Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየተመድ መርማሪ ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ተጠያቂነትን ለማድበስበስ ነው አለ

የተመድ መርማሪ ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ተጠያቂነትን ለማድበስበስ ነው አለ

ቀን:

በሰሜን ኢትዮጵያና ከዚያም ወዲህ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር በተመድ የተቋቋመው የመርማሪዎች ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ሆን ተብሎ ተጠያቂነትን ለማድበስበስ ነው አለ፡፡

ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ የምርመራ ሪፖርቱን ያቀረበው የመርማሪ ኮሚሽኑ በመቶ ሺዎች ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባ ሆነዋል ካለ በኋላ፣ አሁንም የመቀጠል አዝማሚያውና አቅሙ ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡

‹‹በመንግሥት የተቋቋመው የሽግግር ፍትሕ አካታችነትና ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ የመንግሥትን ቀነ ገደብ (Deadline) እንዲያሟላ ግፊት ተደርጎበታል፡፡ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ እነዚህን ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ማየት አይችልም፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ኃይሎችን በአገራዊ ሽግግር ፍትሕው ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ የለም፤›› ሲሉ፣ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ታንዛኒያዊው መሐመድ ቻንድ ሪፖርቱን በተመለከተ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ከተቋቋመ ወዲህ ያቀረበው ይህ ሪፖርት ሁለተኛው ሲሆን፣ የአሁኑ ሪፖርት ከጥቅምት 2013 እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም.  ያለውን ጊዜ ያካተተ ነው፡፡

ጥሰቶቹ ወደ ተፈጸሙባቸው ቦታዎች ሄዶ ለመመርመር የኢትዮጵያ መንግሥት ሊፈቅድልን አልቻለም ያሉት ኮሚሽነሮቹ፣ ሪፖርቱን ያዘጋጁት ተጠቂዎችን በስልክ በማነጋገር፣ ወደ ጎረቤት አገሮች በግጭት ምክንያት የሸሹ ኢትዮጵያውያን ቃለ መጠይቅ በማድረግና የተለያዩ ሰነዶችን በመመርመር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በዚህም መሠረት 545 የዓይን እማኞች በቀጥታ ቃለ መጠይቅ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን ለሪፖርቱ የተጠቀሙት 360 ያህሉን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ የትግራይ ኃይሎች፣ የአማራ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎችና የክልል ልዩ ኃይሎች በተለያዩ ክልሎች ‹‹እስከ ጦር ወንጀል›› እንዲሁም ‹‹እስከ ዘር ማጥፋት›› ሊደርሱ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ በትንሹ ከአሥር ሺሕ በላይ ሴቶችና ሕፃናትም ተደፍረዋል ሲልም ያክላል፡፡

ምንም እንኳን ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በትግራይ ትልልቅ ጦርነቶች ቢቆሙም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግን ቀጥለዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ በኦሮሚያ የቀጠለው ግጭትና በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት አገሪቱ ‹‹የብጥብጥና የአመፅ›› ቦታ ሆና እንድትቀጥል አድርጓታል ሲሉ ኮሚሽነሮቹ ተናግረዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያሉ አሳሳቢና አስደንጋጭ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀጠል የለባቸውም፡፡ ለተፈጸሙት ጥሰቶች ጠንካራ (Serious) የዓለም አቀፍ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት መስፈን አለበት፡፡ በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያን መንግሥት ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም፤›› ሲሉ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑ አባል የሆኑት ስሪላንካዊቷ ራዲካ ከማራስዋሚ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ‹‹የከፉ›› በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ሩዋንዳን ጨምሮ የብዙ አገሮችን መርምሬያለሁ፣ የኢትዮጵያው ግን የከፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

መቀመጫውን ኢንቴቤ ኡጋንዳ ያደረገው የተመድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ቀነ ገደቡ በታኅሳስ 2016 ዓ.ም. የሚያበቃ ሲሆን፣ እንደገና በአንድ ዓመት ይራዘማል ወይስ ይዘጋል የሚለው አልታወቀም፡፡ ይህን ለመወሰን የጉባዔው አባል አገሮች በቅርቡ ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹እስካሁን የሠራነው ሪፖርት የተሟላ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጥሰቶቹ ዋነኛ ተጠያቂ የሆኑት ባለሥልጣናትንና ወታደራዊ አዛዦች አግኝተን ማናገር አልቻልንም፡፡ ስለዚህ ካውንስሉ የኮሚሽኑን ዕድሜ ያራዝማል ብለን እንጠብቃለን፤›› ሲሉ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ተመድ ኮሚሽኑን ያቋቋመው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጣሰ መንገድ የምዕራባውያንን ፖለቲካ ፍላጎት አንግቦ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑን አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑ በተመድ በጀት እንዳይመደብለትም ሆነ የሥራ ጊዜ (Mandate) እንዳይራዘም፣ ኢትዮጵያ ለተመድ ያቀረበችው ጥያቄ በድምፅ ብልጫ ውድቅ ተደርጎባታል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ብሪክስን (BRICS) ከመቀላቀሏ ጋር ተያይዞ በቀጣይ በሚደረገው የድምፅ አሰጣጥ ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ኮሚሽኑን ሲደግፉ የነበሩት አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር የቆዩትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ነበረበት እየመለሱ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ግን ኢትዮጵያ በእጅጉ የምትፈልገውን ገንዘብ ከመልቀቅ እንደተቆጠቡ ነው፡፡ ምክንያቱ በግልጽ ባይገለጽም ከሽግግር ፍትሕና ከተጠያቂነት ከጀርባ ያሉ ጉዳዮች እንደሆኑ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የተቋቋመው አገር በቀል ከሽግግር ፍትሕ ባለፉት ዓመታት ብቻ ሳይሆን፣ ባለፉት መንግሥታት ጭምር የተፈጸሙትን ጥሰቶች እንደሚመለከት እየገለጸ ነው፡፡

‹‹የተፈጸሙት ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመደበኛው ሕግ ሊታዩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለየት ያሉ ተቋማት ጥሰቶችን በመመርመር፣ ዳኝነትን በማስፈንና ዕርቅ በማምጣት አገሪቱን ወደ ሰላም ለማምጣት ዝግጅት እያጠናቀቅን ነው፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር)  ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ከተቋቋመ ባለፉት ስምንት ወራት ያከናወናቸውን ሥራዎች ሪፖርት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር አዳራሽ አቅርቧል፡፡ ቡድኑ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ ትግበራ ይገባል ሲሉ የቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...