በታምራት ደሴ (ዶ/ር)
በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የሚገኘውን ጀምቦሮ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤትን ለማሻሻል፣ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ይህ ተግባር በወረዳው አስተዳደርም ጭምር ይሁንታን ያገኘ ሲሆን፣ መላው የወረዳችንና የዞናችን ሕዝብ እንዲሁም በጎ ማድረግ የሚሹ ሁሉ እንደሚያግዙን እምነታችን ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርት ባልተጀመረበትና ባልተስፋፋበት ዘመን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብርሃንን ሊፈነጥቅ ተመሥርቷል፡፡ የጀምቦሮ (የዠምቦረ) አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደተቋቋመ ከታሪክ ማኅደሩ መረዳት ይቻላል፡፡
በ1962 ዓ.ም. ተጨማሪ የግንብ ክፍሎች ተገንብተው በርካታ ታዋቂ ተማሪዎችን ለውጤት አብቅቷል፡፡ ከሞህር፣ ከኧዣ፣ ከስልጢ፣ ከጌይታ እንዲሁም ከቸሃ ድንበር አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ አስተምሯል፡፡ የኔታ ተሰማ ታየ የእዚህን ዕውቀት ገላጭ ትምህርት ቤት መሠረት በመጣላቸው ይታወሳሉ፡፡ የኔታ ደርግ ‹‹መሣሪያ ደብቀሀል›› ብሎ የገደላቸው የዕውቀት አባታችን ናቸው፡፡ በእሳቸው እግር ሥር ሆነው ፊደል ከቆጠሩት የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች መካከል አቶ ዓለሙ ገሳ፣ አቶ ሰሊማ ኡመር፣ አቶ መድኅን ተሰማ፣ አቶ ዋቅነዳ ወገሬ፣ አቶ ጉዱ ወግባጋ (ገብረ ኢየሱስ ኃይለ ማርያም)፣ አቶ ዕውቀቱ መላን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኔታ ተሰማ መደርቾ አካባቢ ባለው ቤታቸው አቅራቢያ ዛፍ ሥር የጀመሩት ፊደል ማስቆጠር ወደ ዠንቦረ በመውሰድ ትምህርት ቤት እንዲመሠረት አድርገዋል (ብርሃነ ዓለሙ “ታንታዊ” 2013 ዓ.ም.)
ይህ በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊው የጉመር ጀንቦሮ ትምህርት ቤት በ1932 ዓ.ም. በካቶሊክ እምነት ተከታይና ካህን በነበሩት የኔታ ተሰማ በላቸው መሥራችነትና መምህርነት፣ በመደርቾ መንደር በመኖሪያ የጎጆ ቤታቸው አጠገብ በሚገኝ ዛፍ ሥር ተጀምሯል፡፡ በወቅቱ በጉራጌ ሀገረ ስብከት ካህን በነበሩት አባ ፍራንሶ ማርቆስ መሪነት በ1934 ዓ.ም. የቀድሞ ጉመር ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በነበረበት፣ አሁን ትምህርት ቤቱ በሚገኝበት ግቢ ውስጥ የዘመናዊ ትምህርትን መስጠት ጀመረ፡፡ ከጀምቦሮ ትምህርት ቤት በቅርብ ርቀት የሚገኘው ናደነ ቀበሌ የተወለዱት እኚህ አባት፣ ለትምህርት ቤቱ ከምሥረታው ጀምሮ ጉልህ አሻራቸውና በጎ ሥራቸው ሁልጊዜ በትውልድ ቅብብሎሽ መካከል የሚታወስ ነው፡፡
ከትምህርቱ በተጨማሪ በአሁኑ ‘Green Legacy Initiative’ እየተባለ የሚጠራው የአረንጓዴ ልማት አሻራ፣ ከመቶ ዓመት በፊት በጉራጌ ምድር አባ ፍራንሶ እንደጀመሩት ይወሳል፡፡ ለዚህም ማሳያ እሳቸው ያስተከሉት የፎረ ኸና ጥቅጥቅ ደን አንደኛው ነው፡፡
