Wednesday, September 27, 2023

የሕዝቡ የምሬት ምንጭ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአዲስ ዘመን አዲስ ተስፋ ሰንቆ በአዲስ ዕቅድ ሥራን ለመጀመር በግለሰብ ደረጃም ይሁን በተቋማት ዘንድ የተለመደ አሠራር ነው፡፡

ትናንት መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተከበረው አዲስ ዓመት ዋዜማ፣ መጪው ጊዜ የተሻለ ተስፋን ይዞ እንዲመጣ ከበርካቶች ዘንድ ሲሰማ የነበረ የምኞትና የተስፋ ጥሪ ነበር፡፡

ከተጠናቀቀው 2015 ዓ.ም. የቀጠሉት የአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ፈተናዎች በይዘታቸውም ሆነ በዓይነታቸው ሰፋፊ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሰፋ ያለው አገራዊ ችግር ከፖለቲካና ከኑሮ ውድነት ጋር የተገናኙ የኢኮኖሚ ይዘትን የተላበሱ ጥያቄዎችን የያዘው ይገኝበታል፡፡

በፖለቲካው ረገድ ምንም እንኳ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ከተማ በተደረገው የሰላም ስምምነት በተፈጠረው ሰላም፣ በጦርነቱ ውስጥ የነበሩትን ክልሎች ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በበርካቶች ዘንድ ተስፋን ያለመለመ ነበር፡፡

የሕዝቡ የምሬት ምንጭ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ይሁን አንጂ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ተፈታ ቢባልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ውጥረት ተፈጥሯል፡፡ ለዚህም እንደ ማሰያ ሊጠቀስ የሚችለው የአገር መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር የጀመረው ጦርነትና የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች አዋሳኞች የሚታየው የይገባኛል ጥያቄ የፈጠረው ውጥረት፣ በኦሮሚያ ክልል በአገር መከላከያ ሠራዊትና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ  ፓርቲዎች በኩል የተጀመረው አለመግበባትና ውጥረት፣ በቀድሞው የደቡብ ክልል በሕዝበ ውሳኔ የተለያዩ ክልሎች መመሥረታቸው፣ በተጨማሪም አዳዲስ የመዋቅርና  የክልልነት ጥያቄዎች፣ በሸገርና በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የቤቶች ፈረሳ፣ የጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች አፈሳና እስር፣ የመንቀሳቀስ ገደብ፣ እንዲሁም ለበርካታ ጉዳዮች መልስ መስጠት የአዲስ ዓመት የመንግሥት የፖለቲካ የቤት ሥራ ናቸው፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት እየተፈታተነ ያለው የምርት አቅርቦት እጥረት፣ የማዳበሪያ አቅርቦት ውስንነት፣ የትራንስፖርት እጥረት የፈጠረው የአቅርቦት ችግር፣ በየዜው እየጨመረ የመጣውና ሊያባራ ያልቻለው የዋጋ ንረት፣ በጦርነትና በግብዓት አቅርቦት እጥረት ምክንያት የግብርና ሥራ መስተጓጎል፣ ሥራ አጥነት፣ የገቢና የወጪ አለመመጣጠን፣ የቤት ሽያጭና የኪራይ ዋጋ አልቀመስ ማለትና የመሳሰሉት፣ በአጠቃላይ ያልተረጋጋው የገበያ ሥርዓት የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ያጎሳቆሉ ናቸው፡፡

በዚህ ሁሉ ሒደት በብልፅግና ፓርቲ የበላይነት የሚመራው መንግሥት በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ባገኟቸው መድረኮች ሁሉ ኢትዮጵያ በብልፅግና ጎዳና መሆኗንና በተምሳሌት የምትወሰድ አገር ነች ሲሉ ይደመጣሉ፡፡  

በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ ጉባዔ ኢትዮጵያ ቡድኑን እንድትቀላቀል መፈቀዱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚዲያ ባደረጉት ንግግር፣ አሁን በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ድል፣ ኢንቨስትመንትና ለውጥ ኢትዮጵያውያን በውል  ባይረዱትም ዓለም ይህን በደንብ ተገንዝቦት በዚያ ደረጃ ዕውቅና እየሰጠውና ዓለም በሙሉ በከፍተኛ አድናቆትና ምሥጋና ስለመቀበሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህና በተለያዩ መድረኮች የሚያደርጓቸው ንግግሮች መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይገልጹ፣ ነባራዊ እውነታውን የማያሳዩ ናቸው በማለት የሚሞግቱ አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችና 21 ሚሊዮን ያህል ደግሞ ዕርዳታ ጠባቂዎች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ውስጣዊ ችግሮች እያለፈች ያለችው ኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ለውጥ እንድታመጣ ከተፈለገ የሕዝቡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቅሬታዎች  ምንጭ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት የሰላማዊ መንገዶች ፈር ቀዳጅ እንጂ ጦርኛነትን የማይመርጥ፣ እንዲሁም የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ በመረዳት ኢኮኖሚያዊ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ የተለያዩ አካላት ሐሳባቸውን ሲሰጡ ይደመጣል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ስትራቴጂክ ጥናቶች መምህር አቶ ገብረ መድኅን ገብረ ሚካኤል፣ በቀጣይ ወራት ለችግሮች ሁሉ ውይይት መደረግ አለበት የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህን ውይይት ለመጀመር የሚታዩት ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያታቸው መታወቅ እንዳለበት፣ ቢያንስ ወደ ውይይት ሊያመሩ የሚችሉ የመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታዎች መለየት አለባቸው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥት ግጭትና ጦርነትን ሊያስነሱ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት አለበት ያሉት አቶ ገብረ መድኅን፣ ሰላም የሚሰፍነው በዚህ መንገድ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት ምንም ዝግጁ ቢሆን እንኳ አሁን የሚታዩት ሁሉም ችግሮች፣ በተጀመረው 2016 ዓ.ም. ይፈታሉ ለማለት ከባድ መሆኑንና ችግሮቹ ጠለቅ ያሉ ስለመሆናቸው አቶ ገብረ መድኅን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ለሰላም መንገድ መጥረግ ጦርነቱን ማስቆምና ለውይይት ለመቀመጥ አመቺ ሁኔታ የሚከፈትበት ጊዜ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡፡  

ለዚህ እንደ ምክንያት የጠቀሱትም የችግሮቹ ስፋትና ይዘት፣ እንዲሁም የግጭቶቹ መነሻ ረዘም ያሉ፣ ጥልቅ የሆኑና ወደኋላ ከ2010 ዓ.ም. በፊት የነበሩ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግሮች በመሆናቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. በፊት የነበሩ የዴሞክራሲና የመብት ጥያቄዎች፣ ሕገ መንግሥቱና የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን የተመለከቱ ጥያቄዎች፣ የአገራዊና የብሔራዊ ማንነት ሚዛንን የተመለከቱ ጥያቄዎች፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር መለወጥና መሰል በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ ጥያቄዎች ነበሩ ብለዋል፡፡

 ይሁን እንጂ በድኅረ 2010 ዓ.ም. መጣ በተባለው ለውጥ የነበረው የዴሞክራሲ ጥያቄ የሰዎች መቀያየር እንጂ፣ ከምርጫም ሆነ ከዜጎች መብት መከበር ጋር ምንም የተሻለ ነገር አልተፈጠረም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የልማትና ፍትሐዊነት ጥያቄ በ2010 ዓ.ም. ለመጣው ለውጥ አንዱ መነሻ የነበረ ቢሆንም፣ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት አገሪቱ በተከታታይ ዕድገት ታሳይ እንደነበር፣ ነገር ግን ይህ ዕድገት ፍትሐዊ አለመሆኑ ግልጽ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አገራዊ ዕድገት አለ ቢባልም አንድ ምንም ያልነበረው ግለሰብ ከየት አመጣ ሳይባል የሕንፃና የመኪና ባለቤት ሆኖ ይታይ እንደነበር፣ ይህ ሊሆን የቻለውም ከባለሥልጣናት ጋር በነበረ ግንኙነት ወይም በኮንትሮባንድ በመሰማራት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተወሰነ ደረጃ የነበረው ዕድገት ከለውጡ በኋላ ጭራሽ መጥፋቱን ሲያብራሩ፣ ለምሳሌ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ የመስኖ ግድብ ግንባታዎች ግንባታ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች፣ በተለይም በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመጨረሻ ሥልጣን ዘመን ተጀምረው የነበሩ ነገር ግን አሁን ቆመው ምንም ሥራ እየተሠራባቸው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በርካታዎቹ ተጠናቀው ወደ ልማት መግባት ሲጠበቅባቸው ገንዘብ እንዳልወጣባቸው አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ብለዋል፡፡

መንግሥት አስገዳጅ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት  ቀዳሚ ተግባሩ ከሆነ ችግሮች የማይፈቱበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ኢኮኖሚው በትክክለኛው መስመር እንዲሄድ ከተፈለገ ትኩረቱ ሁሉ ከፖለቲካ መውጣት አለበት፡፡

ለኢኮኖሚው የብልፅግና ወይም ሌላ የፖለቲካ ስያሜ እየሰጡ መሄዱ የትም የማያደርስ በመሆኑ፣ የኢኮኖሚው ጉዳይ በተለየ መንገድ ትኩረት ካልተሰጠው አገሪቱ ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ የፖለቲካ ጨዋታ እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡  

‹‹ይህች አገር ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ፖለቲካ አይበላም አይጠጣም ነገር ግን ኢኮኖሚውን መጦ የሚሄድ በመሆኑ ተገቢ የሆነ ዕርምጃ ኢኮኖሚው ላይ ሊወሰድ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ ቀንሷል ቢባልም ግሽበቱ አሁንም ስለመቀጠሉ የሚናገሩት  ደምስ (ዶ/ር)፣ ግሽበቱን ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ ወሰድኩት ከሚላቸው ዕርምጃዎች ቴክኒካዊ የሆኑ እንጂ ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ችግሩን የማይፈቱ ስለመሆናቸው ያክላሉ፡፡

በብሔራዊ ባንክ የተወሰዱት ዕርምጃዎች መንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር መጠን መቀነስ፣ የንግድ ባንኮች የብድር መጠናቸውን ካለፈው ዓመት ጋር በመቶኛ መወሰንና መሰል የገንዘብ ፖሊሲ የትም ሊያደርሱ አይችሉም ብለዋል፡፡

ላኪ ድርጅቶች ያገኙት የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ከ30/70 ወደ 50/50 ያወረደው ክፍፍል በተወሰነ ሁኔታ ችግሩን ሊቀርፍ እንደሚችል ጠቅሰው፣ በመሠረታዊነት የአገሪቱ ችግር ግን ለኢኮኖሚው ተገቢ የሆነ ትኩረት አለመስጠትና ገበያውን በተለያየ መንገድ የሚያምሰውን ተቆጣጥሮ መስመር ለማስያዝ አለመቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 ‹‹መንግሥት በመጀመሪያ የአገር ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ በሁለተኛ ደረጃ  ኢኮኖሚውን በሕግ በፖሊሲ መምራት፣ እንደ አስፈላጊነቱ መቆጣጠርና መስመር የማስያዝን ጉዳይን መንግሥትም ደክሟል፣ ሁላችንም አልሠራንበትም፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫና የኢኮኖሚው ጥያቄ ሳይቀር የፖለቲካ ሥራ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ደምስ (ዶ/ር፣) ‹ከሸማችነት ወደ አምራችነት›› በሚል መሪ ቃል የተከበረውን ጳጉሜን 4 ቀን አይዋጥልኝም ብለዋል፡፡

መሪ ቃሉ የአምራችነት ቀን ተብሎ ቢቆም የተሻለ እንደነበረ፣ ነገር ግን ከሸማችነት ወደ አምራችነት የሚለው ዕሳቤ በጣም የተዛባ ነው በማለት  ገልጸዋል፡፡ አክለውም በማክሮ ኢኮኖሚክስ አስተምሮ መመዘኛ ይህ ስህተት ነው ብለዋል፡፡

ፍጆታ፣ ኢንቨስትመንት፣ የመንግሥት ወጪ ከሸመታ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ባደጉትና እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ትልቁን የአገራዊ ሀብት የሚያመነጨው የሸማቹ ክፍል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔራዊ ባንክ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ወይም የገንዘብ ሚኒስቴርን ሪፖርት ቢታይ አጠቃላይ አገራዊ ሀብት ከ65 እስከ 75 በመቶ የሚመነጨውና ያለው በሸመታ ኢኮኖሚ ውስጥ ነው የሚሉት ደምስ (ዶ/ር)፣ ከሸመታ ወደ አምራች ሲባል ነገሩ የፖለቲካ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ ነገሩ ፈር እየለቀቀ የአካሄድ ስህተት እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -