Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል አየር መንገዶች በአገር ውስጥ መደበኛ በረራ መሳተፍ እንዲችሉ ሊፈቀድላቸው ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የአቪዬሽን ፖሊሲው ባይፀድቅም የግል ባለሀብቶች በሌሎች የአቪዬሽን ሥራዎች እየተሳተፉ ነው››

የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን

የግል አየር መንገዶች ወደ ክልሎች በመደበኛ በረራ መሳተፍ እንደሚችሉና ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጪ የማይፈቀደውን መደበኛ በረራ ላይ መሥራት ከፈለጉ ማመልከት እንደሚችሉ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እንደተናገሩት፣ የግል አየር መንገዶች ከዚህ በፊት የማይፈቅድላቸው ቢሆንም፣ አሁን ግን ‹‹ምንም የሚከለክላቸው ነገር የለም›› ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ‹‹እኔን መጥተው ቢጠይቁኝ ዘርፉ ክፍት እንደሆነ ሊያውቁ ይችላሉ፤›› ሲሉም አስረድዋል፡፡

የግል አየር መንገዶች የአገር ውስጥ መደበኛ በረራ ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ፈቃድ ማግኘት እንደሚችሉ ‹‹በግልጽ እንደተነገራቸው››፣ እንዲሁም በሌሎችም የአቪዬሽን ዘርፎች መሳተፍ እንደሚችሉ ነው ሌሎችም የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች የተናገሩት፡፡

የግል ዘርፉ በበርካታ የአቪዬሽን ሥራዎች እንዲሳተፍ የሚፈቅደው ለበርካታ ዓመታት በዝግጅት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ፖሊሲ፣ የዝግጅት ምዕራፉን እንዳጠናቀቀና ‹‹በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት›› ግምገማ እየተደረገበት እንደሆነ ኃላፊዎቹ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ የአቪዬሽን ፈጠራ ኤክስፖ በሳይንስ ሙዚየም ለማካሄድ እየተዘጋጀ እንደሆነ በማስመልከት፣ ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጌታቸውና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑ አቶ ዳንጌ ቦሩ በተገኙበት መግለጫ ተሰጥቶአል፡፡

‹‹የአቪዬሽን ፈጠራ ለላቀ ተወዳዳሪነት›› በሚል መሪ ቃል ሊካሄድ የታቀደው የአቪዬሽን ኤክስፖ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በኤክስፖው ላይ ድሮንን ጨምሮ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ለዕይታ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡

ባለሥልጣኑ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ኢትዮጵያን የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ ማቀዱ ተገልጾ፣ ብሔራዊ አገር አቀፍ የአቪዬሽን ልማት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ እንደሆነና የአቪዬሽን ፈጠራ ማዕከል ለመገንባትም እየተሠራ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የአቪዬሽን ፖሊሲው ዝግጅት ረዥም ጊዜ መውሰዱንና አለመፅደቁን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ታይቶ ለሌላ የመንግሥት አካል በመቅረብ ዕይታ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሆኖም በአቪዬሽን ፖሊሲው የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ግን መተግበር እንደተጀመሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በጣም ጥቂት ከሚባሉ ጉዳዮች በስተቀር በፖሊሲ ምክንያት መሥራት እየፈለግን የማንሠራቸው ጉዳዮች የሉም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የኤርፖርት መሠረተ ልማት የፌዴራል መንግሥት ሚና ብቻ እንደሆነ ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ አሁን ግን የግል ባለሀብቶች፣ የክልል መንግሥታት፣ ከተማ አስተዳደሮችና መለስተኛ ተቋማት ለራሳቸው አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለንግድ አገልግሎት ኤርፖርት ገንብተው እንዲያስተዳድሩ ተችሏል፤›› ብለው፣ ፖሊሲው ባልፀደቀበት ሁኔታ ወደ ተግባር መቀየሩን ገልጸዋል፡፡

‹‹ቀላል የማይባሉ›› በተለይ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች በግል ባለሀብቶች አማካይነት እየተገነቡ እንደሆነ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ለአየር መንገድ ማረፊያ ግንባታ ፈቃድ አግኝተው እየገነቡ ያሉትን የባለሀብቶችና ድርጅቶች ዝርዝር ከባለሥልጣኑ ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ሳይካ ቀርቷል፡፡ በተያያዘም የግል አየር መንገዶችን በአገር ውስጥ የመደበኛ በረራ ሥራ ለመሳተፍ ስላላቸው ፍላጎት ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች