ሰላም! ሰላም! በአዲሱ ዓመት የመስከረም አየር ሽው እያለብን አንገታችንን ቀና አድርገን ስንራመድ፣ ልባችን ደግሞ ብሩህ ተስፋ ሰንቆ ለሕይወት ዕድገትና ለነፍስ ተሃድሶ እያወጣና እያወረደ ነው፡፡ ‹‹አሮጌው ዓመት ለአዲሱ ዓመት ቦታውን እየለቀቀለት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…›› የሚለው ማን ነበር? የድሮ ካድሬ ብላችሁ እንዳታስቁኝ አደራ፡፡ አሁንም እኮ ‹‹ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…›› የሚሉ በየቦታው አሉላችሁ፡፡ ለማንኛውም ‹‹ሰው ጥራ ቢሉት ራሱ መጣ…›› የሚባሉ ዓይነቶችን ትተን እስቲ ወጋችንን እንሰልቅ፡፡ ሰላምታውን በወጉ ሳላቀርብ ነገሬን አንጣጣሁት አይደል? ርችት ማንቻቻት ባልችል ቃላት ላንጣጣላችሁ እንጂ። በዚህ አዲስ ዓመት ርችቱ ቀርቶበት ፈንድሻ ለማፈንዳት አቅም ያጠረው ስንቱ ወገን ይሆን? ‹‹አንገት ማስገቢያ ታዛ አጥቶ በየጥጋጥጉ የወደቀውስ ስንት ይሆን?›› ነው ያላችሁት? ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች በባዶ ኪስ በዓል ማክበር አቃተን ብላችሁ፣ የደላቸውን ፈንጠዝያ ከል አታልብሱ እባካችሁ…›› እያለ አንዱ ወፈፌ እዚያ ድድ ማስጫችን ላይ ሲያፌዝብን፣ ‹‹ከእኛ ይልቅ አንተ ያበድከው ትሻላለህ…›› ያሉት አንዲት ምስኪን እናት ነበሩ። እውነታቸውን ነው!
የምር ግን ‹የምጣዱ እያለ የእንቅቡ እየተንጣጣ› የሚባለው ነገር እኔና እናንተን ያካትት ይሆን? ለነገሩ መቸገር ብርቃችን ባይሆን ያሰኝ ነበር። ግን ስልምልም የሚል ተስፋ ታቅፈን ባንኖር ሞራል ሰበራ ይሆንብናል። አንድ የዘመናችን ነገር ግራ ግብት ያለው ወዳጄ፣ ‹‹መሪዎቻችን ለሞራላችን መቶ በመቶ ባይጠነቀቁልንም፣ እኛ ግን ሁለት መቶ ፐርሰንት ድረስ ተሻግረን እንጠነቀቅላቸዋለን…›› ያለው ድንቅ ብሎኝ፣ ‹‹ለመሆኑ ምን ሆነህ ነው ወዳጄ?›› ስለው፣ ‹‹ከላይ እስከ ታች እኮ ቁጥር በጣም ስለሚደፍሩ በሌለ አቅማችን ጠግበን የምንኖር ቅንጡ ያስመስሉናል፡፡ ሃይማኖተኞች መሆናችን ታዲያ ምኑ ላይ ነው? የተመጣጠነ ምግብ በማያውቅ አንጀቴ እንዴት ነገር እችላለሁ?›› አይለኝ መሰላችሁ? አሁንማ ዝም ብዬ ሳስብ ዘመኑ የሥልጣኔ ይሁን የድንቁርና ግራ ግብት እያለኝ ነው። በፊት ይህንን ወዳጄን የማውቀው በመጠጥ ተደፍቆ ኑሮን መርሳት አማራጭ ሲያደርግ ነበር። በነገራችን ላይ የሜድትራኒያን ባህርና የሰሐራ በረሃ የበላቸው ስደተኞች ብዛት ሲያመን፣ እንዴት አጠገባችን በአልኮል ባህር በቁም የሞቱ ወገኖቻችን ሥቃይ እንደማያመን አይገባኝም። በከሰል ጭስ ምክንያት ላጥ ከሚለው ቃታ ስቦ አናቱን በርቅሶ ለሞተ የሚወርደው ሙሾ ተሽሎ መገኘት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንጃ። እና ምን ልላችሁ ነበር? ‹በምድራችን ሕግና በመንግሥት ላይ የነበረውን ተስፋ ወደ ሰማዩ መንግሥት ከመቼው አዞረው? ከመቼ ጀምሮ ተለወጠ?› እያልኩ የፌስቡክ ‹ፕሮፋይሉን› ስጎረጉር ውዬ ማታ ሳየው እሱ ያው ነው። ቀን እየፀለየ ሌሊት አውሬ የሚሆነው መብዛቱ መሰለኝ ችግር የሆነብን፡፡ መጥኔ በሉ እንጂ!
