Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በክልላችን በስሜት የሚነዳ ማኅበረሰብ  የለም›› ነስሪ ዘከሪያ፣ የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር

በሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሥራ የጀመሩት በ1989 ዓ.ም. ነበር፡፡ ለ25 ዓመታት ባገለገሉበት ተቋም ከምልምል ፖሊስነት ተነስተው እስከ ኮሚሽነርነት መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡ የመኮንንነት ኮርስ በ1991 ዓ.ም. የተሳተፉት የዛሬው የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከሪያ፣ በተለያዩ ጊዜያት በፖሊስ ሳይንስና በመደበኛ ትምህርት ማለፋቸውንም ያስረዳሉ፡፡ በሊደርሺፕ ማስተርስ ዲግሪ ያገኙት ኮሚሽነር ነስሪ በፒስ ኤንድ ሴኪዩሪቱ ለሁለተኛ ማስተርስ እየተማሩ ሲሆን፣ በኮሚሽነርነት ማገልገል ከጀመሩ ሦስት ዓመታት ተጠግተዋል፡፡ በሐረሪ ክልል ስላለው የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ፣ እንዲሁም ወንጀል የመከላከልና ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ የሰጡበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በክልሉ ያለው የወንጀል መከላከል እንቅስቃሴ ምን ይመስላል፡፡ አጠቃላይ ፖሊሳዊ አገልግሎቱን ቢገልጹልን?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- የሐረሪ ክልል የፌደራሉን መንግሥት ካዋቀሩ ክልሎች አንዱ ነው፡፡ በክልሉ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ከተቋቋሙ ተቋማት አንዱ ደግሞ የፖሊስ ኮሚሽናችን ነው፡፡ ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ሥራውን የሚያከናውነው ደግሞ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ፣ በዚህ የተነሳም በሥራዎቻችን ካለፈው ዓመት አንፃር ዘንድሮ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበናል፡፡ ኅብረተሰቡን በሁለት ዓይነት አደረጃጀቶች ነው የምናሳትፈው፡፡ አንዱ የማኅበረሰብ አቀፍ ፓትሮሊንግ አደረጃጀት ነው፡፡ ይህ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው የክልል መዋቅር የተዘረጋ ነው፡፡ ሁለተኛው ገለልተኛ አማካሪ ቡድን ነው፡፡ ይኼኛው ለፖሊሳዊ ሥራ ጠቃሚ የሆኑ ስትራቴጂዎችን፣ የፖሊስን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየትና ከፖሊስ ጋር በመመካከር አቅጣጫ የማስቀመጥ ሚና የሚወጣ ነው፡፡

ኅብረተሰቡን የምናሳትፍበት የፓትሮሊንግ አደረጃጀት እስከ ቤተሰብ የሚወርድ ነው፡፡ በክልል ደረጃ ወደ 534 ብሎኮች አሉን፡፡ አንድ ብሎክ እስከ 50 አባወራ ቤተሰብን የያዘ ማለት ሲሆን፣ ይህም በከተማ ደረጃ ያለ ነው፡፡ በገጠር ደግሞ ወደ 139 መንደሮች አሉ፡፡ በእነዚህ መንደሮችም የቤተሰብ አደረጃጀቶች አሉን፡፡ በአጠቃላይ በከተማ 13,500 ያህል የቤተሰብ ፖሊሶች ነው ያሉን፡፡ በገጠር ደግሞ 7,600 የቤተሰብ ፖሊሶች አሉን፡፡ እነዚህ ወገኖች ከፖሊስ ጋር ተደራጅተው አካባቢያቸውን በመጠበቅ፣ ለፖሊስ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በመስጠት፣ ቀላል ማኅበራዊ ችግሮችን በመፍታት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው ያሉት፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ እንኳን ብናይ የፖሊስ ሥራን የሚያጨናንቁ ቀላል የሚባሉ 14,276 ኬዞች በእነሱ በኩል ዕልባት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ወደ 6,539 ማኅበራዊ ግጭቶችን በእነሱ በኩል እንዲፈቱ አድርገናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የሕዝብን ሰላም የመጠበቅና የማረጋገጥ ሥራዎችን ከእኛ ጋር ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

ከእነዚህ ባለፈም መንፈሳዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ሕዝባዊ በዓላት በሚኖሩበት ጊዜ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ከፊት ሆነው ነው ሰላም የማረጋገጥ ሥራ ሲሠሩ የነበረው፡፡ ይህን በማድረጋቸውም ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በዓላቱ በክልላችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቁ ማድረግ ችለናል፡፡ የክልሉ ፖሊስ በራሱ መንገድ ወንጀልን በመከላከል ረገድ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የፓትሮሊንግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ነው የሚሠራው፡፡ ባለፈው ዓመት 454 የስርቆት ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን፣ ሁሉም ማለትም 454 ያህል ወንጀል ፈጻሚዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ 318 የሚሆኑት በዚያው በወንጀሉ መፈጸሚያ ቦታ በፓትሮል ሥራ ላይ በነበሩ አባሎቻችን እጅ ከፍንጅ የተያዙ ናቸው፡፡ በ2015 ዓ.ም. የስርቆት ወንጀሉ አፈጻጸም ራሱን የመቀያየር መልክ የነበረው ቢሆንም፣ ነገር ግን በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሥራ በማከናወን አብዛኞቹን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አውለናል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለወንጀሎች መንስዔ ይሆናሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ነገሮችን ለምሳሌ ወጣቶች አምራች ዜጋ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ሺሻ ማጨሻ፣ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀሚያና ሌሎች የሱስ ማዘውተሪያ የሆኑ ቦታዎችን ጥናት በማድረግ ዕርምጃ ወስደናል፡፡ በዚህም ወደ 128 ቦታዎች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ 128 የሺሻ ዕቃዎች እንዲወገዱ አድርገናል፡፡ ከአደገኛ ዕፅዋት ጋር በተገናኘ በ2015 ዓ.ም. ከሌላው ጊዜ በተለየ ፍንጮች በማየታችን ለጉዳዩ በሰጠነው ልዩ ትኩረትና ክትትል ቢያንስ 449 ኪሎ ግራም የሚሆን አደገኛ ዕፅዋት በመያዝ እንዲወገድ አድርገናል፡፡ ዕፅዋቱን ሲያመርቱ፣ ሲያዘዋውሩና ሲጠቀሙ የነበሩ 79 ግለሰቦችን ይዘን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑም አድርገናል፡፡ ከአደገኛ ዕፅ ጋር በተገናኘ ወደ 330 ኪሎ ግራም በገጠር አካባቢ በእርሻ ላይ በቅሎ የተገኘና እንዲወገድ የተደረገ ነው፡፡

በኮንትሮባንድ መከላከል ሥራ በዋናነት ኃላፊነቱ በሕግ የተሰጠው የፌደራል ፖሊስ ቢሆንም፣ ሆኖም በክልሉ የሚፈጸሙትን መከላከል ላይ በቅንጅትና በጋራ ነው የምንሠራው፡፡ እነሱ በማይደርሱባቸው ወይም በማይሸፍኗቸው አንዳንድ ቦታዎች ባደረግነው ክትትል ግምታቸው 57.1 ሚሊዮን ብር የሆነ አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫና ሌሎችም ዕቃዎች ተይዘው ለመንግሥት ገቢ ተደርገዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከተሰጠው አንዱ ሥራ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን መቆጣጠር ነበር፡፡ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር ለማድረግ፣ እንዲሁም ያላግባብ ለመጠቀም መሞከር ላይ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ አቅጣጫ በተሰጠው መሠረት ጥብቅ ክትትል አድርገናል፡፡ በዚህም 39,807 ሊትር ቤንዚን በሕገወጥ መንገድ በችርቻሮ ሲገበያይ ይዘናል፡፡ በተጨማሪም 6,600 ሊትር ናፍጣ ይዘናል፡፡ ይህ ሁሉ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ያሉ ሥራዎችን እንጂ ከዚያ በኋላ በሕገወጥ ነዳጅ ግብይት ቁጥጥር የተያዙ ኬዞችን አይጨምርም፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድ 3.03 ሚሊዮን ብር፣ ወደ 60,742 ዶላር፣ እንዲሁም ሌሎች የገንዘብ ኖቶችን በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ይዘን ገቢ አድርገናል፡፡ ከሰዎች ሕገወጥ ፍልሰትና ዝውውር ጋር በተገናኘ ደግሞ፣ በአብዛኛው ክልላችን ለሕገወጥ ሰዎች ዝውውር መሸጋገሪያነት ተጋላጭ ነበረ፡፡ ይህ መልኩን እየለዋወጠ ወጣቶችን በአመዛኙ ሰለባ የሚያደርግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል አሁን ግን አንዳንድ የክልላችን ገጠራማ አካባቢዎችን መነሻ እያደረገ ይገኛል፡፡ ወደ ዓረብ አገሮች የማሸጋገር እንቅስቃሴዎች አጋጥመውናል፡፡ በዚህም 782 ሊኮበልሉ የነበሩ ሰዎችን የያዝን ሲሆን፣ እነሱን ድንበር ለማሻገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወደ 24 ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችም ተይዘው ለሕግ ቀርበዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የወንጀል መከላከል ሥራዎቻችን እኛ ከደረስንባቸውና ለፖሊስ ሪፖርት ከተደረጉ ወንጀሎች አንፃር፣ አምና ካስመዘገብነው አፈጻጸማችን በክልሉ የሚመዘገበው የወንጀል አኃዝ በ8.42 በመቶ ቀንሷል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ዓመቱ ጠንካራ የወንጀል መከላከል፣ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ የመጠበቅ ሥራ የተሠራበት ነው ማለት እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሕገወጥ ነዳጅ ግብይትን በተመለከተ በትልልቅ ሥራ በማይሠሩ ፔጆ መኪኖች ነዳጅ በመቅዳት ለባለሦስት እግር ባጃጅ መኪኖች በውድ የመሸጥ ድርጊት እንደሚፈጸም ሰምተናል፡፡ ይህን መሰል ድርጊቶችን ይዛችኋል?    

