Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አዲሱን ዓመት ለመቀበል የመጨረሻዋ ምራቂ ጳጉሜን ወር ስትገባ ለስድስቱ ቀናት መንግሥት ስያሜ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ የአገልጋይነት፣ የመስዋዕትነት፣ የበጎነት፣ የአምራችነት፣ የትውልድና የአብሮነት ቀናት ተብለው በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓቶች ተከብረዋል፡፡ በበኩሌ ለጳጉሜን የተሰጡ ስያሜዎች ዓመቱን ሙሉ ልባችንና አዕምሮአችን ውስጥ ታትመው ቢኖሩ እመኛለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አብዛኛው ነገር ለታይታ ያህል የተካሄደ ነው የሚመስለኝ፡፡ ለእኔ ግን የገጠመኜ መነሻ የሆነው እሑድ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም አዛውንቶች፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች የታደሙበት ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

አዲሱ ትውልድ የነገ አገር ተረካቢ በመሆኑ ሁልጊዜም የትውልድ ዕጣ ፈንታ ከሚያሳስባቸው ዜጎች አንዱ ነኝ፡፡ እኔ ልጅነቴ፣ ወጣትነቴ፣ ጎልማሳነቴም ሆነ የአረጋዊነት ዘመኔ ያለፈውና እያለፈ ያለው አንገር አንቀጥቅጥ በነበረው አብዮትና ከዚያ በኋላ በተከታታይ ባጋጠሙን ሁከቶች፣ ፍጅቶችና ውድመቶች ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የየካቲት 1966 ዓ.ም. ፈንድቶ ዘውዳዊው ሥርዓት ከተፈነገለ በኋላ፣ ኢትዮጵያ በሰላም ያሳለፈችበትን ጊዜ ለማስታወስ ብሞክር ምንም ነገር አይታየኝም፡፡ የእኔ ትውልድ አባላት በዘመነ ደርግ መጀመሪያ በተነሳው ቅራኔ ሳቢያ እርስ በርስ ተፋጅተዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ በሰሜንና በምሥራቅ በነበሩ ጦርነቶች አልቀዋል፡፡

በአንድ ወቅት እንደ አሸን የፈሉ መጻሕፍት የከተቧቸው ታሪኮች ከእነ ችግሮቻቸው የሚነግሩን ደርግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሻዕቢያ፣ ወያኔ፣ ኦነግና ሌሎች በተለያዩ ጎራዎች ያስከተሉትን ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከእነ ሥርዓታቸው ከመወገዳቸው በፊት በፊውዳሎችና በተማረው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል የተፈጠረው ቅራኔ፣ ለሥር ነቀል ለውጥ በማነሳሳት አገሪቱ በአብዮቱ ፍንዳታ ማግሥት አንድ ትውልድ አጣች፡፡ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› ተብሎ አንድ ትውልድ እርስ በርሱ ተባልቶ አገሪቱ በደም ታጠበች፡፡ ለአገራቸው ታላላቅ ሥራዎች ለማከናወን ከፍተኛ ዕቅድ የነበራቸው ወጣቶች እንደ ወጡ ቀሩ፡፡

የዚያ አሳዛኝ ታሪክ ሒደት ቀጥሎ ከግራ አክራሪ የማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ተሰንጥረው የወጡ ደግሞ፣ የእነ ስታሊንን እንደ ወረደ የተፈበረከ የብሔርተኝነት ካባ ለብሰው አገር ለመበታተን የሚያስችል ዕቅድ ነደፉ፡፡ ኢትዮጵያን የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት በማስመሰል፣ አንዱን የሌላው ጠላት አድርገው በመሳል ለዘመናት አብሮ የኖረን ታሪካዊ ሕዝብ የሚከፋፍል ሕገ መንግሥት ቀረፁ፡፡ ውጤቱን ከመጠን በላይ እያየን ይመስለኛል፡፡ ትውልዱ በአገሩ እንዳይኮራ፣ በአገሩና በሕዝቡ እንዳይመካ፣ አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው የሚለውን ዕሳቤ በመደበቅ እንደ ጋሪ ፈረስ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያይ በማድረግ ክፍፍል ፈጠሩ፡፡ ዛሬ በገዛ አገር ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ ያልተቻለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ብልጦቹ ብሔርተኞች ራሳቸውን ‹‹ፌዴራሊስት›› በማለት ሌሎችን ‹‹አሀዳውያን›› እያሉ ተከታዮቻቸውን ሲያጃጅሉ፣ እነሱ በዓለም ላይ በሚታወቁ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ማስተርሶቻቸውንና ፒኤችዲዎቻቸውን በመያዝ ትውልዱን ግራ ያጋቡታል፡፡ ትውልዱ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝቶ ሞጋች እንዳይሆን፣ በመንጋ አስተሳሰብ ጠፍንገው በመያዝ ገዳይና አውዳሚ እያደረጉት ነው፡፡ ትናንት አርቆ ማሰብ የተሳነው አንድ ትውልድ ቢያንስ አንባቢ ነበር፡፡ የዛሬው ግን ንባብ ህርሙ ሆኖ ፈተና የሚያልፈው በኩረጃ ነው፡፡ ኩረጃ በጠንካራ የፈተና ዝግጅት መና ሲቀር የተገኘውን አሳፋሪ ውጤት አንረሳውም፡፡

የተማሩ የሚባሉ ጽንፈኞች ግን ከፈተናዎች ድርጅት ከሸሪኮቻቸው ጋር በማበር ፈተና በማሰረቅ ያደረሱትን ኪሳራ አንረሳውም፡፡ በትውልዱ ሕይወት ላይ የሚቆምሩት የእነሱ ያረጀና የዛገ አጀንዳ እንዲሸከምላቸው ብቻ ነው፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ ለውጡ በጋለበት ወቅት አሜሪካና አውሮፓ ሆነው በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ከፍተኛ ተከታይ ያፈሩ አክራሪ ብሔርተኞች፣ በለውጡ ማግሥት አገር ቤት ገብተው ያደረሱትን ፍጅትና ውድመት አንረሳውም፡፡ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ በማነሳሳት ትውልዱ እጁን በንፁኃን ደም እንዲለቃለቅ አድርገውታል፡፡ እነ ሻሸመኔን፣ ዝዋይን፣ አርሲን፣ ባሌንና ሌሎች ሥፍራዎችን መዘንጋት አይቻልም፡፡

በቀደም ዕለት የትውልድ ቀን ሲዘከር ፕሬዚዳንቷም ሆኑ የትምህርት ሚኒስትሩ ጠቃሚ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡ ትውልዱ ከመንጋ አስተሳሰብ ተላቆ ሞጋች እንዲሆን የሚያስችል ጥራት ያለው ትምህርትና መደላድል አስፈላጊነትን አውስተዋል፡፡ እርግጥ ነው ለዘመኑ ትውልድ የሚመጥኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከመነደፋቸው በፊት፣ ትውልዱ ራሱ ዋነኛ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ሊታለፍ የማይገባው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ አውቅልሃለሁ ማለት አይቻልም፡፡ አንጋፋው ትውልድ ለአዲሱ መደላድሎችን ማመቻቸት እንጂ ይህ ‹‹ይሻልሃል፣ እንዲህ ብታደርግ ይመረጣል፣ ወይም እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለማከናወን ይህንን መርህ ተከተል፣ ወዘተ›› ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይ የመንግሥት ሥልጣን የያዛችሁ ከዚህ ድርጊት ተቆጠቡ፡፡

‹‹የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ሰው ተወው›› የሚባል ዕድሜ ጠገብ አገራዊ አባባል አለ፡፡ ያለፈው ትውልድ ከራሱ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ሲያጋራ ጥፋቶቹንም በሚገባ ማመን አለበት፡፡ ስለሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች ሲናገርም በተግባር ያለፈባቸውን ሒደቶች ማመላከት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነትና ዘራፊነት ዘውድ ደፍተው ተኮፍሰው ሳለ፣ ይህንን ለዓመታት የዘለቀ በሽታ እንደ ዋዛ ማለፍ ሳይሆን የችግሩን ምንጭ አፍረጥርጦ መናገር ተገቢ ነው፡፡ አገር የሚያተራምሱና ለማፍረስ የማይመለሱ አደገኛ ድርጊቶች ምክንያታቸው ጭምር መነገር አለበት፡፡ ከዚህ በተረፈ ለትውልዱ መታነፅ መሰናክል የሚሆኑት አምባገነንነት፣ ሴረኝነት፣ ሌብነት፣ ውሸታምነት፣ ኢሰብዓዊነትና ኢሞራላዊነት በተግባር እንዲወገዱ ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ የታይታ ሥራዎች ፋይዳ የላቸውም፡፡

(ኤርሚያስ ዮሐንስ፣ ከገርጂ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...