Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልቀደምቱን ከአሁኖቹ ጋር ያስተሳሰረው የዕውቅና መድረክ

ቀደምቱን ከአሁኖቹ ጋር ያስተሳሰረው የዕውቅና መድረክ

ቀን:

‹‹ክፉም ለራስ ነው ደግም ለራስ ነው›› የሚባል ብሂል አለ፡፡ አንዳንዶች የተፈጠሩበትን ዓላማ በአግባቡ በመከወን ከራሳቸው፣ ከቤተሰባቸውና ከአገራቸው ተሻግረው ለዓለም የማይነጥፍ አሻራቸውን አስቀምጠው ወደማይቀረው ሞት ያመራሉ፡፡

ክፉዎች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የራሳቸውን ተስፋ አደብዝዘው ወገንና አገራቸውን አሳዝነው የማይጠፋ ዘመን ተሻጋሪ መርዛቸውን ዘርዝረው ከሞት አያመልጡም፡፡

በጎ ሥራን ሠርተው ለአገር ወገናቸው እስከሞት ድረስ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ የአገር ባለውለታዎች፣ የወገን የቁርጥ ቀን ልጆች በሠሩት መልካም ሥራ አገር ዘለዓለም ታወድሳቸዋለች፣ ታከብራቸዋለች፡፡

በጎነት ብዙ ዓይነት መገለጫዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡ በዋናነት ግን በጎነት በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ታማኝ ውጤታማና ትጉህ አገልጋይ በመሆን ለአገርና ለወገን በሃቀኝነት ማገልገል፣ ለሌሎች አርዓያና ምሳሌ በመሆን የጠፋውን በማልማት የጎበጠውን በማቅናት፣ የተሳሳተውን በማረም እንዲሁም ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ማድረግ የበጎነት መገለጫዎች ናቸው፡፡

ብዙ ጊዜ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ሕዝብ ነው›› የምትለዋ ዓረፍተ ነገር ከብዙዎች አንደበት አትጠፋም፡፡ አያይዘውም ሲያብራሩ እውነትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ሕዝብ ነው ምክንያቱም ደግሞ ያለውን ተካፍሎ ‹‹ስሞት አፈር ስሆን›› ተባብሎ በሐዘንና በደስታው ተረዳድተው አንዱ ያለውን ለሌላው ሰጥቶ የሌለው ካለው አምጥቶ ብዙ ግፍና መከራዎችን ረሃብና ጦርነቶችን ተዋግቶ ያሸነፈ ሕዝብ በመሆኑ ነው፡፡

ምንም እንኳን ክፉዎች እየተበራከቱ፣ ክፉነትም በየመስኩ በየዘርፉ እየገባ ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘች ሰሊጥ…›› እንዲሉ ብዙ መልካምና ደጋግ ሰዎች  ታታሪና ሃቀኛ ግለሰቦች ከክፉዎች ጋር አብረው እየተደቀሱ የጅምላ ፍረጃ ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡

ኃላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣ ሰው እንደ ጥፋቱ ክብደትና ቅለት የቅጣት ብይን እንደሚጣልበት ሁሉ፣ በተሰማራበት የሙያ ዘርፉ ባደረገው ቅንነትና መልካምነት ለአገር ብሎም ለወገን ላበረከተው በጎ አስተዋጽኦ፣ ተምሮ ያገኘውን ጥበብ ጥሮ ግሮ ያፈራውን ሀብት እንዲሁም፣ በመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት አገርን በሚያኮራ ሕዝብን በሚጠቅም ሁኔታ ለሠራ ሰው ደግሞ በሠራው ልክ ማመሥገንና መሸለም ለቀጣይ ለሚሠራቸው መልካምና በጎ ሥራዎች የበለጠ ከማጠናከሩ ባሻገር ሌሎችም የበጎዎችን ከፍታ አክብሮትና ምሥጋናን በማየት እንዲከተሉና በጎ ሰዎች በምድር ላይ እንዲበረክቱ ያደርጋል፡፡

