Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ634 ሚሊዮን ብር ወጪ የገነባው የአረጋውያን መጠለያ ማዕከል ተጠናቆ ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ማዕከሉ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው የራሱ ገቢ ማስገኛ አለው ተብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ ትልልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት የተለያዩ ግንባታዎችን በማካሄድ ለአገልግሎት እያበቁና ድጋፍ እየሰጡ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳመለከቱት፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በተለያዩ ቢዝነሶች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች፣ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ዙሪያ እያሳዩ የሚገኙት ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡ 

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ634 ሚሊዮን ብር ወጪ የገነባው የአረጋውያን መጠለያ ማዕከል ተጠናቆ ሥራ ጀመረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የአረጋውያን ማዕከሉ ከፊል ገጽታ

ማኅበራዊ ኃላፊነትን በተደራጀ መንገድ ለመወጣት እንዲቻል አስተዳደሩ ጉዳዩን እንደ አንድ ሥራው በመያዝ መንቀሳቀስ በመጀመሩ በርካታ ኩባንያዎች በተለያዩ በጎ ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ለብዙዎች እንዲደርስ ማስቻሉንም ይጠቅሳሉ፡፡ ባለፈው ሐሙስ መስረከም 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር በሚገኘው በሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን የተገነባውን የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል መርቀው በከፈቱበት ወቅትም በአዲስ አበባ፣ ባለሀብቶች በጎ እጃቸውን ካሳረፉበት ትልልቅ ግንባታዎች መካከል አንዱ ይኼው የአረጋውያን ማዕከል ነው፡፡ 

ለማዕከሉ ግንባታና ውስጣዊ መገልገያዎች ግዥ ከ634 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ በዓይነቱ የተለያየ ነው የተባለው የአረጋውያን ማዕከል በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 750 አረጋውያንን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

የሰንሻይን ፋውንዴሽን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተደረሰው ስምምነትና በገባው ቃል መሠረት ማዕከሉ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ አዲስ አበባ ከተማ በዚህ ደረጃ የአረጋውያን መጠለያ ማዕከል ያልነበራት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ 

የማዕከሉ ግንባታና አጠቃላይ ውስጣዊ ይዘት ለአረጋውያኑ እንክብካቤ ምቹ ሆኖ የተገነባ ከመሆኑም በላይ እንደ ሞዴል እንዲታይ የሚያስችሉ የተለያዩ ገጽታዎች የያዘም መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡  

በባለሀብቶች በጎ እጆች በከተማው ውስጥ እየተሠሩ ያሉ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ያስቻሉ ሥራዎች በሌሎች የከተማው ባለሀብቶች ጭምር እየተለመደ የመጣ እንደሆነ የገለጹት ከንቲባዋ፣ የማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደ ሕግና እንደ አሠራር እየተወሰደ ያለ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡ 

‹‹ሀብት ስላለ ብቻ ወይም ሕግና ፖሊሲ ስላለን ብቻ እንዲህ ያለውን ማኅበራዊ ኃላፊነት መወጣት አይቻልም፤›› ያሉት ከንቲባዋ፣ ለበጎ ተግባራቱ ቅን ልቦና የሚያስፈልግ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

‹‹እንዲህ ዓይነቱን በጎ ሥራዎች ለመሥራት፣ እንዲሁም ለሌሎች ለመትረፍ፣ ልበ ቀና መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ሳሙኤልን ጨምሮ ብዙ ልበ ቀና እያፈራን ነው፤›› በማለት በተለያዩ ባለሀብቶች እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች አድንቀዋል፡፡ አያይዘውም፣ በመንግሥት ብቻ የዜጎችን ሕይወት መቀየር ስለማይቻል ተባብሮ መሥራትና ለሌሎች መድረስ ትልቅ ዕርካታ የሚሰጥ እንደሆነም በማውሳት፣ ሌሎችም እንዲህ ባለው በጎ ተግባር ይሳተፉ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ 

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ በዓይነቱ ለየት ብሎ እንዲገነባና ውስጣዊ መገልገያዎቹም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነውን ማዕከል ለአገልግሎት ማብቃት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡  

አቶ ሳሙኤልም ሆኑ ከንቲባ አዳነች ይህንን የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከል ልዩ ያደርገዋል ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ፣ ማዕከሉ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው የራሱ ገቢ ምንጭ እንዲኖረው መደረጉ ነው፡፡ 

ለማዕከሉ የራሱ ገቢ ምንጭ የሚሆነውና ለተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎች ሊያገለግል የሚችል ሕንፃ ተገንብቶለታል፡፡ የዚህ ሕንፃ በመገንባት አረጋውያኑ ያለ ምንም ችግር ከማዕከሉ የገቢ ምንጭ እንዲጦሩ የሚያስችል በመሆኑ እንደ ሞዴል የሚታይ ነው ተብሏል፡፡ 

ከዚህም ሌላ የከተማ ግብርና የዕደ ጥበብ ሥርዓት መዘርጋቱም የተለየ የሚያደርገው ሲሆን፣ አቅም ያላቸው አረጋውያን በከተማ ግብርና በዕደ ጥበብ ሥራ እንዲሳተፉ ማስቻሉም ለየት ያደርገዋል፡፡

ማዕከሉ የአረጋውያን መኝታ ቤቶች፣ ክሊኒክ፣ መመገቢያና ማብሰያ ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ላውንደሪና የአረጋውያን አልባሳት ማኖሪያ ለብቻው ተገንብቶለታል፡፡ ሌሎች የማዕከሉን አገልግሎት ይደግፋሉ የተባሉ ግንባታዎችን የያዘው ይህ ማዕከል፣ አሁን ሥራ በጀመረበት ወቅት 80 አረጋውያንን ተቀብሎ ማስተናገድ የጀመረ ሲሆን፣ ከ15 ቀናት በኋላ 200 መቶ፣ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ 750 እንደሚያደርስ ታውቋል፡፡

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለበጎ ሥራዎች አሻራውን ሲያሳርፍ፣ ይህ የመጀመርያ ያለመሆኑ የመሰከሩት ከንቲባ አዳነች፣ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የገነባቸውን የተለያዩ ግንባታዎች ጠቅሰዋል፡፡

ሰንሻይን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ በተለይ ካለፉት 12 ዓመታት ወዲህ በቋሚነት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝበት በተለያዩ አካባቢዎች የገነባቸው ትምህርት ቤቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

በዚህ በጎ ተግባር ዙሪያ ሲያደርጉ የነበረውን ሥራ በተመለከተ አቶ ሳሙኤል፣ እንደገለጹትም በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተገኙበት በእነዚህ ትምህርት ቤቶች አነስተኛ የገቢ ያላቸው የቤተሰብ ልጆችን፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን በማጣታቸው ምክንያት የትምህርት ዕድል ላላገኙ ታዳጊ ወጣቶችና መማር እየፈለጉ ዕድሉን ማግኘት ላልቻሉ ዜጎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ያስቻለ ነው፡፡ 

እነዚህም ትምህርት ቤቶች በኦሮሚያ ክልል፣ ነቀምት፣ በትግራይ ክልል አክሱም፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል አገና በመገንባት ሥራ ከጀመሩ 12 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደብረ ብርሃን በ54 ሚሊዮን ብር በመገንባት በመጪው ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. የሚመረቅ መሆኑንም አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡ 

በአጠቃላይ ሥራ በጀመሩት በእነዚህ በትምህርት ቤቶች ከ1,600 በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከነፃ የትምህርት ዕድል በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ተማሪ የሚሰጠውን 250 ብር ወርኃዊ የኪስ ገንዘብ ጨምሮ፣ ሥራ ላይ ላሉ ትምህርት ቤቶች በየወሩ 1.1 ሚሊዮን ብር ወጪ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች የወጣውን ወጪና ለአረጋውያን ማዕከሉ ግንባታና ውስጣዊ መገልገያዎች ግዥ፣ እንዲሁም ተያያዥ ለሆኑ ድጋፎች የሰንሻይን ኢንቨስመንት ግሩፕ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ በቀጣይ ወር ወደ ሥራ የሚገባው የደብረ ብርሃን ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎችና አስተዳዳር ወጪ የሚመደብ በመሆኑም፣ ኩባንያው ለአጠቃላይ ትምህርት ቤቶቹ በየወሩ የሚያወጣው ወጪ ከፍ እያለ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡  

ሰንሻይን የኢንቨስትመንት ግሩፕ ከእነዚህ በጎ ተግባራቱ ሌላ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ የገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በዚሁ ክፍለ ከተማ አቶ ሳሙኤል የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተማሩበት የፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት የዲጂታል ላይብረሪ፣ ሚኒ ሚዲያና ክሊኒክ ገንብተው ማስረከባቸውንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በዚህ ማዕከል ለመጦር ዕድል ያገኙ አረጋውያን በምረቃ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩበት እጅግ ወደ ተሻለ ቦታ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከንቲባዋ በገቡልን ቃል መሠረት የተሻለ መጦሪያ አግኝተናልም ብለዋል፡፡  

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እስካሁን ላበረከተው የበጎ ሥራ ተግባሩ አስተዳደሩ ዕውቅና የሰጠው ሲሆን፣ ይህንንም የዕውቅና ሰርተፍኬት አቶ ሳሙኤልንና ባለቤታቸው ወ/ሮ ፈትለወርቅ አላላ ከከንቲባዋ እጅ ተረክበዋል፡፡ 

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኮንስትራክሽን በሆቴል፣ በሪል ስቴትና ቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግና በመሰል ቢዝነሶች ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለ ኩባንያ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከስድስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች