Sunday, July 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሐረር ታይዋን እሳት አደጋ ተጎጂዎች የክልሉ መንግሥት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲመልሰቸው ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ በተለምዶ የቀድሞው ታይዋን ወይም ካርቶን ተራ በእሳት አደጋ የንግድ ቤቶቻቸውን ያጡ ተጎጂዎች፣ የክልሉ መንግሥት በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲመልሳቸው ጠየቁ፡፡ ጳጉሜን 1 ለጳጉሜን 2 አጥቢያ በግምት ከሌሊቱ አሥር ሰዓት በደረሰው አደጋ በአማካይ ወደ 60 የንግድ ቤቶች መውደማቸው ታውቋል፡፡ የእሳት አደጋው ሱቃቸውን ከእነ ሙሉ ንብረቱ ያወደመባቸው ተጎጂዎች፣ የክልሉ አስተዳደር በቶሎ የመሥሪያ ቦታ ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲያስገባቸው ጠይቀዋል፡፡

በተለይም ሸዋ በር በሚባለው ቦታ የጀጎል ግንብን ታኮ የተመሠረተው በእሳት የወደመው የታይዋን ገበያ፣ በአሁኑ ጊዜ በፖሊስ ጥበቃ ተከልሏል፡፡ የክልሉ ፖሊስ የጉዳቱን መንስዔ እያጣራ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በጉዳቱ ማግሥት የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከተጎጂ ነጋዴዎች ጋር ስብሰባ መቀመጣቸው የታወቀ ሲሆን፣ በቶሎ ወደ ሥራ እንዲመለሱ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተውላቸው ነበር ተብሏል፡፡

ሪፖርተር ጉዳቱ በደረሰበት ቦታ ተገኝቶ ያናገራቸው የጉዳቱ ሰለባዎች ግን፣ የክልሉ መንግሥት ወደ ሥራቸው ለመመለስ የገባውን ቃል ፈጥኖ እንዲተገብር ጠይቀዋል፡፡

የአምስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑትና ከ700 ሺሕ ብር በላይ ንብረት በጉዳቱ እንደወደመባቸው የተናገሩት አቶ ከበደ ተካ፣ እሳቱ ያስከተለው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹እስከ 10 እና 12 ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ነጋዴዎችን አውቃለሁ፡፡ ለእኛ ዕቃ የሚያቀርቡ ሰዎችም ተጎጂ ናቸው፡፡ ቦታው ትንሽ ቢሆንም የጅምላ ወይም የማከፋፈል ንግድ የሚሠራበት ሞቅ ያለ ገበያ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የጫኝና የአውራጅ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ጭምር የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የነጋዴው መሠረታዊ ጥያቄ ወደ ሥራ መልሱን የሚል መሆኑን ያከሉት አቶ ከበደ፣ የቃጠሎው ጉዳት በ60 የንግድ ቤቶች የተወሰነ ብቻ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በእሳት በወደመው የገበያ ቦታ ሲጀመር ጀምሮ ለ41 ዓመታት ሲሠሩ የቆዩት አቶ ኃይሉ ወልደ አረጋይ በበኩላቸው፣ አደጋው ስምንት ቤተሰቦችን የሚያስተዳድሩበትን ንግድ እንዳሳጣቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት ዕዳ ስለነበረብኝ የኖርኩበትን ሱቅ አከራይቼ በራፌ ላይ ተቀምጬ ነበር የምነግደው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለሁ ነው ይህ አደጋ የደረሰብኝ፡፡ ሱቄን የተከራየው ሰው በውስጡ 1.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት እንደ ወደመበት አሳውቋል፡፡ ምትክ ቦታ ይሰጣል ቢባልም ነገር ግን የሱቅ ባለቤቶችን ሳይሆን ተከራይተው የሚነግዱ ንብረት የወደመባቸውን ብቻ ነው የሚመለከተው መባሉ ሥጋት ውስጥ ከቶናል፤›› ብለዋል፡፡

በዚሁ የገበያ ቦታ ሱቃቸው የወደመባቸው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አይናለም እሸቱ በበኩላቸው፣ የተጎጂዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ ከክልሉ መንግሥት ጋር መግባባት የሰፈነበት ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹የተጎጂዎች ሁኔታ በትክክለኛ መንገድ እንደተጣራና እንደተጠናቀቀ፣ እንዲሁም በተገቢው ሁኔታ ተጎጂዎች የመሥሪያ ቦታ እንደሚሰጣቸው ክልሉ አረጋግጦልናል፡፡ በኖርንበት ቦታ ይሁን ሌላ ቦታ መሥሪያ ቦታው የሚሰጠን ገና አልታወቀም፡፡ አከራይ ነው ወይስ ተከራይ የመሥሪያ ቦታ የሚሰጠው የሚል ልዩነት የለም፡፡ ሁሉም ተጎጂ እንደሚያገኝ ነው ቃል የተገባልን፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የክልሉ ንግድ ቢሮ፣ የክልሉ አደጋ መከላከል፣ እንዲሁም የብልፅግና ጽሕፈት ቤትና ፖሊስ ከተጎጂው ኮሚቴ ጋር ተከታታይ ውይይቶች ማድረጋቸውንም አቶ አይናለም አስረድተዋል፡፡

በማከራየትም በመከራየትም በቦታው ሲሠሩ እንደቆዩ የገለጹት አቶ አይናለም፣ በቦታቸው ሳያከራዩ የሚሠሩ ከስምንት ሰዎች እንደማይበልጡ ነው የጠቀሱት፡፡ ከ700 ሺሕ ብር በላይ ንብረት እንደወደመባቸውና ስምንት ቤተሰቦችን በሥራቸው ሲያስተዳድሩ መቆየታቸውን አክለዋል፡፡

በሐረር ከተማ የሰሞኑን ጉዳት ተከትሎ ‹‹ደግሞ እንደገና አቃጠሉት›› የሚል ቅሬታ በነዋሪዎች ዘንድ ሲሰማ ሰንብቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በመብራት ኃይል ገበያ፣ በሀርት ሼክ ተራ ገበያ፣ እንዲሁም በልብስ ተራ ገበያዎች የደረሱ ተደጋጋሚ የገበያ ቃጠሎ አደጋዎችን በማስታወስ ነዋሪዎች ብሶት ሲያሰሙ ነበር፡፡ የአሁኑን ጨምሮ እነዚህ ተደጋጋም የገበያ ቃጠሎዎች ሆን ተብሎ የተፈጠሩ ሴራዎች እንደሆኑ ብዙዎች በተለያዩ መንገዶች ቅሬታ ሲያቀርቡም ቆይተዋል፡፡

ጉዳዩን የሚከታተለው የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ ግን፣ ይህ ሁሉ መሠረት የሌለው ከእውነታ የራቀ አሉባልታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰሞኑ የታይዋን ገበያ ቃጠሎ ገና እየተመረመረ መሆኑንና ውጤቱ አለመጠናቀቁን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹የመንግሥት አካል ሆኖ ይህን መሰል አደጋ የሚፈጽም የለም፡፡ ዜጎች ላይ ጉዳት የማድረስ ፍላጎት ያለው መንግሥት የለም፡፡ ይህንን በተመለከተ ከተጎጂዎች ጋር ባደረግነው ውይይት አረጋግጠንላቸዋል፡፡ ጥሩ መግባባትም ተፈጥሯል፡፡ ተጎጂዎቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረግ ያለበት ሁሉ ይደረጋል፤›› በማለት ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች