኖታል፡፡ በዘመነ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለም እየተከተሉ፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን ማስተናገድ አቅቷቸው ‹‹የመስመር ልዩነት›› ተባብለው አንድ ትውልድ አልቋል፡፡ ያ የመስመር ልዩነት መኖሩ እስከማያስታውቅ ድረስ ዛሬ በፀፀት ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ናቸው፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ የመሬት ሥሪቱ ከኢሕአዴግ ፍላጎት በተቃራኒ መስተካከል እንዳለበት ጥያቄ ሲቀርብ፣ ‹‹በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር…›› እየተባለ በርካታ ቀውሶች ደረሱ፡፡ ኢሕአዴግ ተወግዶም ያ ጥያቄ ግን ዛሬም አለ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር በአብዛኛው የተሞላው በአርቆ አሳቢዎችና በብልሆች ባለመሆኑ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የጥራዝ ነጠቆችና ከታሪክ ለመማር ዝግጅት የሌላቸው ስለሞሉበት፣ ኢትዮጵያን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ጎትቶ ለማውጣት አዳጋች ሆኗል፡፡ የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ ቢረፍድም ጥራት ያለው ትምህርት አግኝቶ እንዲታነፅ ማድረግ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ አዲሱ ትውልድ በግብረ ገብነት ተኮትኩቶና በሥነ ምግባር ታንፆ ሲያድግ ከንቱ ነገሮችን ይፀየፋል፡፡ ከግላዊ ምቾትና መንደላቀቅ በላይ ለአገሩና ለሕዝቡ ዕድገትና ሰላም ይጨነቃል፡፡ እንደ ነቀዝ አገሩን በቁሟ ለመብላት ከማድባት ይልቅ፣ በምን ዓይነት ዘዴ አድጋለት ከሠለጠኑ አገሮች ጋር እኩል እንደምትሆን እንቅልፍ አጥቶ ይተጋል፡፡ መሬት በመውረር፣ የመንግሥት ካዝና በማራቆት፣ ግብር በማጭበርበር፣ ካልተገባ ግዥ፣ ጨረታና ኮንትራት በመጠቀም፣ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት አንቆ በመያዝ ትርፍ በማግበስበስና በመሳሰሉት ወራዳ ተግባራት ውስጥ አይሰማራም፡፡ ይልቁንም ኢሞራላዊ ድርጊቶች በተግባር እንዲወገዱ ሽንጡን ገትሮ ይፋለማል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሙሉ በብሔር፣ በእምነት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገደቡ ለትምህርት ሁለንተናዊ ዕድገት በአንድነት ይቁሙ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን ወላጆች ልጆቻችሁ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ፣ ትምህርት ከማናቸውም የፖለቲካ የገመድ ጉተታዎች እንዲላቀቅ በጋራ ክትትል አድርጉ፡፡ ልጆቻችሁ ጠንካራና ብቁ መሆን የሚችሉት በዕውቀትና በክህሎት ሲበለፅጉ ነው፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዕውቀትና ክህሎት ተሳታፊ ሲሆኑ የማንም መፈክር ተሸካሚ አይሆኑም፡፡ ማንም እየተነሳ እንደ ጋማ ከብት አይጭናቸውም፡፡ ብርቱ ሞጋችና ጠያቂ ስለሚሆኑ በቀላሉ የማንም አጀንዳ ማስተጋቢያ አይደረጉም፡፡ ማንም በቀደደው ቦይ እንደ ወራጅ ውኃ አይፈሱም፡፡ በሐሰተኛ መረጃዎች በቀላሉ ስለማይታለሉ ከዓላማቸው ፍንክች አይሉም፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙዎች የተጎዱት በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ጥራት ያለው ትምህርት ባለማግኘታቸው ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ጥራት ላለው ትምህርት መዳረስ በአንድነት መቆም የግድ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ይላቀቅ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...

የስኳር ፋብሪካዎች መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው  እያመረቱ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ውስጥ ከተካተቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለጥቃት ተጋላጮች አስተማማኝ ከለላ ይሰጥ!

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብዓዊ...

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...