የዘመናዊውን ትምህርት በማስፋፋት ረገድ ደግሞ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በቸሃ አውራጃ የቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንደኛ ደረጃ፣ አሁኑ እምድብር አንደኛ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የቀድሞው ልዑል ዘርዓ ያዕቆብ የአሁኑ አባ ፍራንሷ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ፣ የራዘ ሥላሴ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የደብረትዩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የናደነ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የዠምቦሮ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የጌቶ ቋንጤ አንደኛ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የየቅመነ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ትምህርት ቤት፣ የምሁር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የገራን አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የወለኔ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የጉንችሬ አንደኛ ደረጃ የወሸዋሰር አንደኛ ደረጃና የጡማነ ዝግባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ናቸው፡፡
የጀምቦሮ ትምህርት ቤት ሥራ ከጀመረበት 1934 ዓ.ም. እስከ 1954 ዓ.ም. ድረስ ለአሥራ አንደ ዓመታት ከአንደኛ አስከ ስድስተኛ ክፍል እያስተማረ ቆይቷል፡፡ በ1955 ዓ.ም. ሰባተኛና በ1956 ዓ.ም. ስምንተኛ ክፍል ማስተማር ጀምሮ እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ ጀምቦሮ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተባለ መቆየቱም ይታወሳል፡፡ በ2000 ዓ.ም. ከዘጠነኛ እስከ አሥረኛ ማስተማር የጀመረው ትምህርት ቤቱ በ2006 ዓ.ም. እስከ 12ኛ ክፍል ማስተማር በመጀመር ላለፉት 80 ዓመታት ገደማ ለአገርም ጭምር በከፍተኛ ማዕረግ ያገለገሉ ምሁራንን አፍርቶልናል፡፡
የዛሬ 80 ዓመት ገደማ እንደተመሠረተ ታሪኩ የሚያስረዳው ይህ ትምህርት ቤት እኔን ጨምሮ በርካቶቻችን ለወግ ማዕረግ በቅተንበታል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች አንቱታን ያተረፉ ምሁራን ከእዚህ ትምህርት ቤት ወጥተዋል፡፡ ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን አገልግለዋል፣ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያገኙት የኢሲኤ ተወካይ፣ ጸሐፊና ደራሲ ገብረ የሱስ ኃይለ ማርያም የጀምቦሮ ውጤት ናቸው፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ አማኑኤል ተሰማ ላጫ (ኮሎኔል)፣ ስንታየሁ ገብረማርያም ወልደ ሐዋርያ፣ ብርሃኑ ወልደ ጊዮርጊስ (አየር መንገድ ኃላፊ)፣ ገብረ ፃዲቅ ወገሬ (የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ)፣ ዕውቀቱ መላ (የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና ኃላፊ)፣ አብራር ዓሊ (የእንስሳት ዶክተር)፣ ወልደ ገብርኤል ወልደ ዮሐንስ (የአየር ኃይል አባል/ኮሎኔል)፣ ክብሩ ብዛ (ሜዲካል ዶ/ር)፣ አምሣሉ ተረዳ (ዶ/ር)፣ ምኑቴት መንጀታ (ዶ/ር)፣ ፈቀደ ምኑታ (ዶ/ር)፣ ሙሉነሽ ንዥኖ (ሜዲካል ዶ/ር)፣ ታምራት ደሴ (ዶ/ር)፣ አባ ተሾመ ፍቅሬ (የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጸሐፊ) እና በጣም ብዙ ስማቸው ያልተጠቀሱ በእዚሁ ትምህርት ቤት ፊደል የቆጠርን ነን፡፡
