በአማራ ክልል ከባለፈው ዓመት 2015 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ጀምሮ ተከስቶ በነበረው የኮሌራ በሽታ 70 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በተከሰተው የኮሌራ በሽታ ከሞቱት ሰዎች ባሻገር 3,800 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሐምሌ ወር ቋራ በተባለ የፀበል ቦታ አካባቢ በሽታው እንደተቀሰቀሰ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተከሰተበት አካባቢ ከከተማ ራቅ ያለ ቢሆንም የመሠራጨት ሁኔታው በፍጥነት ጨምሮ እንደነበር ገልጸው፣ ነገር ግን በተደረገ ርብርብ ሥርጭቱ በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስ ችሏል ብለዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሲታይ በጣም ብዙ ላይባል ይችላል ነገር ግን በጣም ጥንቃቄ ካልተደረገ ከዚህ በላይ ሊሆን ይችላል፤›› ያሉት አቶ በላይ፣ የሞት መጠኑም ቢሆን ኮሌራ እስካልጠፋ ድረስ ሊጨምር ይችላል በማለት ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሽታው ባህር ዳርንና ጎንደርን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ላይ ቀድሞ የተስፋፋ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሁሉም ዞኖች በተለይ ደግሞ በምዕራብ አማራ በሚባለው አካባቢ ሰሜን ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደርና ጎጃም እንዲሁም በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች በሰሜን ሸዋ አካባቢ አልፎ አልፎ እየተከሰተ ነው ብለዋል፡፡
ወደፊትም ሊከሰት ይችላል ነገር ግን ይሄ እንዳይሆን በስፋት ሊሠራ ይገባል ሲሉ አቶ በላይ አክለዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆይ ክትባት እንደሚሰጥ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ክትባቱ አዲስ በመሆኑ በሚፈለገው መጠን ስለማይገኝ 1.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ብቻ እንደሚሰጥ ተናግረው ክትባቱ የሚሰጠውም ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነው ሲሉ አቶ በላይ አብራርተዋል፡፡
ክትባቱ የሚሰጥባቸው አካባቢዎችም መጀመርያ አካባቢ ተከስቶባቸው በነበሩ ዘጠኝ ወረዳዎች በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በሽታው የተከሰተባቸው ሌሎች ቦታዎች ቢኖሩም በዋናነት ክትባቱ የሚሰጠው ባህር ዳርና ጎንደርን ጨምሮ በዘጠኙ ወረዳዎች አካባቢ ነው ሲሉ አቶ በላይ አብራርተዋል፡፡
በሌሎች የመከላከያ መንገዶች እንሠራለን የሚል ነው እንጂ ክትባቱ የሚሰጥባቸው ቦታዎች በቂ አይሉም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን በቀጣይ ፌዴራል መንግሥቱ እንዲያቀርብ ግፊት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
‹‹ኮሌራ በሽታ የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ ነው›› ያሉት አቶ በላይ፣ በተለይ በታዳጊ አገሮች ላይ በሚታየው የንፅህና ጉድለትና ባለው የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር ተጋላጭነቱ እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልል በጣም ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
በተለያዩ የፀበል ቦታ አካባቢዎች፣ የመጠለያ ጣቢያዎች፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት አለመኖር ለበሽታው መከሰት እንደ መንስዔ የተነሱ ሲሆን፣ በደብረ ብርሃን የመጠለያ ጣቢያና በከተማው ውስጥ ላሉ ሰዎች ክትባቱ እንደሚሰጥ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በማረሚያ ቤቶችና መሰል ተጋላጭ ቦታዎች በአገር ደረጃ ክትባቱ ቢሰጥ ጥሩ ነው ያሉት አቶ በላይ፣ ነገር ግን መድኃኒቱ ውድና አዲስ በመሆኑ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማዳረስ የሚቻል አይደለም ነው ያሉት፡፡
እንደ አገር ኮሌራን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፣ ሰዎች የንፁህ ውኃ አገልግሎት ካገኙና ንቃተ ጤናቸው ከፍ ካለ በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል ብለዋል፡፡
እንደ አማራ ክልል ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የፌዴራል ተቋማት የጤና ግብዓቶችንና የተለያዩ ድጋፎችን ጠንከር ባለ ሁኔታ እንዲያደርጉ ጥሪአቸውን አቅርበዋል፡፡