Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ ከወራት በኋላ ሥራ እንደሚጀምር ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የግንባታው አጠቃላይ ወጪ እስከ ስድስት ቢሊዮን ብር ሊጠይቅ ይችላል ተብሏል

ከተጀመረ ዓመታትን ያስቆጠረውና በሦስት ዙር የሚገነባው የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ በመጪዎቹ አምስት ወራት የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ሊጀምር እንደሆነ ታወቀ፡፡ በሦስት ዙር የግንባታ ሒደት የተከፋፈለው ማዕከሉ በ2009 ዓ.ም. የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ሲሆን፣ ግንባታው በ2010 ዓ.ም. ተጀምሮ በ2016 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡

የማዕከሉ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው አባተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ጋር በአጋርነት ግንባታው መጀመሩን አስታውሰው፣ በአጋርነት ታስቦ የነበረው ፕሮጀክት ወደ አክሲዮን ኩባንያነት ተቀይሮ አሁን ከ1,000 በላይ ባለድርሻዎች አሉት ብለዋል፡፡

ማዕከሉ 11 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን፣ በአሁኑ ጊዜ 1,052 ባለአክሲዮኖች እንዳሉት፣ የማዕከሉ ባለአክሲዮን ከሆኑ መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ተገልጿል፡፡  

ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ወጋገን ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ አቢሲኒያና አዋሽ ኢንሹራንስ፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ውጪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች ግለሰቦች ናቸው ተብሏል፡፡

ከእነዚህ ተቋማት መካከል የከተማ አስተዳደሩ 800 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 150 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 300 ሚሊዮን ብር፣ ኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት 170 ሚሊዮን ብር፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና 130 ሚሊዮን ብር በመቶ የሚሆነውን ካፒታል እንደሚሸፍኑ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በምሥራቅ አፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያውና ትልቁ ነው ያሉት አቶ ጋሻው፣ ሥራ ሲጀምር በዲፕሎማሲውም በፖለቲካውም ዘርፍ የተሻለ ገጽታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በጣሊያን፣ በሆንግ ኮንግና በዱባይ ከተገነቡ መሰል መሠረተ ልማቶች ልምድ በመውሰድ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በተያዘው ዓመት አጋማሽ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ አልቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በግንባታ ላይ የሚገኘው ማዕከሉ የንግድ መደብሮች፣ ሬስቶራንቶች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾችና የኤግዚቢሽን አዳራሾች እንዳሉትም አክለዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚጀመረው የሁለተኛው ምዕራፍ የግንባታ ሒደት በአንድ ጊዜ 5,000 ሰዎችን መያዝ የሚችልና ከዚያ ያነሰ መጠን ያላቸው የተለያዩ መሰብሰቢያ አዳራሾች የሚገነቡበት እንደሚሆን፣ በሦስተኛውና በመጨረሻው ምዕራፍ ባለአምስት ወይም ባለሰባት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት መታሰቡን ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ ሙሉ በሙሉ በ2016 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም የዋጋ ንረት፣ የብር የውጭ ምንዛሪ መውረድ፣ የግንባታ ዕቃዎች መጥፋትና ሌሎችም ተደማምረው የግንባታውን ሒደት ማዘግየቱን ገልጸዋል፡፡

በማዕከሉ ግንባታ የመጀመሪያ የአዋጭነት ጥናት ላይ ቀርቦ የነበረው ዋጋ 1.2 ቢሊዮን ብር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱንና በአጠቃላይ የሦስቱም ምዕራፎች ግንባታ እስከ ስድስት ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል አቶ ጋሻው ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች