Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዳዲስ ባንኮች በመንግሥት የተጣለው የ14 በመቶ የብድር ገደብ እንዲነሳላቸው ጥያቄ ሊያቀርቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳንኤል ንጉሤ

ባለፉት ሦስት ዓመታት የባንክ ዘርፋን የተቀላቀሉት አዳዲስ ባንኮች መንግሥት የጣለው የ14 በመቶ የብድር ገደብ እንዲነሳላቸው፣ ለኢትዮጵያ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ሊያቀርቡ መሆኑን ለሪፖርተር ገለጹ።

የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንሱ የሚችሉ በርካታ የፖሊሲ ዕርምጃዎች መወሰዱንና ወዲያውኑ ሥራ ላይ እንዲውሉ መወሰኑ ይታወሳል።

የዳይሬክተሮች ቦርዱ ካሳለፋቸው አምስት ውሳኔዎች መካከል አንዱ የባንኮች ብድር ዕድገት ከ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ በ14 መቶ ጣሪያ መገደብ ሲሆን፣ ሁሉም ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚሁ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲስተካከል ውሳኔ የሚለው ይገኝበታል፡፡

የሒጅራ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሐሰን መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ውሳኔው አዲስ በተመሠረቱት ባንኮች እንቅስቃሴ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ በተለይ አዳዲስ ባንኮች በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት አብዛኛውን ተቀማጭ ገንዘባቸውን ብዙ ቅርንጫፎች በመክፈትና የሰው ኃይል በመቅጠር ላይ ኢንቨስት እንዳደረጉት ገልጸው፣ ውሳኔው ተገቢ አይደለም ብለዋል።

‹‹ረዥም ጊዜ የቆዩ ባንኮች ሰፊ አድማስ ስላላቸውና ከዚህ በፊት ፋይናንስ ያደረጉት ትልቅ ገንዘብ በመሆኑ፣ 14 በመቶ  ገደብ ያን ያህል ጫና ላያሳድርባቸው ይችላል፤›› ብለዋል። አክለውም ይህንን በሚመለከት ከሌሎች በቅርብ ከተቋቋሙ ባንኮች ጋር በመሆን ብሔራዊ ባንክን ለመጠየቅ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዘምዘም ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ለባንኮች የኢንቨስትመንት ገደብ በመኖሩ ምክንያት አብዛኛውን የባንክ ሥራ ላይ ሲሠሩ እንደቆዩ ጠቅሰው፣ በምሳሌነትም ዘምዘም ባንክ በሁለት ዓመት ውስጥ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ላይ እንዳልተሳተፈ ገልጸው፣ ብሔራዊ ባንክ የወሰነው ውሳኔ ለአዳዲስ ባንኮች ትልቅ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል።

እንዲሁም ውሳኔው ትክክል እንዳልሆነና አዳዲስ ባንኮች በፐርሰንት ሳይሆን እንዳገኙት ገቢ መጠን ተተምኖ የብድር ገደቡ መወሰን እንደነበረበት ጠቅሰው፣ ‹‹ውሳኔው ነባር ባንኮችን ትልቅ ሆነው ይቆዩ፣ አዳዲሶቹ ደግሞ ይዘጉ ከማለት ያልተናነሰ ነው፤›› ብለዋል። አክለውም ጉዳዩ ለአዳዲስ ባንኮች በተለየ ሁኔታ ካልታየላቸው በስተቀር የመቀጠላቸው ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚገባ፣ ፖሊሲው በአጠቃላይ አዳዲስ ባንኮችን የሚጎዳ ስለሆነ ባንኮቹ ብሔራዊ ባንክን ለመጠየቅ እንቅሰቃሴ መጀመራቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የባንክ ዘርፍ ባለሙያው አቶ አብርሃም ተሬቻ በበኩላቸው፣ አዳዲስ ባንኮች በደንበኛም ሆነ በተቀማጭ ገንዘባቸው በቂ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት ይሆናል በሚባልበት በዚህ ወቅት ባንኮቹ ከፍተኛ ውድድር ስለሚያጋጥማቸውና ውድድሩን ሊወጡት ስለማይችሉ፣ እነሱን ለመደገፍ ሲባል አዲስ ፖሊሲ ቢወጣ መልካም ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፈቃዱ ደግፌ በጉዳዩ ላይ  ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ከባንኮቹ ጥያቄ እስካሁን እንዳልቀረበና በግላቸው ምንም እንደማያውቁ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች