ዕንቊጣጣሽ
እንኳን መጣሽ!!
ያዲስ ዓመት በር
የማለዳ ውብ ጀምበር
የጉም – ደመና ግርዶሽ
የዝናብ – ዶፍ ጥሎሽ
ያፈር – ጭቃ ድልጦሽ
የመብረቅ ብልጭታ ውጋት
የቸነፈር ጥፊ ምታት
የነጎድጓድ – ጉምጉምታ ልጋት
የክረምት ጭጋግ ድምር – ሕይወት
ሲያልፍ – ሲተካ ባዲስ ዓመት
አንቺ አንድ ዕለት
ያሮጌው ዓመት ማግሥት፡፡
አንቺ አንድ ዕለት
መባቻዋ ያዲስ ዓመት፡፡
ዕንቊጣጣሽ
እንኳን መጣሽ!!!
በያመቱ ያምጣሽ!!!
በአደይ አበባ አጊጠሽ
የተስፋ ስንቅ ሰንቀሽ
ጣጣሽን ከጀርባሽ ጥለሽ
ዕንቊሽን ብቻ ይዘሽ
ነይ!
አበባየሁ በይ!!!
- አሰፋ ጉያ ‹‹የከንፈር ወዳጅ››