Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹እናንተን ከመምከር በስተቀር ሌላ ሥራ የለኝም››

ትኩስ ፅሁፎች

ስለ ሰውነት የሚያስብ፣ የሚሠጋ ሁሉ በዚያ መንገድ እንዲያልፍ የሚመክሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ብዙ ነገር የሚረግፍለት ስለሆነ ምክሩን ከመደገፍ የማንቆጠብ መሆናችንን እየገለጽን፤ ሶክራቲስ በሐሰት ተከሶ በሀገሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት ከመቀበሉ በፊት ተግባሩን፣ ሥነ ምግባሩን በመከላከል (አፖሎጊያ) ከተናገረው ባጭሩ እንጠቅሳለን፡፡ ስለ ነፍስ ማሰብ መጠንቀቅ (ኤፒሜሊያ ፕስሂስ) እንደሚገባ በተነገረው ላይ እናተኩራለን፡፡

አቴናውያን ወገኖቼ ሆይ! ምንም እንኳ ብወዳችሁና ባከብራችሁ ከእናንተ ይልቅ ለሰማይ መታዘዝን እመርጣለሁ፡፡ እስከ መጨረሻው ጥበብን ከመከታተል አላቋርጥም፡፡ እንዲሁም በመንገድ ለምትገጥሙኝ ሁሉ እውነትን ከመጠቆምና ከማሳሰብ ቸል አልልም፡፡ እንደ ልማዴ እንዲህ እያልኩ፡፡ መልካም ወዳጄ ሆይ! በጥበባት ሀብት ዝነኛ የሆነችው የታላቋ ከተማ የአቴና ዜጋ ነህ፡፡ ብልጽግናን፣ ክብርን፣ ዝናን፣ የመሰሉትንም ሁሉ ለማከማቸት ይህን ያህል ስትደክም ለጥበብ፣ ለዕውቀት ለነፍስህ መሻሻል ምንም አለማሰብህ አያሳፍርህምን ለነዚህ ነገሮች የሚያስብ መሆኑን በመግለጽ ቢቃወመኝ ወዲያው ትቼው መንገዴን አልቀጥልም፡፡ እጠይቀዋለሁ፡፡ እፈትሸዋለሁ፡፡ የሚወደውን በጎነት (አሬቲ) እንደሚለው ያልያዙ ሆኖ ካገኘሁት እጅግ ውድ የሆኑትን ነገሮች ርካሽ አድርጎ፤ ዋጋ ቢስ የሆኑትን ውድ አድርጎ በመቀበሉ ሳልወቅሰው አላልፍም፡፡ ለሚገጥመኝ ሁሉ ሽማግሌም ሆነ ወጣት፤ በተለይም፣ ወገኖቼ፣ ሕዝቤ ለሆናችሁ ለእናንተ ይህን ከማድረግ አልቆጠብም፡፡ ይህ የግዜር ትእዛዝ ነው፡፡ አትጠራጠሩ፡፡ እኔ ለዚህ አገልግሎት ከመቆሜ የተሻለ ሌላ ዕድል አቴናውያን እንዳልገጠማችሁ አምናለሁ፡፡ እናንተን ከመምከር በስተቀር ሌላ ሥራ የለኝም፡፡ ወጣትም፣ ሽማግሌም ለአካላችሁ፣ ለሀብት ለንብረት ከምታስቡት የበለጠ ለነፍሳችሁ መሻሻል አስቡ፡፡ ለዚህኛው ቅድሚያ ስጡ፡፡ ደግነት ከሀብት የሚገኝ አይደለም፡፡ ሀብትንና ማናቸውንም ሌላ ነገር ሁሉ በግልም በማኅበራዊም ኑሮ ረገድ ለሰው ዋጋማ የሚያደርገው ደግነት ነው፡፡ ይህን በመናገሬ ወጣቶችን አሳስተሃል ትሉኝ እንደሆነ ግድ የለኝም፡፡

  • እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹ብፁዓን ንጹሐነ ልብ›› (2005)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች