ተቋማትን ከተቋማት መንግሥታትን ከመንግሥታት ለመለየትና ለማወቅ የየራሳቸው የሆነ መለያ (ብራንድ) እንዲኖራቸው ይገባል፡፡ ይኼንን መለያ ከጥንት ጀምረው የነበሩ ነገሥታት በተለያዩ መገልገያዎቻቸውና ቤተ መንግሥታቸው አካባቢ በብዛት ይጠቀሙበት እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው፡፡
እነዚህ ልዩ ልዩ መለያዎች በየዘመኑ በሚመጡ መንግሥታት መቀየራቸውና በሌላ መተካታቸው አይቀርም፡፡ መለያዎቹ ቢቀየሩም ትዝታዎችን መቀስቀሳቸው አይቀርም፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር መለያዎችን ከሚጠቀሙና የመለያ ጥቅምን ቀድመው ከተረዱ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት መቶ ዓመታት ትጠቀምባቸው የነበሩ ልዩ ልዩ መለያዎችን (ብራንዶች) የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ ሲከፈት ከቀረቡት መለያዎች መካከል የዘመነ ዳግማዊ ምኒልክ ይገኙበታል፡፡
ኢትዮጵያ በዘመኗ የነበሯትን ልዩ ልዩ መለያዎችን፣ ነገር ግን እየጠፉ ያሉትንና በሥራ ላይ እያገለገሉ የሚገኙትን መለያዎችን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ የዓውደ ርዕዩ አዘጋጅ ነዋሪነታቸው በስዊድን የሆነው አቶ ኤፍሬም በየነ ተናግረዋል፡፡
መለያዎቹ በመልዕክት ተቀባይና ላኪ መካከል ስሜታዊና ሥነ ልቦናዊ ግንኙነትን ለመገንባት ሲያገለግሉ መኖራቸውን የተናገሩት አቶ አፍሬም መተማመንና ቃል ኪዳንን ለማጠናከር ወሳኝ መሣሪያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
መለያዎቹ የሚናገሩት ቁም ነገርና የሚቆሙለት ዓላማ አላቸው፡፡ የሰዎችን ልብ ይነካሉ፣ እንዲሁም የታሪክ ባለቤት ናቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
‹‹ተዓማኒነት ያለው መለያ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፤›› ያሉት አቶ ኤፍሬም ሃይማኖትን ለማጠናከር፣ መልካም ሥራን ለማበረታት፣ አገዛዝን ለማጽናት እንዲሁም ሸቀጦችንና የመሳሰሉትን ለመሸጥና ለማስተዋወቅ ይረዳሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ብዙ ጊዜ ከስዊድን ወደ አዲስ አበባ ለሥራ በምመላለስበት ወቅት ወጣትነቴን የሚያስታውሱኝ፣ ትዝታዎቼን የሚቀሰቅሱብኝ የቀድሞ መለያዎችን የያዙ መጻሕፍትን ከየቦታው በማሰባሰብና የተሰባሰቡትን የቀድሞ መለያዎች ለእይታ እያቀረብኩ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የቀድሞ መሪዎች፣ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ጠንካራ መለያዎችን በመጠቀም፣ ተግባቦትን ለመፍጠር የሚያበረክቱትን ፋይዳ ጠንቅቀው የተገነዘቡ ሥልጡን ነበሩ ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ ልዩ ምልክቱም የአማርኛ ፊደላትና አንዳንዴም የውጭ ፊደላትን በማዋሃድ ከፍ ባለ ጥበብ የተሠሩ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
በዓውደ ርዕዩ ላይም እነዚህን ድንቅ የሆኑ፣ የተለያዩ መለያዎች ምሥልም የተግባቦት ዘይቤ አስደናቂ ክህሎት የተገለጸባቸው፣ ባልተወሳሰበ ግን ደግሞ ረቂቅነትና ሀቀኝነት በሚነበብት ጥበብ የተሞሉ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩ 29 የተለያዩ መለያዎች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ‹‹የወሎ ፈረስ›› የሚለው መለያ ይገኝበታል፡፡ ‹‹የወሎ ፈረስ›› በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበሩት አምስት ታዋቂ የትራንስፖርት ተቋማት አንዱ የነበረ ሲሆን፣ መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ደሴንና መቐለን በማቋረጥ መዳረሻውን አስመራ ያደርግ ነበር፡፡
ከወሎ ፈረስ ባሻገር፣ ማሞ ካቻ፣ ሳታየ፣ ሃጂ አብዱና አጎናፍር ይባሉ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በእነዚህ የጉዞ ተቋም ሥር የነበሩ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች በአገሪቱ ወጣ ገባ መልክዓ ምድሮች ሲጓዙ ማየት ከፍተኛ ተመስጦ የሚፈጥር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ጥንታዊ የምግብ ማቅረቢያ ቁሳቁሶች፣ የቤተ መንግሥት የመጠጥ ዋንጫዎች፣ የኢትዮጵያና የጂቡቲ የምድር ባቡር ድርጅት፣ የቀድሞው አንበሳ መድኃኒት ቤት እንዲሁም የአፄ ምኒልክ የመኪና ታርጋ ቁጥርና የመሳሰሉት ልዩ ትኩረትን የሚፈጥሩ የቀድሞ መለያዎች በዓውደ ርዕዩ ከቀረቡት መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