Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአሉቶ ላንጋኖ ጂኦተርማል ኃይል ለማመንጨት የሚፈልጉ ኩባንያዎችን ለመምረጥ ጨረታ ሊወጣ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቁፋሮ ተጠናቆላቸው ኃይል እንደሚያመነጩ ለተረጋገጠላቸው የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰ ምድር እንፋሎት ማመንጫ ጉድጓዶች፣ ራሰቸው ፋይናንስ በማፈላለግ ወይም ከመንግሥት ጋር በአጋርነት ለመሥራት የሚፈልጉ ኩባንያዎችን ለመምረጥ ጨረታ ሊወጣ ነው፡፡

በባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋ እንደተደረገው፣ በአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ (ጂኦተርማል) አሥር ጉድጓዶች ተቆፍረው ስድስቱ ተጠናቀው በተደረገው ሙከራ ከ25 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ሊመነጭባቸው ይችላል፡፡

የቀሪዎቹን አራት ጉድጓዶች ሙከራ እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ በማጠናቀቅና ሌሎች ተጨማሪ አራት ጉድጓዶችን ደግሞ ከዓለም ባንክ በተገኘ ተጨማሪ ድጋፍ እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም. በመቆፈር ነው፣ ከእንፋሎት የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የታቀደው፡፡

በአሥሩ ጉድጓዶች እስከ 70 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት እንደታሰበና ለሚገኘውም ኃይል ማመንጫ የሚተክልና ቀሪ ሥራዎችን የሚያናወኑ ኩባንያዎች ለመምረጥ የጨረታ ሒደት እንደሚካሄድ ለሪፖርተር የገለጹት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡

ወደ ኃይል ማምረት ሥራ ለመግባት ትልቅ የፋይናንስ አቅም እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም በቀጣይ ጨረታ ለማውጣት ሰነድ እየተዘጋጀ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

‹‹ፋይናንስ ይዘው መጥተው የሚሠሩ ወይም በመንግሥትና ግል አጋርነት ማልማት የሚችሉ በሚል በሁለቱም የጨረታ ሰነድ አዘጋጅተናል፤›› ያሉት አሸብር (ኢንጂነር)፣ ጨረታው ካወጣና ምላሽ ከተገኘ በኋለ በአንዱ ተወስኖ እንደሚሄዱበት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ቁፋሮ እየተካሄደ እንደሆነና ኃይል መኖሩን መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የፋይናንስ አቅም እጥረትን የመሰሉ ችገሮች እንደገጠሙትና ትንሽ መዘግየት እንዳለበት፣ ሆኖም በአንዱ ጉድጓድ የእንፋሎት ኃይል መኖሩ ተረጋግጧል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት ሥራ ውድ እንደሆነ፣ አንዳንዴም ጉድጓድ ተቆፍሮ ምንም ላይገኝ እንደሚችል፣ ከተሳካም ከአንድ ጉድጓድ ብቻ 20 እና 30 ሜጋ ዋት ሊገኝ እንደሚችል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች