- እስከ መስከረም 11 ክምችታቸውን የማያሳውቁ ነዳጅ አይጫንላቸውም ተብሏል
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ሥርጭትን በዲጂታል ለመከታተል እንዲያመቸው፣ የነዳጅ ኩባንያዎችና ማደያዎች ያላቸውን የክምችት መጠን እንዲልኩለት አሳሰበ፡፡
ኩባንያዎቹ ከነዳጅ ማደያዎቻቸው ያላቸውን የክምችት መጠን በመሰብሰብ መረጃውን ለባለሥልጣኑ እስከ መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲያሳውቁ፣ መረጃውን ካልሰጡ ግን ‹‹ከነዳጅ ጭነት ውጪ›› እንደሚሆን ባለሥልጣኑ አሳስቧል፡፡
በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሃርላ አብዱላሂ ተፈርሞ ለሁሉም የነዳጅ ኩባንያዎች መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ የነዳጅ ማደያዎችን እንቅስቃሴ ለመከታተል ሲባል ነው የክምችት መጠናቸውን ለማወቅ የተፈለገው፡፡
የነዳጅ ግብይት ቁጥጥርን ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል የማድረግ ዕቅዱን ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው ባለሥልጣኑ፣ በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች በሚገኙ ከፊል ማደያዎች ላይ ብቻ ተግባራዊ በማድረግ እየሠራበት ነው፡፡
የነዳጅ ዲጂታል ክትትል ቁጥጥሩ የሚከናወነው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በጂቡቲ ለነዳጅ ኩባንያዎች ነዳጁን ሲያራግፍ ጀምሮ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ደግሞ ነዳጁን አጓጉዘው ለማደያዎቹ እስኪያራግፉና ማደያዎቹም ለደንበኞቻቸው ነዳጅ እስኪቀዱ ድረስ ያለውን ሒደት ኢትዮ ቴሌኮም ባለማው መተግበሪያ ነው፡፡
አሠራሩ በመንግሥት ውሳኔ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ በማደያዎች የሚደረገውን የነዳጅ ሽያጭ በቴሌ ብርና በሌሎች የዲጂታል ክፍያ መተግበሪያዎች ብቻ እንዲሆን ከሆነ በኋላ፣ ኩባንያዎችም ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ከማደያዎቹ ጋር የሚኖራቸውን ግብይት በዲጂታል ቁጥጥር ውስጥ ለማካተት የታለመ ነበር፡፡
በዚህም የዲጂታል ሥርዓቱ ተዘርግቶ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ አስገዳጅነቱ በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች በሚገኙ ኩባንያዎችና ማደያዎች ላይ ነበር፡፡ ከማደያ ወደ ተሽከርካሪ የሚደረገው የነዳጅ ሽያጭ ግን በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች በግዴታ በቴሌ ብርና በሌሎች መተግበሪያዎች እየተተገበረ ነው፡፡