Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ዕርምጃ ያስከተለው የብድር ወለድ ጭማሪ የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ይታሰብበት!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣው የገንዘብ ፖሊሲ በዋናነት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የወጣ ስለመሆኑ በሰፊው ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ ፖሊሲውን በማስመልከት ባንኩ በዝርዝር ያቀረበው ትንታኔና ትንበያም ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ በዚሁ የፖሊሲ ሰነድ ውስጥ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ያግዘኛል ብሎ ተፈጻሚ ይሆናሉ ብሎ ካስቀመጣቸው አስገዳጅ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ የንግድ ባንኮች የብድር ምጣኔ ላይ ገደብ መጣሉ ነው፡፡

በወጣው የገንዘብ ፖሊሲ መሠረት ሁሉም የንግድ ባንኮች በ2016 በጀት ዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ዕድገት ከ14 በመቶ በላይ እንዳያድግ ገደብ ተጥሎበታል።

እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች በእርግጥም የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚያግዙና የሚታመንበት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም የዋጋ ንረትን ለማርገብ ሊወሰዱ ከሚገባቸው ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ይስማሙበታል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔው ይህንን የሚያመላክት ቢሆንም፣ የገንዘብ ፖሊሲውን ተከትለው የወጡት ድንጋጌዎች በትክክል መሬት ላይ ለማውረድ ቀላል አይሆንም የሚል ሥጋት መጫሩ ግን አልቀረም፡፡ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በጥንቃቄ ካልተተገበሩና ከሥር ከሥር ክትትል የማይደረግ ከሆነ የዋጋ ንረቱን ሊያባብስ ይችላል የሚል አመለካከት መኖሩ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ 

ባለፉት ዓመታት የባንኮች ዓመታዊ የብድር ምጣኔ ዕድገት በአማካይ ከ30 በመቶ በመሆኑ፣ የመመርያው መተግበር የብድር ዕድገታቸውን ከግማሽ በላይ የሚቀንስና የትርፍ ምጣኔያቸው ይዘቀዝቀዋል የሚለው አስተያየት የተደመጠው ወዲያው ነበር፡፡ የብድር ገደቡ የሚያሳጣቸውን ጥቅም ለማካካስ ሌላ ዘዴዎች ሊጠቀሙ እንደሚችሉም ሲጠበቅ ነበር፡፡ እንደተገመተውም አልቀረም፡፡ ባንኮች የፖሊሲውን ጫና ለማካካስ ይረዳናል ብለው ያመኑበትን ዕርምጃ እየወሰዱ ስለመሆኑ እየተሰማ ነው፡፡ 

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አንዳንድ ባንኮች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን ከፍ በማድረግና ይህንኑ ውሳኔያቸውን የሚገልጽ መረጃ ለተበዳሪዎቻቸው እየሰጡ መሆኑ ነው፡፡

የብድር ወለድ ጭማሪ ያደረጉት ባንኮች እንደ የብድር ዓይነቱ ጭማሪው የሚለያይ ቢሆንም፣ አንዳንድ ባንኮች በአንድ ጊዜ እስከ ሁለት በመቶ ጭማሪ ያደረጉበት የብድር ዓይነት ስለመኖሩ ማወቅ ተችሏል፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ የተደረገው ጭማሪ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህም ማለት ተበዳሪዎቹ ለወሰዱት ብድር እስከዛሬ ሲከፍል ከነበረው ወለድ በላይ መክፈል እንዳለባቸው የሚያስገድድ ነው፡፡ ተበዳሪዎች ከውላቸው ውጪ በአስገዳጅነት ለብድር ወለድ ተጨማሪ ክፍያ የሚያስከፍላቸው በመሆኑ፣ ብድር የወሰዱበትን የኢንቨስትመንት ወጪ በዚያው ልክ ከፍ ያደርገዋል፡፡ 

የገንዘብ ፖሊሲውን ተከትሎ ባንኮች መውሰድ የጀመሩት የብድር ወለድ ጭማሪ ለብቻው የሚያስከትለው ያልታሰበ ወጪ ቀላል አይሆንም። በተለይም በብድር ተገዝተው ወደ አገር የሚገቡ ምርቶችን የመሸጫ ዋጋ ሊያንረው እንደሚችል አያጠራጥርም። የብድር ወለድ ጭማሪ በገበያ ላይ የሚፈጥረው የዋጋ ልዩነት ሄዶ ሄዶ የሚያርፈው ሸማቹ ላይ መሆኑም አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካወጣው የገንዘብ ፖሊሲ አንፃር ሲታይ ብዥታ የሚፈጥር ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን ያወጣበት ዋና ምክንያት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ መሆኑ በግልጽ ተቀምጦ ሳለ፣ ይኼው ፖሊሲ የዋጋ ንረት የሚያስከትል የብድር ወለድ ጭማሪ ካስከተለ የፖሊሲ መወጣት ትርጉሙ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ጭምር ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ፖሊሲ ሲያወጣና እንዲተገበር ሲያዝ፣ ባንኮች ውሳኔው ሊያሳጣቸው የሚችለውን ነገር አስበው ወደ ብድር ወለድ ጭማሪ ሊገቡ እንደሚችሉ ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብምና እንዲህ ያሉ አዝማሚያዎች በምን ዓይነት መንገድ መቆጣጠር እንደሚቻል መልስ ሊሰጥበት የሚገባም ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ፖሊሲውን የሚፃረር ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጭራሽ የዋጋ ንረቱን ሊያብሱ የሚችሉ ድርጊቶችን እንዴት ተቆጣጥሮ ፖሊሲን ሊያስፈጽም ይችላል? የሚለውም ጥያቄ መልስ የሚያስፈልገው ሆኗል፡፡ 

በመሆኑም የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ዕርምጃም ሆነ ይህንን ተከትሎ እየታየ ያለው የባንኮች የወለድ ጭማሪ ይዞ ሊያመጣ የሚችለው ያልታሰበ የዋጋ ንረት ከግምት በማስገባት በነካ እጁ መፍትሔ ማበጀት አለበት፡፡ ከሰሞኑ የባንኮች ውሳኔ አንፃር የብድር ወለድ ምጣኔ ዕድገቱ ኢኮኖሚው ላይ ሊፈጥር የሚችለውንም ጫና ደግሞ መፈተሽ ይጠበቅበታል፡፡ በእርግጥ የባንኮች የብድር መጠን ዕድገት በ14 በመቶ ብቻ እንዲገደብ የሚደረገው ለተወሰነ ጊዜ ነው ከተባለም፣ ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን በዚህ ፍጥነት ማሳደግስ ተገቢ ነው ወይ? የሚለውም ጉዳይ አብሮ መመርመር ያለበት ነው፡፡ 

ከዚህም ባለፈ ባንኮች ይህንን የብድር ወለድ ምጣኔ ዕድገት ተፈጻሚ የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገደቡን እስኪያነሳ ድረስ ነው? ወይስ በዚያው የሚቀጥል ጉዳይ ነው? የሚለውም ጥያቄም ቢሆን በአግባቡ መልስ ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በገንዘብ ፖሊሲ አማካይነት በባንኮች ላይ የተጣለው የብድር ገደብ ለአንድ ዓመት ብቻ የሚፀና በመሆኑ፣ ለጊዜያዊ ገደብ ዘላቂ የብድር ወለድ ምጣኔ መጨመር ተገቢና ምክንያታዊ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለሆነም የሰሞኑ የባንኮች የብድር ወለድ ጭማሪ የበለጠ የዋጋ ንረቱን እንዳያባብሰው ትኩረት ሰጥቶ መመርመር እንደሚገባ አመላካች ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ተበዳሪዎች መጀመርያ ከገቡት ውል ውጪ ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔ መጨመር ይችላሉ አይችሉም? የሚለው ጉዳይ ራሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ምናልባትም አዲስ ብድር ላይ የብድር ወለድ ጭማሪ ማድረጉ ትክክል ነው ቢባል እንኳን፣ በነባር ብድር ላይ የወለድ ጭማሪ ማድረግ ምክንያታዊ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ በተጨማሪም ባንኮች የሚያደርጉት የብድር ወለድ ጭማሪ የዋጋ ንረት የማስከተል አቅም ያለው በመሆኑ ተናቦና ተማክሮ መሥራት የግድ ይሆናል፡፡ እንደ ሸማች የዋጋ ንረቱን የሚቀንሱ መረጃዎች የሚፈልጉ በመሆኑ፣ ከዚህ በተፃራሪ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ወቅቱን ያገናዘቡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ቢሆን ባንኮቹ ሳይጎዱ፣ እሱም ያወጣውን ፖሊሲ ለማስፈጸም ሚዛናዊ ሊሆን የሚችል ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት