Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጎዳና ተዳዳሪዎችን በግዳጅ ማቆያ ማስገባት በአስቸኳይ እንዲቆምና የፖሊሲ ምላሽ እንዲሰጥ ኢሰመኮ አሳሰበ

የጎዳና ተዳዳሪዎችን በግዳጅ ማቆያ ማስገባት በአስቸኳይ እንዲቆምና የፖሊሲ ምላሽ እንዲሰጥ ኢሰመኮ አሳሰበ

ቀን:

  • በማቆያ ማዕከሉ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ አስታውቋል

የጎዳና ተዳዳሪዎችን በግዳጅ ማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ የማድረግ ተግባር በአፋጣኝ እንዲቆምና ለዚሁ ለችግር ዘለቄታዊና ሁሉን አቀፍ የፖሊሲ ምላሽ እንዲሰጥ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡

ኢሰመኮ ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአብዛኛው ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ያደረጉ ሰዎች ከጎዳና ላይ ተነስተው የሚቆዩበት በሸገር ከተማ ሲዳ አዋሽ ወረዳ በተለምዶ ‹‹ሲዳሞ አዋሽ›› እንደሚባል አስታውቋል፡፡ ጊዜያዊ ማቆያው ለኢንዱስትሪ ዕቃዎች ማከማቻ የተዘጋጀ ቢሆንም በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያነት እንዲያገለግል መደረጉን አስታውቋል።

የማቆያ ማዕከሉ አስተባባሪዎችና ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላትን፣ በቦታው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎችንና ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኙ የነበሩ የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን በማነጋገር ስለጉዳዩ አስፈላጊ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ የማቆያ ቦታው የተሟላ መሠረተ ልማት የሌለውና ለተፈለገለት ዓላማ ምቹ ባለመሆኑ፣ በጣቢያው የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ ክብር የጠበቀ አያያዝ እንዳይኖር አድርጎታል ብሏል፡፡

የተሟላ የንፅህና ቤቶች አለመኖር፣ ለግል ንፅህና መጠበቂያ የሚሆኑ የውኃና የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦቶች አለመሟላት፣ አልጋ፣ ፍራሽና አልባሳት አለመኖራቸው፣ ለማደሪያ የተዘጋጀው ቦታ በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን የማያገኝ መሆኑንና ከፍተኛ የንፅህና ችግር እንዳለ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በዚህ ማዕከል በተባይ የሚተላለፍ ሕመም በመከሰቱ ሳቢያ ለተላላፊ በሽታ የተጋለጡ ሰዎች ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እንዳገኙ የኢሰመኮ መግለጫ ያስረዳል፡፡

የተከሰተው ተላላፊ በሽታ በተባይ በ‹‹ቅማል›› የሚመጣ ተስቦ (Relapsing Fever) መሆኑን፣ በመጠለያ ጣቢያው ከነበሩ ሰዎች መካከል 190 ሰዎች በሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን፣ ክትትሉ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የሦስት ሰዎች ሕይወት ያለፈ መሆኑንና ሦስት ሰዎች ደግሞ በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ሕክምና እያገኙ እንደነበር ከሕክምና ተቋሙ ለማወቅ መቻሉን፣ የኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባደረገው ክትትል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማቆያ ማዕከሉ ውስጥ ይገኙ እንደነበር ገልጾ፣ በቅርቡ ባደረገው ሪፖርት ክትትለል ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ኢሰመኮ የማቆያ ማዕከሉ አስተባባሪዎች ገለጹልኝ እንዳለው፣ በጊዜያዊ ማዕከሉ ከሚገኙት ሰዎች ውስጥ 29 በቀን ሥራ የሚተዳደሩ የጥበቃና የግንባታ ሠራተኞች፣ እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተለቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሚመለከታቸው የከተማ የፀጥታና አስተዳደር አካላት በአሁኑ ወቅት በዚህ ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ሰዎችን አያያዝ ለማሻሻል፣ ሰብዓዊ ክብርና አያያዝን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የምግብ፣ የውኃ፣ የመኝታ፣ የንፅህናና የሕክምና አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ሊያሟሉ እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

ሰዎችን በግዳጅ ወደ አንድ ማቆያ ማዕከል ማስገባት ወይም ለኑሮ ከመረጡት ቦታ ወደ የማይፈልጉበት አካባቢ እንዲሄዱ ማስገደድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚያስከትል መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

ይህ አስገዳጅ አሠራር በአስቸኳይ እንዲቆም በማድረግ መኖሪያቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን ከጎዳና ላይ ማንሳትና ተገቢ አገልግሎቶችን መስጠት፣ በፈቃደኝነትና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት ሊተገበር የሚገባ በመሆኑ በአስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚከናወኑ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ጉባዔዎችና ከሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ መኖሪያቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በኃይል ከጎዳና ላይ በማንሳት በአንድ ሥፍራ እንዲቆዩ የሚደረጉበትን ሁኔታ በተመለከተ የክትትል ውጤቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...