የእንግሊዝ መንግሥት ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ5.9 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ አበረከተ፡፡ ድጋፉ በእንግሊዝና በኔዘርላንድስ ቀይ መስቀል ማኅበራት የቴክኒክ ዕገዛ ይታከልበታል፡፡

ድጋፍም ተደርጓል
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የማሠልጠኛ ማዕከል፣ መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት የተበረከተው ድጋፍ የሚውለው ለጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና ንፅህና አጠባባቅ ላይ ትኩረት ላደረጉ ፕሮጀክቶች ማከናወኛ ነው፡፡
ከተበረከተውም ድጋፍ ውስጥ 3.4 ሚሊዮን ፓውንድ በገንዘብ የቀረበ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ለቴክኒክ ድጋፍ እንደሚውል ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለፕሮጀክቶቹ አገልግሎት የሚውሉ አሥር ተሽከርካሪዎችም ድጋፍ መደረጉ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
የፕሮጀክቱ ማስጀመርያ የስምምነት ሰነድም በእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልሽና በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ መካከል ተፈርሟል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተቋቋመው ከፋሺስት ጣሊያን ወረራ በፊት በሐምሌ 1928 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሥራውንም የጀመረውን በጦርነቱ ለቆሰሉ የኢትዮጵያ ወታደሮችና በወረራው ጉዳት ሊደረሰባቸው ሲቪሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረግ ነው፡፡
ማኅበሩ የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር 48ኛው አባል ለመሆን የበቃው በተመሠረተ በሦስተኛው ወር ላይ ነው፡፡