Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች በተሰጡ ብድሮች ላይ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ ማድረጋቸው ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከፍተኛ የወለድ መጠን 23 በመቶ ማለፉ ተጠቁሟል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በብድር ዓመታዊ ዕድገት ላይ የ14 በመቶ ገደብ መጣሉን ተከትሎ ባንኮች የወለድ ምጣኔ ላይ ማስተካከያ ማድረጋቸው ታወቀ።

በባለፈው ወር መጀመሪያ ተግባራዊ የተደረገው የወለድ ገደብ፣ ባንኮች በ2015 መጨረሻ ላይ በሰጡት ብድር ላይ 15 በመቶ ተጨማሪ ብቻ እንዲያበድሩ ያስገድዳል።

ዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ያለመው ገደቡ የባንኮች የወለድ ገቢ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ ባንኮች የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ ለማድረግ መገደዳቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሥራ ኃላፊ ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት የባንክ ኢንዱስትሪ አማካይ የወለድ መጠን 14.5 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ የወለድ መጠን ወደ 21.5 በመቶ ይጠጋል።

ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንክ ገደብ ከተጣለ በኋላ ከፍተኛ የወለድ መጠን ከ23 በመቶ ማለፉን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ተዋንያን ተናግረዋል።

ባንኮች ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙት እንዲሁም የወጪያቸውን የአንበሳ ድርሻ የሚሸፍኑት ከወለድ ገቢ እንደመሆኑ መጠን ማስተካከያ መደረጉ ትክክል ነው የሚሉት አንድ የግል ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ባንኮች የሚያወጡት ወጪ ከኪራይ አኳያ ቢታይ ከ100 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ ታይቶበታል ብለዋል።

‹‹የቅርንጫፍ ኪራይ ዋጋ በካሬ ቢታይ ከ60 ብር ወደ 120 ብር ሊያድግ ችሏል›› የሚሉት የሥራ ኃላፊው፣ የደመወዝ ወጪም ዘርፉ ውስጥ በሚታየው የሠራተኛ የመቀማማት ያልተገባ ፉክክር ከ50 በመቶ በላይ የዓመታዊ ጭማሪ አሳይቷል በማለት አክለዋል።  

በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር 31 የደረሰ ሲሆን፣ አሥር ባንኮች ዘርፉን የተቀላቀሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ነበር። በዘርፉ የተሰጠው የብድር ክምችት ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ የተሻገረ ሲሆን፣ የብድር ክምችት መጠን በተመሳሳይ ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ተሻግሯል።

ሁሉም ባንኮች ብድር በሚሰጡበት ወቅት ከተበዳሪዎች ጋር የሚፈራረሙት ውል የብድር ወለድ ምጣኔ ማስተካከያ ማድረግ የሚፈቅድላቸው ሲሆን፣ በቅርቡ የተደረገው ጭማሪ ይህንኑ የሚያስጠብቅ እንደሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን ሙሐመድ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ጭማሪ መደረጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የተጣለው የ14 በመቶ ገደብ ብድርን ሊያስወድድ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።

የብሔራዊ ባንክ ዓላማ በተዘዋዋሪ የብድርን ወለድ እንዲወደድ በማድረግ የብድር ፍላጎት እንዲቀንስ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን፣ የተደረገው የገደብ ጭማሪ ማስከተሉ ይጠበቃል ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የዋጋ ግሽበትን 20 በመቶ ለማውረድ ያቀደ ሲሆን በ2017 ደግሞ ወደ አሥር በመቶ ለመቀነስ ይሠራል ብሏል።

በሐምሌ ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 29.3 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር ትንሹ ነው።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች