Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

አጋዥ መጻሕፍትን ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለማድረስ

አቶ አህመዲን መሐመድ ተወልደው ያደጉት፣ የመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲስ አበባ ነው፡፡ ከዚያም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በኋላም እ.ኤ.አ. በ1985 ወደ አሜሪካ አቅንተው ካሊፎርኒያ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ከሚገኘው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተከታተሉበት የትምህርት ተቋም በአድሚኒስትሬሽን ማኔጅመንት አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ በቀድሞ የአዲስ አበባ ባንክ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ደግሞ በአንድ የግል ባንክ አገልግለዋል፡፡ በአሜሪካ ቆይታቸው ‹ላይብረሪ ኢንፎርሜሽን ፋውንዴሽን ፎር ኢትዮጵያ› የሚል በጎ አድራጎት በመመሥረት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መጻሕፍትን በማቅረብ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ላይብረሪ ኢንፎርሜሽን ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን እንዴት መሠረቱት?

አቶ አህመዲን– ወጣቶችን ማስተማር አገርን መገንባት መሆኑን በመገንዘብ ነው የመሠረትነው፡፡ በቅድሚያ ዓመታት በፊት የሠራሁት ለወጣቶች የሚውሉ መጻሕፍትን ማሰባሰብ ነበር፡፡ ይህንን እንቅስቃሴ ያደረግኩትም አሜሪካ ውስጥ ሲሆን፣ የማሰባሰቡን ሥራ ለማቀላጠፍ ስል ከሚያግዙኝ ሰዎች ጋር አብሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ለዚህ እንዲረዳኝም ላይብረሪ ኢንፎርሜሽን ፋውንዴሽን ፎር ኢትዮጵያ የሚል ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሥርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለመጀመርያ ጊዜ መጻሕፍት የለገሳችሁት መቼ ነበር?

አቶ አህመዲንእ.ኤ.አ. በ1994 ነው፡፡ በወቅቱ 5,000 መጻሕፍት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ላይብረሪ አስረክቤያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አጋዥ መጻፍትም አምጥተው እንደነበር ነግረውናል፡፡ ቢያብራሩልን?

አቶ አህመዲን፡– አዎ፡፡ ይህንን 2007 ነው ያደረግነው፡፡ በወቅቱ ብዙ ውጣ ውረድ ቢያጋጥመንም፣ ያመጣናቸውን 33 ሺሕ መጻሕፍት በ22 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ላይብረሪ ውስጥ እንዲገቡ አድርገናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሡሉልታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ደጀን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመን ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ ወልቂጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አዘዞ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት ይገኙበታል፡፡ 

ሪፖርተር፡- አሁን ደግሞ ለስተኛ ጊዜ ይዘው መጥተዋል ለማስገት እክል ገጥሞዎት ነበር በምን መልኩ ተጠናቀቀ?

አቶ አህመዲን፡- 20 ሺሕ መጻሕፍት፣ 15 ኮምፒዩተርና ላፕቶፖች፣ እንዲሁም ያገለገሉ 100 ኳሶች በኮንቴይነር ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓጓዝ ያደረግነው ከዘጠኝ ወራት በፊት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሰበሰቡት መጻሕፈት ምን ዓይነት ናቸው?

አቶ አህመዲን– ማጣቀሻ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- መጻሕፍቱ መቼ ነበር ጂቡቲ ወደብ የደረሱት?

አቶ አህመዲን፡- በጥር 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ የሚያገለግሉትም ከቅድመ መደበኛ እስከ አራተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በአጋዥነት ነው፡፡ በበጎ ፈቃድ ሥራ ነው ከ12 ትምህርት ቤቶች የተገኙት፡፡ ለማስጫን ‹‹በጎ ፈንድ ሚ›› ገንዘብ አግኝተናል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የረዱኝም አሉ፡፡ ከመጻሕፍቱ ጋር ለመምህራን ዩኒቨርሲቲ የሚሆን ወደ 34 ካርቶን መጻሕፍትም አለ፡፡ የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጻሕፍትና ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቧቸው ዕቃዎች አሉ፡፡ እዚህን በአንድ ኮንቴይነር አድርገን ነበር ወደ ኢትዮጵያ የላክነው፡፡ ሆኖም ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ወደ ሰባት ወራት ገደማ ተንከራተናል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመጫን 15 ሺሕ ዶላር ተከፍሏል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የገጠመን ችግር የግል ዕቃዎችና በበጎ ፈቃድ ለዕርዳታ የተባሉ መጻሕፍት አንድ ላይ ተጭነዋል በሚል ነው፡፡ ይህ መሆኑ ችግሩ አልታየኝም፡፡ ያልረገጥኩት ቢሮ የለም፡፡ ኮንቴይነሩ ወደብ በቆየ ቁጥር ኪራይ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ይግባና መንግሥት ጋር ይቀመጥ ሁሉ ብያለሁ፡፡ የሰማኝ ግን አላገኘሁም ነበር፡፡ ከስንት ውጣ ውረድ በኋላ ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲገባልኝ ደብዳቤ ተጽፎ ጉምሩክ ባለፈው ሳምንት እንዲገባ ፈቅዷል፡፡ ችግሩ ግን ጂቡቲ ላይ ከ10 ሺሕ ዶላር በላይ እንድንከፍል ተጠይቀናል፡፡ በወቅቱ መጽሐፉ እንዲገባ ቢደረግ ይህንን ሁሉ አንጠየቅም ነበር፡፡ መጻሕፍቱን ያመጣነው ለሕፃናት ነው፡፡ ስለ ትምህርት ጥራት ስናስብ ከሕፃናት ጀምሮ መሥራት አለብን፡፡፡ መንግሥት ካስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ግማሽ እንኳን ማሳለፍ አልተቻለም፡፡ የትምህርት መጻሕፍት ደግሞ ለሥርዓተ ትምህርቱ አጋዥ ናቸው፡፡ ለዚህ ልጆች ላይ መሥራት አለብን፡፡ በዚህ ሁሉ ምልልስ እኔ አልተጎዳሁም፡፡ የተጎዱት ወገኖቼ ናቸው፡፡ አመለካከት ላይ ያለውን ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ ዳያስፖራውም የሚሸሸው እምነት በማጣት ነው፡፡ ዳያስፖራውን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ መጻሕፍቱን ለማደል ያሰብነው ደብረ ብርሃን፣ አፋርና ወሎ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠየቁትን የመክፈል አቅም አለዎት? በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረጉ ነው መጻሕፈቱን ለማስገባት?

አቶ አህመዲን– መጻሕፍቱን ለተቸገሩ ተማሪዎች እንዲማሩበት አስቤ ነው ያመጣሁት፡፡ የተጠየኩትን ገንዘብ የመክፈል አቅም የለኝም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ ጓደኞቼና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት መጻሕፍቱ በሚገቡበት መንገድ እንዲተባበሩኝ እጠይቃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው ለአገሩ ከረሚንስ ውጪ ሊያበረክተው በሚችው ላይ ምን መራት አለበት ይላሉ?

አቶ አህመዲን፡- ከዳያስፖራው ይህንን ያህል ረሚታንስ ተገኘ ተብሎ በተደጋጋሚ ዜና ሲሠራ ይታያል፡፡ ነገር ግን ዳያስፖራው ሊያበረክተው የሚችለው የዕውቀት ሽግግር ቀላል አይደለም፡፡ በትልልቅ ቦታዎች ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሰሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በተዓማኒነታቸውና ኃላፊነትን በመወጣት ይታወቃሉ፡፡ ሥነ ምግባር አላቸው፡፡ ችሎታና ዕውቀትም አላቸው፡፡ ይህንን ለመጠቀም አገር ውስጥ ያሉ አሠራሮች መስተካከል፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ኔት ወርክ መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ዳያስፖው አገሩን ለመርዳት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን እዚህ ሲመጣ የሚገጥሙት መጉላላቶች ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርጉታል፡፡ ኢትዮጵያ ወልዳ አሳድጋ ለሌላ እየሰጠች ነው፡፡ ዳያስፖራው መጥቶ ተበሳጭቶ ስለሚመለስ ኢትዮጵያ ብዙ እያጣች ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...