በዚህም አሥር በሚሆኑ የሙያ ዘርፎች ባበረከቱት በጎ ሥራ፣ ከብዙዎች መካከል ተመርጠው በየዓመቱ ‹‹የበጎ ሰው ሽልማት›› በሚል የሠሩት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በአገር ፊት ተነግሮ ይሸለማሉ፡፡

ዘንድሮም ለ11ኛ ጊዜ ይህ የበጎ ሰው ሽልማት ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል የሽልማት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

የዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በዘጠኝ የተለያዩ ዘርፎች የተበረከተ ሲሆን ሚዲያና ጋዜጠኝነት፣ ንግድ ኢንዱስትሪና ሥራ ፈጠራ፣ በጎ አድራጎት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ መምህርነት፣ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣትና በኪነ ጥበብ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረጉና በባህል በቅርስና ቱሪዝም ባሉ ዘርፎች ላደረጉት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቻቸው እናንተም ቀጥሉበት ሌሎችንም አስተምሩበት በማለት ምሥጋናና ሽልማት ተበራክቶላቸዋል፡፡

በመምህርነት ዘርፍ በርካታ ተግባርን በማከናወን የዓመቱን የበጎ ሰው ሽልማት የወሰዱት አቶ አዝማች ይርጋ ገበሬ ሲሆኑ፣ ማይምነትን በአሥር ዓመት ውስጥ ለማጥፋት ዕቅድ አውጥተው በማፅደቅ ማስጀመራቸው፣ እንዲሁም የመሠረተ ትምህርትን ያቀዱና ያስጀመሩ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል በንግድ ኢንዱስትሪና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ ኩሪፍቱ ሪዞርት ስፓ ሽልማቱን የወሰደ ሲሆን፣ የብርሃን ለሕፃናት በጎ አድራጎት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ እቴነሽ ወንድም አገኘሁ በበጎ አድራጎት ዘርፍ የተበረከተውን ሽልማት ሲቀበሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ደግሞ ሠዓሊ ወርቁ ጎሹ አሸንፈዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ኃላፊ የነበሩት ያየህይራድ ቅጣው (ዶ/ር) ደግሞ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነትን በአግባቡና በብቃት በመወጣት ዘርፍ የተሸለሙ ሲሆን፣ በሚዲያና በጋዜጠኝነት ዘርፍ ጋዜጠኛ ኤፍሬም እንዳለ፣ እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሙሉዓለም ገሰሰ ከተሸላሚዎቹ መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡

በትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘርፍ አስፋው ጃጀው ሲሸለሙ፣ በዘውዳዊው ሥርዓት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ በዓመቱ በልዩ ዘርፍ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1963 በሪቻርድ ፓንክረስት (ፕሮፌሰር) በወቅቱ በዋና ዳይሬክተርነት ይመሩት የነበረው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የ11ኛው የበጎ ሰው ሽልማት አንዱ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ተቋሙ ከምሥረታው ጀምሮ ላለፉት ስድሳ ዓመታት ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ማኅበራዊ ጥናቶች ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ነው፡፡

ተቋሙ በዋናነት ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም የጥናትና ምርምር ክፍል፣ የጥናት ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም ናቸው፡፡ የተቋሙ የጥናትና ምርምርት ክፍል የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናትና የጥናት ጉባዔዎችን በማዘጋጀት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ ከምሥረታው ጀምሮ ደግሞ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚያሳትመው የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት (ጆርናል ኦፍ ኢትዮጵያን ስተዲስ) ከፍተኛ መለያው ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ የተጻፉና መጻሕፍትን በማቅረብ ለተጠቃሚዎች እያገለገለ ያለ ሲሆን፣ ከሰባት ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ መንግሥታት የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች በዚሁ ቤተ መጻሕፍት እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡

ተቋሙ በእነዚህና መሰል ተግባራት ለአገርና ለሕዝብ ባበረከታቸው ጉልህ ተግባራት ተሸላሚ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...