የኔታ ተሰማ በላቸው (የመጀመሪያው መምህርና ርዕሰ መምህር የነበሩ ናቸው) እንዲሁም አባ ፍራንሷ ማርቆስ ለትምህርት ቤቱ መመሥረት ከፍተኛውን አበርክቶ የነበራቸው ናቸው፡፡ በመቀጠል አቶ ፍራንሲስ አትራጋ፣ አቶ ፍቅረ ኢየሱስ፣ ወ/ሮ ትንሳይ፣ አቶ ቲጂ ወልቀባ፣ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ፈረጃና ሌሎችም በቅደም ተከተል በርዕሰ መምህርነት ያገለገሉ ሲሆን ለአብነት መምህር ካሳ፣ መምህር ማርቆስ፣ መምህር ገዛኸኝ፣ መምህር ካሳ፣ መምህር ወልደ ተንሳይና መምህር ዳሞ እንድሪያስ የዠምቦረ ትምህርት ቤት የዘመናዊ ትምህርት የመጀመርያ መምህራን ናቸው፡፡ ልጅ አድነው ጨረቶ፣ አዝማች እንዳሸ፣ ገብረ ሐና ሙላስ፣ ዳሞ ጋጋር ይሮርሸ፣ ግራዝማች ሰይፉና አቶ ግርማ ፈለቀ በተለያየ ጊዜ የሕዝቡ ተወካይ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ምንም እንኳን የትምህርት ቤቱ አመሠራረት በአገር አቀፍ ደረጃ አንጋፋ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ቢሆንም፣ ከነበሩበት ጫና የተነሳ በሚፈለገው መጠንና ትምህርት ሚኒስቴር በሚፈቅደው መሠረት ደረጃ በደረጃ ማለትም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ መሰናዶ ትምህርት ባለማደጉ ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅግ ትልቅ አቅም የነበራቸው ተማሪዎች በወቅቱ በቅርበት የሚቀበላቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ተለያዩ የአገራችን ከተሞች እንዲሰደዱ ሆኗል፡፡ ዕድል የቀናቸው ከብዙ ጥቂቶቹ ትምህርታቸው ወደ ግቡ አድርሰው ትልቅ ደረጃ ቢደርሱም ገሚሶቹ እንደሚናገሩት ምንም እንኳ ለትምህርት ፍላጎት ቢኖራቸውም የሄዱበት ቦታ በወቅቱ የነበረባቸውን ጫና መቋቋም ባለመቻላቸው አያሌዎች ከትምህርት ገበታቸው እንደተፈናቀሉ ያስረዳሉ፡፡
ከረዥም ዓመታት በኋላ መንግሥት ካስቀመጠው የትምህርት ተደራሽነት ከማሳካት አንፃር፣ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ቢፈቀድም በወቅቱ ከነበረው አሻጥር ይህን አንጋፋ ትምህርት ቤት ዕድል ቢሰጠውም በወቅቱ ፈቃድ ለመስጠት ለሱፐር ቪዥን የተላከው ግብረ ኃይል ምንም እንኳን የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት እንደነ አዝ ከድር ኬርጋ የግል ቼካቸውን እስከ መስጠትና በበቂ ሁኔታ ግብዕት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ የላቦራቶሪ ግብዓቶች፣ የቤተ መጻሕፍት ግብዓቶች፣ ወንበሮች እንዲሁም፣ በወቅቱ ለትምህርት ደረጃ ያሟላሉ የተባሉትን ዕቃዎች ጭነው ቢሄዱም ትምህርት ቤቱ የሚጠበቅበትን ነገር ስላላሟላ ፈቃድ አይሰጣችሁም ቻው ብለው መኪናቸውን አስነስተው ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡ ከትምህርት ቤቱ ተወካዮች መልዕክት ከደረሳቸው በኋላ አዝ ከድርና ኮሎኔል መለሰ ወልደ ዮሐንስ ተነጋግረው በዚያው ዕለት ቤተሰቦቻቸውን ጥለው በአመሻሽ ጉዞ ወደ ሐዋሳ ለመሄድ እንደ ወሰኑ ትዝታቸው እያስለቀሳቸው አዝ ከድር ኬርጋ እንዲህ አጫውተውኛል፡፡
ጊዜው መስከረም 15 ቀን 1998 ዓ.ም. ነበር፡፡ ጉራጌ ከተለያየ አገሮች እንዲሁም ከየክፍለ ሀገር ጭምር አንድ ላይ ተሰብስቦ ፈጣሪውን የሚያመሠግንበትና ለቀጣይ ደግሞ ከአገር ሽማግሌዎች ምርቃት የሚቀበልበት ትልቁ የመስቀል በዓል ለማክበር ተሰባስቧል፡፡ በአገር ቤት ከቤተሰብ ጋር እንደነበሩ የደቡብ ትምህርት ቢሮ ሱፐርቪዥን ቡድን፣ የጀምቦሮ ትምህርት ቤት ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እንዲያድግ ፈቃድ ለመስጠት በጀምቦሮ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደ ከተመ መረጃ እንደደረሳቸውና አቅም በሚፈቅደው መሠረት ጥሩ ዝግጅት ተደርጎላቸው ወደ ሥራ እንደገቡና ውጤቱም ጥሩ እንደሚሆን ይጠባበቁ እንደነበርም አዝ ከድር ያስታውሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ከዚያም አጠቃላይ ያለውን ሁኔታ ቡድኑ ከገመገመ በኋላ መሟላት የነበረባቸው ሌሎች ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ ስላልተሟሉ አሁን ባለበት ሁኔታ መሥፈርቱን ትምህርት ቤቱ አላሟላምና ፈቃዱን አንሰጣችሁም በማለት ወደ መጡበት ይመለሳሉ፡፡
ኮሚቴዎቹ ግን በመነጋገር በዋናነት አልተሟሉም የተባሉትና ግዥ የተፈጸመባቸውን ደረሰኞች በመያዝ ሌሊቱን ተጉዘው ሐዋሳ ከተማ መስከረም 16 ጠዋት በመድረስ ከክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጋር በመነጋገርና ያሳለፉትን ውጣ ውረድ ሳግ በተሞላበት ለቅሶ በማስረዳት በልዩ ሁኔታ እንደተፈቀደላቸው አጫውተውኛል::
ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ 80ኛ ዓመቱ ለማክበር ሲሰናዳ ማየቱ እጅግ አስደሳች ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሕይወት ባይኖርም ወጣት ሳኒ (ነፍስ ይማር) የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ አንዱ ከግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር የፈጸመው ተግባር ማሳት ይገባል፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሲጀመር ትምህርት ቤቱ የክፍል እጥረት እንዳይገጥም ሳኒ ተጨማሪ ብሎኮች እንዲሠራ በማድረጉ እስከ ዛሬ በትውልዱ እያታወሰ ይኖራል፡፡
የጀምቦሮ ትምህርት ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ስመጥር እንዲሆን ካስቻሉት ተማሪዎች ውስጥ የፈታዘር ቀበሌ ተማሪዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለአብነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት ረዥም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ያፈራ፣ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ክፍል ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የአዋሽ ባንክ መሥራችና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም፣ የነጋዴው ባንክ ተብሎ የሚታወቀው የንብ ባንክ መሥራችና ፕሬዚዳንት ይጠቀሳሉ፡፡
እንዲሁም የተለያዩ ባንኮች የቦርድ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አመርጋ ካሳ፣ ወንድማቸው ደራሲና መምህር ጠና ካሳ፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ ኃላፊ የነበሩ፣ ከዚያም ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ አገሮች ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉ፣ ከፈታዘር እስከ ሳንፍራንሲስኮ የሚል መጽሐፍ ደራሲው ገብረ ፃዲቅ ወገሬና በአገር አቀፍ ደረጃ የጉራጌ ባህል በሚገልጽ ሁኔታ ኖርማልና እስፔሻል ክትፎ በኮባ ጥለስ በአሻሻት ቆጮ ፈር ቀዳጅ በመሆን ለሌላው ምሳሌ የሆኑ ወንድማማቹ ግርማና ግዛው መንጀታም ይወሳሉ፡፡
በተለይም ከጉራጌ አካባቢ ወደ ከተማ የሚመጡ ልጆች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለብዙዎች በከተማና ገጠር ትልቅ ኢንቨስትመንት ከሌሎች ጋር በመፍጠር የሥራ ዕድልን የፈጠሩ ናቸው፡፡
ባለምጡቅ አዕምሮው አቶ አብሽሮ አንግብ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ የወርቅ ሰዓት የተሸለመውና በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ኃላፊ የነበረው በኋላ ላይ አማርድ የሚባል የጉራጌ ፓርቲ መሥርቶ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ወቅት በደርግ የተገደለው የዚህ የጀምቦሮ ትምህርት ቤት ፍሬ ነበር፡፡
ከትምህርት ቤቱ ፍሬዎች አንዱ የሆነው የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እ.ኤ.አ. በ2012 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት፣ መቀመጫው በፈረንሣይ ካደረገውና በወ/ሮ ሎሬታ ኮይንተ ዳይሬክተርነት የሚመራው ስኩል ሄልፒንግ ፕሮጀክት ጋር በመጻጻፍ፣ ለትምህርት ቤቱ በተለይም ባዶ የነበረውን በተለይ የአይሲቲ ክፍል ኮምፒዩተሮች፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎች እንዲሟሉለት ከማስደረጉም በተጨማሪ፣ ለማጣቀሻነት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚረዱ መጻሕፍትን በወረዳው ለሚገኙ ሦስት ትምህርት ቤቶች (ለአረቅጥ፣ ለእንጀፎና ለችሜ) ጭምር እንዲረዱ የድርሻውን ተወጥቷል፡፡
ፈታዘር ቀበሌ በሰሜን አቅጣጫ እዣ ወረዳ፣ በደቡብ ውልባረግና ትርትሮ፣ በምሥራቅ እንጀፎ ቀበሌ እንዲሁም በምዕራብ ጀምቦሮ ቀበሌ የሚያዋስናት ሲሆን፣ በስሯ ያሞራ ዘር፣ የዤር፣ የግንድ፣ የሳሰራ፣ ከፊል ያንፋር፣ ከባሮ፣ ቃጫ፣ ይርቀተረ፣ ጫጮ፣ ቀጡቻ፣ መደርቾ የሚባሉ ቀበሌዎች ይገኙበታል፡፡
በወርልድ ቪዥን አማካይነት የተሠራውና አሁን መንግሥት ተረክቦት እያስተዳደረው ያለው የፈታዘር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ስምንተኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ በፊት ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ሄደው እንዲማሩ የሚገደዱበትን ሁኔታ ስለነበር፣ ያንን በማስቀረት ብዙዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ አንጋፋው የጀምቦሮ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ሚናው እጅግ የላቀ ነው፡፡
ከዚህ ትምህርት ቤት የወጡ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት መዋቅር፣ በግል ድርጅቶች፣ እንዲሁም በተሰማሩበት የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በመመሥረት ለብዙዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለመንግሥት የውጭ ምንዛሪ በማምጣትና በአገር ውስጥ ትልቅ መጠን ያለው ገንዘብ ግብር በመክፈል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የዕውቅናና ሜዳሊያ ተሸልመዋል፡፡
ሲጠቃለል፣ ትምህርት ቤቱ አሁን ያለበትን ደረጃ ለማሻሻልና በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎችን ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ 80ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማክበርና የትምህርት ቤቱን የመማሪያ ክፍሎች እጥረት ለመቅረፍ፣ ብሎም ደረጃውን ለማሻሻል በማሰብ ለሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ እንዲቀመጥ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው tdessie76@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