ይገርማችኋል አሁን ቃልና ቃል ሳዋድድ አንዳንድ ዘመናትና አንዳንድ መታወቂያ ቃላቶቻቸው ይመጡብኛል። ብዙ አልጎትታችሁና ዘንድሮ ሃምሳ ዓመት ሊሞላው ከተቃረበው አብዮት ወዲህ የተጠቀሱትን ብቻ እንበልታቸው እስኪ። እዚህ ላይ የአንድ ባላባት ጨዋታ አለ። ያው ያኔ የነበረ ያውቃል። ደርግ ብሎ ጨዋታ ዘበት ነው። ለነገሩ አፍሪካ ውስጥ በአጠቃላይ እንኳን የሥራ ሥሩና የነገራ ነገሩ ጨዋታ ኳስ ጨዋታውም የሚበዛበት እርግጫ ነው። ታዲያ ሰውዬው በዚህ ዘመን እንዳለው አዳራሽ ሙላ ዓይነት ሳይሆን፣ በዚያ ጊዜ በነበረው ርዕዮተ ዓለማዊ ዕሳቤ መሠረት አብዮታዊ ስብሰባ ተጠርተው ይገኛሉ። ሌኒን፣ ማርክስና ኤንግልስ ሲባል በስም እንጂ ሰዎቹን አያውቋቸውም። ኧረ እንኳን እሳቸው እሳት ለኳሾቹ አብዮተኞችስ የት አውቀዋቸው ስትሉ ሰማሁ? ‹የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል› ብዬ ልለፋችሁ እንጂ፣ የመናገር ነፃነታችንን ነፈገን ብላችሁ ወደ እኔ አትመጡም። ወይ ቀልድ!
እናም ስብሰባው ሳይጀመር ጓዶች እየተሰባሰቡ ሳለ ሰውየው መጠየቅ ይጀምራሉ። ‹‹ሌኒን ማን ነው?›› ተነግሯቸው እስኪያዩት ድረስ እየተቁነጠነጡ። ‹‹ያው ሌኒን…›› ብሎ አንዱ በግድግዳው ስፋት ልክ የተዘረጋ አቡጀዲ ላይ ተንሰራፍቶ የሚታየውን ያሳያቸዋል። ‹‹ይኼ ፈረንጁ?›› ሲሉ፣ ‹‹አዎ…›› በማለት ያረጋግጥላቸዋል። ማርክስንና ኤንግልስን ሲጠይቁም ነጎድጓድ ባዘለ አብዮታዊ ድምፅ ተጠቁመው ምሥላቸውን ሲያዩ ምን አሉ መሰላችሁ? ‹‹ታዲያ እነዚህ ፈረንጆች ናቸው አንድ ማገር ሳይማግሩና መርቴሎ ሳያቀብሉ በገዛ ላባችን የሠራነውን ንብረት ያስወረሱብን?›› ካሉ በኋላ የሆኑትን ወይም የተባሉትን እንጃ። በሻሪ ሽረት ሕግ የመደብ ጀርባቸውን ሳይሏቸው ‹አስፎግረው› አቆርቋዥ ወይም አድኃሪ የሚል ጽሑፍ ደረታቸው ላይ አንጠልጥለው ይረሸኑ ይትረፉ አልሰማሁም። ‹‹ከነገር ጅማሬ የነገር ፍፃሜ ይሻላል…›› እያሉ አዛውንቱ ባሻዬ ዘወትር ከሰሎሞን ምሳሌ ሲዋሱ ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ የሚገባኝ አሁን አሁን ሆኗል። እኛ ደግሞ ጥሎብን ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ብለን እየፎከርን ከአገራችን ፊት መሮጥ ስለምንወድ፣ የጅማሬ እንጂ የፍፃሜ ታሪካችን አሳዛኝ ነው። ጊዜው ቆየት ቢልም ግሮሰሪያችን ግድግዳ ላይ፣ ‹‹ለእያንዳንዱ ጅማሬ ፍፃሜ አለው›› የሚል ጥቅስ ነበር፡፡ ወዳጄ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ይህንን ጥቅስ እያየ፣ ‹‹እያንዳንዱ ፍፃሜም ጅማሬ ነበረው…›› ሲል እንደ ዋዛ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ እንዴት ይረሳ!
ወዲህ ስንሻገር ደግሞ የምንጫወተው በ‹ካት ዎክ› ስታይል ነው። አለበለዚያ የጨዋታውን ሕግ ባለማክበርና የመግባቢያ ሰነዱን በመጣስ ተብሎ የሚመጣብን ሊመጣብን ይችላል። ‹‹መጣስ ቀረ የራሱ ጉዳይ…›› አለኝ አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ምኑ?›› ስለው፣ ‹‹አሰልቺው ዝናብ ነዋ፣ ምነው?›› ብሎ አፈጠጠብኝ። መቼም እናንተም እንደ እኔ አንገት ደፍቶ በቃላት ሲባጎ አሸምቆ ከሚያንቃችሁ የሚያፈጥባችሁ ሰው የናፈቃችሁበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል ብዬ እጠረጥራለሁ። ጥርጣሬዬ ወስዶ ያንን የበቀደም በዓል ውሎን ከድሮ ጋር እያነፃፀረ ዓይኔ ዕንባ ዕንባ ይለዋል። አቤት አትሉም? አልሰማችሁኝም እሺ። ነጭ ለባሹ አንሶ ጠብ አጫሪው በዝቶ ዓለማችን እንዲህ እየታመሰች ተጠያቂነትና ግልጽነት ሲርቀን፣ በመናገርና በመጻፍ መብታችን ስም በዘፈን ሲያሳብዱን በሚውሉት ኤፍኤሞቻችን ‹ላግኝሽ ማታ… ማታ…› የሚለውን ተገባብዘን በራችንን መዝጋት ለምዶብናል። ‹ምግብማ ሞልቷል…› ጠዋት ተዘፍኖ ከሰዓት የዕርዳታ እህል መታገዱን በዜና ከሰማን ድርጊቱ በቁጭት ለሥራ ካላነሳሳን ጉድ ነው ያሰኛል። እባካችሁ ሳይደግስ የተጣላንን ዘመን አስታውሱኝ እስኪ!
ጨዋታን ጨዋታ ያስታውሰዋል። ‹‹ወገንና አገር ብቻ በአፍ እየታወሱ በተግባር በዜሮ የሚባዙበት ቀን ብሶ መጣብን እንጂ…›› ሲሉኝ ነበር አዛውንቱ ባሻዬ የበዓል ቀን ተሰባስበን ቡና ስንጠጣ። ብዙ ሰዎች ደላላ በመሆኔ ብቻ ‹የአመለካከት ችግር› ያለብኝ እየመሰላቸው እንደማያዳምጡኝ ብዙ ጊዜ ያጫወትኳችሁ ጉዳዬ ነው። ባሻዬ ግን ያዳምጡኝና የሚደመጥ ጣል ያደርጋሉ። ባሻዬን እንዲህ ስላቸው፣ ‹‹አንተ እኮ የደላህ ነህ። ያ የማንትሴ ልጅ ባለፈው ለአንድ ጉዳይ ላናግረው ሰዓት የሚጠግንባት ሱቁ ሄጄ ያደረገኝን አልነገርኩህም እንዴ?›› ብለው ሳቁ። ነግረውኛልና እኔም በሳቅ አጀብኳቸው። ባሻዬ በአፄው ዘመን የገዟት የእጅ ሰዓት ወደኋላ እየቆጠረች አስቸገረቻቸው። ይሞሏታል ትጎተታለች። ቢጨንቃቸው ወደ ሰዓት ሠሪው ሱቅ ሄዱ። ‹‹ሰዓት አዳሹ ጉንጩ አብጧል…›› ነበር ያሉኝ። ‹‹ሰው አላምጦ የሚውጠው እህል አጥቶ ነው እንዴ ቀንና ሌሊቱን ቅጠል በጉንጩ የሚወጥረው?›› ብለውም አስፈግገውኝ ነበር፡፡ ለሰዓት ሠሪው፣ ‹‹ይህች ሰዓት እየዘገየች አስቸገረች…›› አሉት። ለራሱ መርቅኖ አይናገር አይጋገር ቀና ብሎ እያያቸው፣ ‹‹እሺ ፋዘር ሰላም ነው?›› ይላቸዋል። ‹‹እየሰማኸኝ ነው? ሰዓቴ ትሠራለች ግን ትዘገያለች…›› ይሉታል ደግመው። ቀና ብሎ ዓይቷቸው፣ ‹‹እሺ ፋዘር ሰላም ዋሉ?›› ይላል። እሳቸውም ብልጥ አይደሉ ነገሩ ወዲያው ገባቸው። ጊዜ ራሱ ማርሽ ቀይሮ ዙሩን ስላፈጠነው እንጂ፣ ሰዓታቸው ጤነኛ እንደሆነች ገባቸው። የእጅ ሰዓታቸውን ዙር ከዘመኑ ሰው የጊዜ አቆጣጠር ጋር እኩል ቢያደርጉት ከትርፉ ኪሳራው እንደሚያመዝን ተገንዝበው ተረጋግተው በሰላም ቤታቸው ገቡ። ሰዓታቸውን ሲያዩ ገና ቢሆንም ቀኑ ግን ጨልሞ ነበር። በእኩል ፍጥነት ሳንጓዝ ታዲያ እንዴት እንደማመጣለን? ለአንዱ ቢጨልም ለአንዱ ቢነጋስ ምን ይገርማል? ጉድ እኮ ነው!
በሉ እስኪ እንሰነባበት። የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ስንብት መሆኑ ነው። ለዚህ ነው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዘመንን ብዙ አትደገፈው…›› ሲለኝ የነበረው። የእሱ ነገር እኮ ቢወራ አያልቅም። እዚያም እዚህም ተፍ ተፍ ብዬ ከተቀባበልኳት ላይ ለበዓል ወጪ ተደርጎ ከቁጠባ ተረፍ ያለውን ይዤ ስለነበር፣ ‹‹እስቲ ቤት ደረስ ብለን ምናምን እንቀማምስና ግሮሰሪ ሄደን ትንሽ እንቀዳለን…›› ብዬው ቤት ስንደርስ ማንጠግቦሽ ለመጪው መስቀል በዓል ብላ ቅቤ ታነጥር ነበር። ‹‹ባለሙያ እኮ ነች ውዷ ባለቤቴ…›› ስለው ገና ከሩቅ፣ ‹‹ልብ አድርግ የማንጠግቦሽን ከቅመማ ቅመም ጋር ጊዜ ማጥፋት የሚሰሙ የዘመኑ ልብ አድርቆች፣ ውሎዋን የመብት ረገጣ ነው ብለው በፌስቡክና በዩቲዩብ ዘመቻ ስለሚከፍቱ ላገኘኸው ሁሉ አታውራ…›› አይለኝ መሰላችሁ? በዚህ ጊዜ ቱግ ብዬ፣ ‹‹ቆይ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› ብዬ ሳፈጥበት፣ ‹‹ባህሎቻችንና ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችንን በሚገባ ሳይረዱ፣ በፈረንጅ በጀትና አጀንዳ እየተነዱ ሁሉንም ነገር ከመብት ጋር በማቆራኘት ቤተሰባዊ፣ ማኅበረሰባዊና አገራዊ ትስስሮችን የሚንዱ በዝተዋል ለማለት ነው…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ የምን ጉድ ነው የመጣብን ግን!
‹‹እኔ ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ የትዳሬ ዋልታ እንደሆነች ነው የማውቀው፡፡ ያለ እሷ ሕይወት ለእኔ ባዶ ናት…›› ብዬ መለስ ስል፣ ‹‹ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችንን ለመናድ አንዴ በብሔር፣ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት፣ ቀጥሎ ደግሞ በፆታና በመሳሰሉት እያሳበቡ እንጀራቸውን ላያችን ላይ የሚጋግሩ ባይበዙ ኖሮ አገራችን መጫወቻ አትሆንም ነበር…›› እያለ ተቆጨ፡፡ ‹‹አይገርምህም የዘመንና የአስተሳሰብ አለዋወጥ?›› ስለው እኔም በቁጭት ውስጥ ሆኜ፣ ‹‹ለዚህ ነው ዘመኑን እንምሰል ስንል ለማኅበራዊ መስተጋብሮቻችንና ለጋራ እሴቶቻችን ትልቅ ትኩረት መስጠት የሚያስፈልገው…›› ብሎኝ መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ ግረሰሪያችን ደርሰን ወንበራችን ላይ ስንሰየም ከተፎው አስተናጋጅ ሁለት ያላበው ቢራ ይዞ ከተፍ አለ፡፡ የግሮሰሪያችንን የዘወትር ታዳሚዎች ለአፍታ ቃኘት ሳደርግ ትንሿ ኢትዮጵያ አጠገቤ ያለች መሰለኝ፡፡ ‹‹ተመልከት እስቲ ማዶ ባንኮኒ ላይ በአማርኛ፣ አለፍ ብሎ በትግርኛ፣ ለጠቅ ብሎ በኦሮሚኛ፣ በዚያ በኩል በጉራጊኛ፣ ወዲህ ደግሞ በወላይትኛ፣ ብቻ ምን አለፋህ በብዙ ቋንቋዎች ወጎች ይሰለቃሉ፡፡ የግሮሰሪው ሲዲ ማጫወቻ ደግሞ ከአገረ ሰብ ሙዚቃዎች አልፎ ሬጌ፣ ጃስ፣ ብሉዝና ሌሎችን ያስኮመኩመናል፡፡ ለማንኛውም የአዲሱን ዓመት ጉዞ ከማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን ጋር በክብርና በፍቅር ብንያያዘው የበረከቶቻችን ብዛት ተቆጥሮ አያልቅም ነበር…›› እያለ ምሁሩ ወዳጄ ሲተርክልኝ በአየር ላይ የምንሳፈፍ ያህል ደስ ነበር ያለኝ፡፡ መልካም ሰንበት!