Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ክልል ግጭት ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች መታሰራቸውንና ከ200 በላይ መገደላቸውን ተመድ...

በአማራ ክልል ግጭት ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች መታሰራቸውንና ከ200 በላይ መገደላቸውን ተመድ አስታወቀ

ቀን:

  • ሁሉም ጥሰቶች ተመርምረው ተጠያቂነት መረጋገጥ አለበት ብሏል
  • መርማሪ ቦርዱ በበኩሉ የታሰሩ ሰዎች ብዛት 764 ነው ብሏል

በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭትና ግጭቱን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን፣ እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታወቁ፡፡

የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ሰሞኑን በተጀመረው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመባቸው ናቸው ያሏቸውን አገሮች በመጥቀስ ዋና ዋና ጥሰቶቹንም ዘርዝረዋል። ኮሚሽነሩ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ረገድ በአሳሳቢነት ከጠቀሷቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሊቢያ፣ ሊባኖስ፣ ቱኒዚያና ፔሩ ይገኙበታል። 

በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ከደረሷቸው ሪፖርቶች መረዳታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ግጭቱን ለመግታት የፌዴራል መንግሥት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከጣለ ጀምሮም ከ1,000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በቀጠለው ግጭት ሳቢያም ግድያ፣ እንግልትና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። በትግራይ ክልልም እንዲሁ የጅምላ እስራትና አስገድዶ የማፈናቀል ተግባራት መኖራቸውን፣ ይህ ችግር በተለይም በኤርትራና በአማራ ኃይሎች ተይዘዋል በሚባሉ አካባቢዎች ጎልቶ እንደሚታይ ጠቅሰዋል። 

እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ተመርምረው ጥሰቶቹን የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባልም ብለዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችን በተመለከተ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በአገሪቱ መንግሥት የታቀደውን የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በተጀመሩ ምክክሮች ውስጥ የተገኘውን ዕድገት ዕውቅና ሰጥተዋል። የሽግግር ፍትሕንና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚያበረታቱ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የተጀመረው ምክክር እንዲጎለብት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሴቶችን ጨምሮ ቀጣይ ውይይት እንዲደረግበት አሳስበዋል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር ተብሎ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲከታተል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ በሆነባቸው አምስት ማዕከላት ብቻ 764 ሰዎች ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አስታውቋል።

የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንዴሞ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በተቋቋመው ዕዝ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች የሚገኙባቸውን ማቆያ ጣቢያዎች መርማሪ ቦርዱ መጎብኘቱን ገልጸዋል። በዚህም በሸዋሮቢት፣ በጎንደር፣ በኮምቦልቻ፣ በባህር ዳር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (በኋላ ላይ አዋሽ አርባ የተዘዋወሩ) የመስክ ምልከታ በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ መልካም የሰብዓዊ አያያዝ እየተደረገላቸው መሆኑን መታዘባቸውንና ይህንንም ከተያዙት ሰዎች ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡

አክለውም ቦርዱ ምልከታ ባደረገባቸው አምስት ማዕከላት ብቻ 764 ተጠርጣሪዎች በሕግ ጥላ ሥር እንደሚገኙና የእነዚህንም ማንነት በዝርዝር መመዝገቡን ገልጸዋል። ቦርዱ ምልከታ ያላደረገባቸው የተወሰኑ ማቆያ ጣቢያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን መልቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጀመር ስለሚችል አጠቃላይ የተጠርጣሪዎች ብዛት ከ764 ሊቀንስም ሊጨምርም እንደሚችል የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የተጀመረውን የምርመራ ሒደት በማፋጠን ክስ እንዲመሠረት፣ በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸው እንዲለቀቁ፣ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው በቂ ዋስትና አቅርበው እንዲለቀቁ መርማሪ ቦርዱ ለኮማንድ ፖስቱ ምክረ ሐሳብ ማቀረቡንና የዚህን አፈጻጸም እንደሚከታተል ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...