Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀሐይ ባንክ የአጭር ጊዜ ብድር የሚሰጥበትን የክሬዲት ካርድ አገልግሎት ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሌሎች ባንኮች በተለየ በጥቂት ባለአክሲዮኖች ተቋቁሞ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው ፀሐይ ባንክ ለደንበኞቹ የአጭር ጊዜ ብድር መስጠት የሚያስችለውን የክሬዲት ካርድ አግልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ፡፡ 

ባንኩ አዲስ የጀመረውን አገልግሎት በተመለከተ እንዳስታወቀው በክሬዲት ካርድ የሚሰጠው ብድር የመመለሻ ጊዜው ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ይሆናል፡፡ 

የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን ጨምረው እንደገለጹትም፣ የክሬዲት ካርድ ብድር መመለሻ ጊዜው እንደ ደንበኞች የመመለስ አቅምና ፍላጎት እየታየ አገልግሎቱ እንዲራዘም የሚደረግበት አሠራር ይኖራል፡፡ የብድር አከፋፈሉም የደንበኞችን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ የሚሰላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ባንኩ ይፋ ካደረገው የክሬዲት ካርድ በተጨማሪ ከወለድ ነፃ የዴቢት ካርድና ከወለድ ነፃ የክሬዲት ካርድ አገልግሎቶችንም አብሮ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ 

ፀሐይ ባንክ በኢትዮጵያ ገና በስፋት ያልተጀመረውና በደንበኞች ጥቅም ላይ ያልዋለውን የክሬዲት ካርድ አገልግሎት ማስተዋወቁ የተለየ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል፡፡ 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ፀሐይ ባንክ ያስተዋወቀው ፀሐይ ክሬዲት ካርድና ፈጂር የግዥ ካርድ አገልግሎት፣ ከተለመደው የዴቢት ካርድ የሚለየው ደንበኞች በተፈቀደላቸው የብድር መጠን የብድር ዘመኑ እስኪያበቃ ጊዜ ድረስ እንደፈለጉ መጠቀም የሚያስችላቸው በመሆኑ ነው፡፡ 

ለዚህ የብድር አገልግሎት ደንበኞች ምንም ዓይነት የብድር ማስያዣ የማያስፈልጋቸው ሲሆን የሚከፍሉት የአገልግሎት ክፍያም ተመጣጣኝ ነው ተብሏል፡፡ 

በተለይ የባንኩ የክሬዲት ካርድ አገልግሎት ደንበኞች የሚገጥማቸውን ጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት የሚቀርፍ ከመሆኑም ሌላ ለግብይት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በሚፈልጉበት ጊዜ ተጠቅመው ቆይተው እንዲከፍሉ የሚያስችላቸውንም ዕድል እንደሚሰጥ የክሬዲት ካርዱ የሚሰጠውን ጥቅም በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

እንዲህ ያሉ አጫጭር ብድሮች በብድር ለማግኘት ዕድል ሳያገኙ ለቀሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ እስካሁን ለትልልቅ ተበዳሪዎች ከሚሰጠው ብድር ሌላ ብዙዎች ሊቀጠሙበት የሚያስችል አሠራርን ስለሚፈጥር የባንክ ተበዳሪዎችን ቁጥር ለማሳደግም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል፡፡ 

በክሬዲት ካርድ የሚሰጠው የብድር መጠን ደንበኞች ባላቸው ወርኃዊ ገቢና የመበደር አቅም ላይ የተመሠረተ እንደሚሆንም ታውቋል፡፡ 

ባንኩ ይህንን የብድር አገልግሎት የሚጀምረውም በቂ የቴክኖሎጂ ዝግጅት በማድረግና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችላቸውን ፈቃድ አግኝቶ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ፀሐይ ባንክ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው 30 ቅርንጫፎችን በመክፈት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ አሁን የቅርንጫፎቹ ቁጥር 82 ደርሰዋል፡፡ 

የባንኩ ደንበኞችም ቁጥር ከ280 ሺሕ በላይ መድረሱም ታውቋል፡፡ ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ ይዞት የተነሳው በ2.8 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታልና 737 ሚሊዮን ብር ሲሆን አሁን የተከፈለ ካፒታሉ 1.1 ቢሊዮን ብር መድረሱንና በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ለማድረስ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን ደግሞ 3.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም 2.3 ቢሊዮን መድረሱም ተገልጿል፡፡ 

ባንኩ በአንድ ዓመት የደረሰበት ደረጃ ውጤታማ የሚባል መሆኑን የገለጹት አቶ ያሬድ ይህንን ውጤት የበለጠ ለማሳደግ ተጨማሪ አዳዲስ አገልግሎቶችንም የሚጀምር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ፀሐይ ባንክ ከሌሎች ባንኮች በተለየ 377 ባለአክሲዮኖችን ይዞ የተቋቋመ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች