- ሃሎ…
- ጤና ይስልጥኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ጤና ይስልጥልኝ ክቡር ተደራዳሪ… የጥረትዎን ፍሬ በማየትዎ እንኳን ደስ አለዎት፡፡
- እንኳን አብሮ ደስ አለን፣ ምን ልታዘዝ ታዲያ?
- የውኃ ሙሌቱንና አጠቃላይ የግድቡን የግንባታ ሁኔታ በተመለከተ ቃለ መጠይቅ ጠይቀውኝ ሰጥቼ ነበር።
- ለየትኛው ሚዲያ ነው የሰጡት?
- ለብሔራዊ ቴሌቪዥናችን ነው።
- እሺ፣ ምን ተፈጠረ ታዲያ?
- ክቡር ሚኒስትራችን ስለግድቡ ሙሌት መጠናቀቅ ያስተላለፉት መልዕክት ላይ የነበረውን መጠነኛ የመረጃ መፋለስ ለማረም በቃለ መጠይቁ ላይ ማብራሪያ ሰጥቼ ነበር።
- እሺ።
- ነገር ግን ቴሌቪዥን ጣቢያው በዚህ ጉዳይ የሰጠሁትን ማብራሪያ ቆርጦ በማውጣት እንዳይተላለፍ አድርጎታል፣ የሚገርመው ይህንን ሲያደርጉ እኔን አላማከሩኝም።
- አውቃለሁ ክቡር ተደራዳሪ።
- ምኑን ነው የሚያውቁት ክቡር ሚኒስትር?
- የሰጡት ማብራሪያ ተቆርጦ እንደወጣ አውቃለሁ፡፡
- እንዴት እርስዎ አወቁ? ለእኔ እንኳን አልነገሩኝም እኮ፡፡
- የጣቢያው ኃላፊ ደውሎልኝ ነበር።
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትራችን የመጨረሻው የግድቡ ሙሌት ተጠናቋል ማለታቸው ትክክል አይደለም የሚል ማብራሪያ ሰጥተውናልና ማስተላለፍ ይችሉ እንደሆነ ለመጠየቅ ነበር የደወሉት።
- የእርስዎን ትዕዛዝ ጥሰው ነው የሰጠሁትን ማብራሪያ የቆረጡት ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንደዚያ አይደለም።
- ታዲያ ማብራሪያውን ለምን ቆርጠው አወጡት?
- እኔ ነኝ ቆርጠው እንዲያወጡ ያዘዝኳቸው።
- እርስዎ ራስዎ ክቡር ሚኒስትር?
- አዎ፡፡
- ለምን?
- ምክንያቱም ክቡር ሚኒስትራችንን ክብር የሚነካ በመሆኑ ነው።
- እንዴት?
- ምክንያቱም የሰጡት ማብራሪያ ክቡር ሚኒስትራችን እንደተሳሳቱ የሚገልጽና ክብራቸውን የሚነካ ነው።
- እንዴት አድርጎ ነው ክብራቸውን የሚነካው?
- ጥንቁቅ ናቸዋ? አይሳሳቱም።
- እኔም እኮ መልዕክታቸው ብዥታን ፈጥሯል እንጂ ተሳስተዋል አላልኩም።
- ቢሆንም የሰጡትን ማብራሪያ አለማስተላለፍ በራስ ላይ እንደ መተኮስ ነው።
- እንዴት?
- የአክቲቪስቶች መጫወቻ ነው የሚያደርጋቸው።
- ግን እኮ ማኅበረሰባችን ላይ የተፈጠረውን መደናገር የማስተካከል ኃላፊነት አለብን፡፡
- እሱን እረዳለሁ።
- ታዲያ ለምን እንዳይተላለፍ ከለከሉ? ወይም ደግሞ እንደ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊነትዎ ለምን ማብራሪያ አልሰጡበትም።
- እሱን ማድረግ አልችልም፣ ተገቢ ነው ብዬም አላስብም።
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትራችን ይቀየሙኛል።
- ለምን ይቀየማሉ?
- ምክንያቱም ያስተላለፉት መልዕክት በበርካቶች ላይ ብዥታ መፍጠሩን ሳያውቁ ቀርተው አይደለም ዝምታን የመረጡት።
- እህ… ስለዚህ ራሳቸው ስህተቱን ካላረሙ ትክክል ናቸው እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ትክክል ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፣ ነገር ግን…
- ነገር ግን ምን?
- እርሳቸው ዝምታን ከመረጡ እኛ እንዴት ብለን ተሳስተዋል እንላቸዋለን?
- ስለዚህ ምን ማድረግ ነው የሚሻለው?
- አብረዋቸው የሄዱ ሚኒስትሮች ያደረጉትን ማድረግ ነው የሚሻለው።
- ሌሎቹ ምንድነው ያደረጉት?
- አንዳንዶቹ ዝም ነው ያሉት፣ የተቀሩት ደግሞ መልዕክቱን ተቀብለው ‹‹የመጨረሻ ሙሌት›› ነው ብለዋል።
- እና ምንድነው የሚሻለው?
- ዝም!
- Advertisment -
- Advertisment -