Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ በአራተኛው የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ ያሰማችውን ተቃውሞ መንግሥት አጣጣለው

ግብፅ በአራተኛው የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ ያሰማችውን ተቃውሞ መንግሥት አጣጣለው

ቀን:

በክረምቱ ተጨማሪ የውኃ ድጋፍ አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ኢትዮጵያ ስታበስር፣ ግብፅ ግን ተቃውሞዋን አሰምታለች፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የግብፅን የንዴት ተቃውሞና መግለጫ መሠረተ ቢስና የተለመደ ‹‹የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ›› ብለውታል፡፡

እሑድ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የግድቡ ግንባታ በሚገኝበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የህዳሴውን ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን›› አብስረዋል፡፡

ግብፅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ በኩል በተመሳሳይ ቀን ምሽት ላይ ባወጣችው መግለጫ ሙሌቱን ‹‹ሕገወጥ››፣ ብላ፣ እ.ኤ.አ. በ2015 በሱዳን፣ በግብፅና በኢትዮጵያ የተፈረመውን የመርህ ስምምነት (Declaration of Principles 2015) የጣሰ ነው ስትል ኮንናለች፡፡ በተጨማሪም ግብፅ ሙሌቱ በቅርቡ በተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ጥላ ያጠላል ብላለች፡፡

በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር እ.ኤ.አ. በ2021 ከተቋረጠ በኋላ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በካይሮ የተጀመረ ሲሆን፣ ቀጣዩ ስብሰባ በመስከረም 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ድርድሩ እንደገና ሊቀጥል የቻለው በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ካይሮ ባመሩበት ወቅት ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በመነጋገር፣ በአራት ወራት ውስጥ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ከተስማሙ በኋላ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በወቅቱ ወደ ካይሮ ያመሩት፣ በጦርነት ከታመሰች ግማሽ ዓመት በሆናት ሌላኛዋ የተፋሰሱ አገር ሱዳን ጉዳይ መፍትሔ በሚያፈላልገው ስብሰባ ለመካፈል ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችና ባለሥልጣናት ግን ግብፅ በአራተኛው የውኃ ሙሌት ላይ ያወጣችው የቁጣ መግለጫ ከእውነታው የራቀ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ምንም የተጣሰ ነገር የለም፡፡ ግብፆች ያወጡት ነገር ትክክል አይደለም፡፡ የመርህ ስምምነቱ አልተጣሰም፡፡ በመርህ ስምምነቱ መሠረት የወጣ የሙሌት ሠንጠረዥ አለ፣ በእሱ መሠረት ነው አሁን የሞላነው፡፡ አሁን በቅርቡ የተጀመረው ድርድር የአገሮቹ መሪዎች በሰጡት መመርያ መሠረት ነው የተጀመረውና እየተካሄደ ያለው፡፡ አራተኛው ሙሌት በቅርቡ ከተጀመረው ድርድር ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ግብፆቹ ስለአራተኛው ሙሌት በደንብ ያውቃሉ፡፡ በተስማማነው መሠረት ነው የተሞላው፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የግድቡ ተደራዳሪ ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረው ከቆመበት መቀጠል እንጂ፣ አዲስ ድርድር አይደለም ሲሉ ተደራዳሪው አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር)፣ ሙሌቱ በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የለውም ብለዋል፡፡ ግብፅ ያወጣችውን መግለጫ በተመለከተ፣ ‹‹የእነሱ የሚዲያ እንካ ሰላንቲያ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ ነው፡፡ አሁን ያወጡት መግለጫም የተለመደ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ፍጆታ ነው፣ ለውስጥ ፍጆታ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ እኛ የእነሱ የሚዲያ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡ ይኼ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያከብረው ፕሮጀክት ነው፡፡ ግድቡ የትብብር እንጂ የፉክክር ምንጭ መሆን የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የቀድሞ የሱዳን የግድቡ ተደራዳሪ በበኩላቸው፣ ግድቡን በተመለከተ በቴክኒክ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረስ ቀላል ነበር ይላሉ፡፡

‹‹መሬት ላይ ባለው እውነታና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ የሦስቱም አገሮች ተደራዳሪዎችና ባለሙያዎች እንስማማለን፡፡ ግድቡ በተፋሰሱ አገሮች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያመጣም፡፡ ነገር ግን የግብፅ ፖለቲከኞች ሁልጊዜ የግድቡን ጉዳይ ከቴክኒክ ወደ ፖለቲካ ይጠመዝዙታል፡፡ በእርግጥ ግብፆች የሚፈሩት ይኼኛውን ግድብ ሳይሆን፣ ወደፊት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝና ዓባይን በሚመግቡ ወንዞች ላይ ልታከናውን ባሰበቻቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች ነው፡፡ ለዚህም ነው ቀድማ ስምምነት አስገዳጅ መፈራረም የፈለገችው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አራተኛውን ሙሌት ‹‹የመጨረሻው ሙሌት›› ማለታቸው ግን ብዙዎችን ያላስማማ ነጥብ ሆኗል፡፡ የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ (ኢንጂነር) ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ ‹‹በጉዳዩ ላይ ለመናገር ፈቃድ የለንም፡፡ መንግሥት ባለው መሠረት ብትጠቀሙ የተሻለ ነው፤›› በማለት ከማብራራት ተቆጥበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጨረሻ ሙሌት ነው ቢሉም በቀጣይ የሚያዝ ውኃ መኖሩን ግን ሌሎች ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...