ኮሚሽነር ነስሪ፡- አንዱ የአፈጻጸም መንገድ የተባለው መሆኑን አግኝተናል፡፡ ከዚህ በፊት የከተማ ታክሲ ይሠሩ የነበሩ ፔጆዎች ከገበያ እየወጡ ነው፣ ባጃጆች አሁን በዝተዋል፡፡ የነዳጅ እጥረት ባጋጠመ ጊዜ ግን በፔጆ መኪኖች እየቀዱ የመሸጥ አዝማሚያ ነበር፡፡ በውኃ ፕላስቲክ እየቀዱ መንገድ ዳር የሚሸጡም ነበሩ፡፡ በበርሜልና በጄሪካን እየቀዱ ሱቅ ውስጥ እንደ መደበኛ ሸቀጥ የመሸጥ አዝማሚያም ነበር፡፡ እነዚህንም ቢሆን በቁጥጥር ሥር አውለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ረገድ ክልሉ የወንጀሉ ምንጭ ነው ወይስ መሸጋገሪያ ብቻ?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- ለሁለቱም መነሻ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች መሸጋገሪያ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን አሁን ግን በአንዳንድ የክልሉ ገጠር አካባቢዎች ወጣቶችን የማስኮብለል አዝማሚያ አለ፡፡ ከሐምሌ ወር ወዲህ ይህን የበለጠ የሚያረጋግጡ መረጃዎች አግኝተናል፡፡ በኤረር ወረዳ ለምሳሌ ከ20 በላይ ታዳጊዎችን መልምለው ወደ ዓረብ አገር ያሻገሩ ሰዎች መኖራቸውን አውቀናል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ወደ ስድስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል፡፡ ከገጠር እየመለመሉ አምጥተው በድብቅ ማቆያዎች ያስቀምጣሉ፡፡ ሰዎቹን ከቦታ ወደ ቦታ የሚያሸጋግሩባቸው ተባባሪ የባጃጅ ተሽከርካሪዎችም አሏቸው፡፡ በገጠር ደግሞ ወጣቶችን ለሕገወጥ ስደቱ የማሳመንና የመመልመል ሥራ የሚሠሩም አሉ፡፡ እነዚህ በአጠቃላይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው በቅርብ ሰሞን በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ክልላችን እንደ ከዚህ ቀደሙ የወንጀሉ መሸጋገሪያ ብቻ ሳይሆን የወንጀሉ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን የሚያመለክቱ በቂ መረጃዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ድንበር ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን ድንበር ጠባቂዎች ሲገድሏቸው መታየቱ ዓለምን አሳዝኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጉዳት የደረሰበት ወጣት በዚሁ ሐረሪ ክልል ሲታከም መቆየቱን ሰምተናል፡፡ ሕገወጥ ስደትና የሰዎች ዝውውር እንዲገታ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- በዚህ ረገድ ማድረግ የሚበጀው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ነው፡፡ ወጣቶችን እያስኮበለሉ ያሉት ወገኖች አቀራረባቸው በጣም የሚያማልልና ማንንም ሰው ለስደት የሚያጓጓ ነው፡፡ ለዚህ ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ደግሞ የወንጀሉን ጉዳት መንገርና ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በወንጀል ፈጻሚዎቹ ላይ የሚወሰደውን ሕጋዊ ዕርምጃ ጠንከር ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሩ በፖሊስ ክትትልና ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም በሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ ነው ሊገታ የሚችለው፡፡ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው፡፡ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ ማኅበራዊ ጉዳይና ሌሎችም ተቀናጅተው ቢሠሩ የተሻለ ይሆናል፡፡ ከግንዛቤ ፈጠራ፣ ከቅጣት ማክበድ፣ እንዲሁም ከቅንጅት ሥራዎች በተጨማሪ ለወንጀሉ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን ማድረቅም ይጠይቃል፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የሥራ ዕድል ፈጠራና የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብሮች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ሥራ ጠባቂነትና ሥራ ማማረጥን ወጣቱ በማስቀረት በአገሩ ሠርቶ መለወጥ እንደሚችል አምኖ መትጋት አለበት፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ቢሠራ መንግሥትም አቅም በፈቀደ መንገድ ድጋፍ ያደርጋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አገር ብዙ አለመረጋጋትና ግጭት ባለበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ በሐረሪ ክልል ግን አንፃራዊ የሰላምና ፀጥታ መረጋጋት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ከምን የመጣ ነው? ይህን አስጠብቆ ለማስቀጠል ምን ታስቧል? በክልሉ ሌሎች ቢጋሩት የምትሉት ልምድስ ምንድነው?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- ትልቁ ነገር በክልላችን ኅብረተሰቡ የመከባበርና የአብሮነት ስሜቶች ከድሮም የነበረው መሆኑ ነው፡፡ ይህን አሁንም ድረስ አስቀጥሎታል፡፡ በክልላችን በስሜት የሚነዳ ማኅበረሰብ አይደለም ያለው፡፡ ፖሊስም፣ ሕግ አስከባሪም ሆነ መንግሥትም ከኅብረተሰቡ ጋር የፈጠሩት ቁርኝት ያመጣው ውጤት ነው፡፡ ኅበረተሰቡ ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ ያለውን ፍላጎት ማታ በየአካባቢው በሚያደርገው ጥበቃ ማየት ይቻላል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በተለያዩ መንገዶች የሚነዙ አሉባልታዎችን፣ ውዥንብሮችንና ሐሰተኛ መረጃዎችን ተቀብሎ ምላሽ የሚሰጥ ማኅበረሰብ አይደለም በክልላችን ያለው፡፡ ለዚህም ነው የፍቅር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ከተማ ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው፡፡ የፀጥታ አካሉም ይህን ተጠቅሞ ከኅብረተሰቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራቱ የመጣ ውጤት ነው፡፡ የፀጥታ አካሉ የተሟላ፣ ጠንካራ በመሆኑ ወይም አስፈላጊውን ሥራ በማጠናቀቁ የመጣ ሳይሆን የጋራ ውጤት ነው፡፡ ችግሮችን ገና እንደተፈጠሩ እዚያው በዚያው የመፍታት ባህል ስላለ ነው፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሔርን ከብሔር የማጋጨት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ አዝማሚያዎች አሁንም ግን የሉም ማለት አይቻልም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህን ዓይነት ችግር የመፍጠር ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ያን ነገር ተቀብሎ የሚያስተናግድ ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥትም የፀጥታ አካሉም በመሆኑ ለዚያ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ በእኛ ክልል የተገኘው ፀጥታ ውጤት በአብዛኛው የኅብረተሰቡ ነው፡፡ ሌላ ቦታም ቢሆን ኅብረተሰቡ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህል እንዲኖር ነው የምንመክረው፡፡ ችግሮች ሳይባባሱ በቶሎ የመፍታት ባህል እንዲኖር ነው የምንለው፡፡ የፀጥታ ኃይሉ የነበረበትን ችግር ቀርፎ ከማንም ወገንተኝነት በፀዳ መንገድ ሥራውን በመሥራቱ የመጣ ነው፡፡ የፀጥታ አካሉ ለአንዱ ወገን ወገንተኛ ሆኖ የሚሠራ ከሆነ ችግሮች ይባባሳሉ፡፡ በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊም በዓላት ኅብረተሰቡን አሳትፈን ከወገንተኝነት በፀዳ ሁኔታ ስለሠራን የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ይህንን በክልላችን ውጤት ያመጣ ተሞክሮ መውሰድና መጠቀም ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ የእሳት አደጋ በሐረር ከተማ ደርሷል፡፡ ጉዳዩን እየመረመራችሁት ከሆነ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ የሆነ ልባዊ ሐዘን መግለጽ እንፈልጋለን፡፡ ጥሩ ነገሩ በንብረት ላይ እንጂ በሰው ሕይወት ላይ አንዳችም ጉዳት አልደረሰም፡፡ እንደ መንግሥት ይህን ጉዳይ አጣርቶ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ እኛም ጉዳቱ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ እንዲቆም የሠራናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ ሆኖ የአደጋው መንስዔ ይኼ ነው ለማለት ገና መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ያ የምርመራ ውጤት ሲደርስ ለሕዝቡ እናሳውቃለን፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ በርካታ አሉባልታዎች ነበሩ፡፡ ከእውነት የራቁና ሐሰተኛ ነገሮች ሲወሩም ነበረ፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ከኅብረተሰቡ ጋር ባደረግነው ምክክርና ቅርርብ አረጋግጠናል፡፡ የመንግሥት አካል ሆኖ ይህን መሰል የእሳት አደጋ የሚፈጽም አለመኖሩን ተማምነናል፡፡ ዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚፈልግ መንግሥት አለመኖሩን አስረድተናል፡፡ ከፌደራል የመጡ ባለሙያዎችን ጭምር በማሳተፍ ጉዳዩን የማጣራት ሥራ ሠርተናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ ነው ያለው፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በፀጥታ አካልም ሆነ በመንግሥት ደረጃ መደረግ ያለበትን ነገር እንደምናደርግ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ አደጋዎች እንደገና እንዳይደርሱ ምን ዓይነት ዝግጅት አለ በእናንተ በኩል?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- የመጀመሪያው ነገር ሰዎች ለአደጋ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ነገሮች መራቅ ነው ያለባቸው፡፡ የእሳትና የድንገተኛ አደጋ መከላከሉ በእኛ በፖሊስ ኮሚሽን ሥር ነው ያለው፡፡ ይህ ክፍል በቂ አቅም እንዲኖረው የማድረጉ ሥራ በዕቅድ ተይዞ በሰፊው እየተሠራበት ነው ያለው፣ ዝግጁነቱ አለን፡፡ የእሳትና የአደጋ መከላከል ጽሕፈት ቤቱን በሰፊው እየገነባን ነው፡፡ በርካታ መገልገያዎች ያሉት ማዕከል እየሠራን ነው፡፡ ትልቁ ችግር የውኃ እጥረት ነው፡፡ ያለችዋ መኪና ውኃ ሲያልቅባት ከሌላ ቦታ ሄዳ ለመቅዳት ስለምትገደድ፣ ሄዳ እስክትመጣ ድረስ የአደጋው ጉዳት ሊሰፋ ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ በኮሚሽናችን ቅጥር ግቢ ውስጥ በትንሹ ለ50 መኪና የሚሆን የውኃ ማጠራቀሚያ ታነከር እየተሠራ ነው፡፡ አደጋ ሲከሰት ምላሽ ለመስጠት የሚወጣውን የሳት አደጋ መከላከያ መኪና፣ ሌላ መኪና እንዲከተለው የማድረግ ሥራም ጀምረናል፡፡ በዋናነነት ደግሞ ኅብረተሰቡ እሳት አደጋ በሚከሰት ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አደጋ መከላከያዎችን ከቅርበት እንዲያሟላ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፡፡ እሳት የሚያባብሱ ቁሳቁሶችን ከሌሎች ነገሮች ጋር ቀላቅሎ ማስቀመጥ የሚያስከትለውን ችግር ግንዛቤ ለመፍጠር እየሞከርን እንገኛለን፡፡ ቅድመ መከላከል ላይ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ እሳት አደጋ መከላከሉ አሁን በዳይሬክተር ደረጃ ነው ያለው፡፡ የሰው ኃይሉን ማጠናከር ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ አብሮ ቁሳቁሶችን ማሟላት ይጠይቃል፡፡ ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- የፖሊስ ቁጥርን ለማብዛት መታሰቡን ሰምተናል፡፡

ኮሚሽነር ነስሪ፡- ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት የሚቻለው በሰው ኃይል ነው፡፡ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚቻለውና ወንጀልን መከላከል የሚቀለው የሰው ኃይል ቁጥርን በመጨመር ነው፡፡ በቅርብ ተጨማሪ ኃይል እናስመርቃለን፡፡ አንድ ፖሊስ ምን ያህል ሰው ማገልገል አለበት የሚለው ስታንዳርድ አለን፡፡ እሱ ላይ በሒደት ለመድረስም ጥረት እናደርጋለን፡፡ በቁጥር ወደ 500 አባላት እንጨምራለን፡፡ ተመርቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ቢያንስ አሁን ያለውን የክልላችን ፖሊስ ኃይል ከ47 እስከ 50 በመቶ ያሳድግልናል፡፡ ይህ ብቻውን ግን በቂ አይሆንም፡፡ የምንገነባው ጠንካራ የወንጀል መከላከልና የፖሊስ ሥራ የሚሠራ ኃይል መሆን አለበት፡፡ በሥነ ምግባር፣ በዕውቀትም ሆነ በክህሎት ብቁ የሆነ የሰው ኃይል መገንባት ትኩረት ከሰጠናቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

ከምናስመርቃቸው አዳዲስ የፖሊስ ኃይል አባላት በተጨማሪ፣ የወንጀል አፈጻጸም ሥልቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጡና እየተወሳሰቡ ስለመጡ ያለውን ነባር የሰው ኃይልም በሥልጠና ብቃት የመገንባት ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ በትምህርትና በሥልጠና ረገድ በፖሊስ ተቋማት በዲግሪና በማስተርስ፣ እንዲሁም በሲቪል ሙያ ትምህርቶች የሚማሩ ሰዎች አሉ፡፡ በተቋም ደረጃ የፖሊስ መኮንንነት ዕድገት በመስጠት የምናበቃቸውም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሐረሪ ክልል ፖሊስ ባልደረቦች የሚለብሱት የደንብ ልብስ እንኳን እንደሚቸገሩ ነግረውናል፡፡ ይህ ከምን የመጣ ነው?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- እንዲህ ዓይነት ችግሮች የመጡት በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ አንድ ፖሊስ በመደበኛነት በየዓመቱ ማግኘት ያለበትን የደንብ አልባሳትና ትጥቅ ያገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም እንጠቀምበት የነበረው የፖሊስ የደንብ ልብስ በአገር ደረጃ እንዲቀየር ተባለ፡፡ ይህን ለመቀየር ደግሞ ምርቱ የሚገኘው ከአንድ አምራች በመሆኑ በጊዜ ገደቡ ሊደርስልን አልቻለም፡፡ ተቋሙ የአገሪቱን ፖሊስም ሆነ የመከላከያን የደንብ አልባሳት የሚያዘጋጅ ስለሆነ፣ የኮሚሽናችን ባልደረቦች ማግኘት በሚገባቸው ጊዜ አልባሳቱን አላገኙም፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜ ሒደት ችግሩ ተቀርፏል፡፡ አንድ ዙር የዘለላቸው ባልደረቦች ቢኖሩም በሒደት ጨረታ ወጥቶ ግዥ ተከናውኖ ተሟልቶላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕፃናት (ታዳጊ ጥፋተኞች) ማቆያ ቦታን በተመለከተ ምን እያሰባችሁበት ነው?

ኮሚሽነር ነስሪ፡- ከወላጆች ወይም ከትልልቆች ጋር የሚመጡ ታዳጊ ጥፋተኞችን ለይቶ የማቆያ ሥፍራ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ሠርተናል፡፡ ይህ በእርግጥ በአገር ደረጃ ያለ ችግር ነው፡፡ የእኛም የተሟላ ነው ባንልም ቦታ ለመገንባት ጥረት አድርገናል፡፡ ሴቶችና ወንዶች በአንድ ግቢ የማቆየት ሁኔታ እንዳይኖር ለማድረግ፣ ሕፃናት ማቆያን ለብቻው የሚያደርግ ዲዛይን ተሠርቶ ተገንብቷል፡፡ ቤቱ አለ ነገር ግን በተሟላ ሁኔታ አገለግሎት ላይ ልናውለው አልቻልንም፡፡ በ2012 ዓ.ም. አካባባቢ በተፈጠረ የአንድ አካባቢ ግጭት ምክንያት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ቦታ እስኪያገኙ ድረስ በሚል አማራጭ በማጣት በዚህ ቦታ እንዲቆዩ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ቤታቸው እየተገነባ በመሆኑ ለሕፃናት የተከለለውን ቦታ ለቀው የሚወጡ ይሆናል፡፡ በኮሚሽን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በየወረዳው ባሉ ማቆያዎችም ራሱን የቻለ ማቆያ እንዲገነባ እያደረግን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጉብኝት በተደረገ ወቅት አቅጣጫ የተሰጠን በመሆኑ በዚህ ላይ አተኩረን እየሠራን ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች