Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የአጋር አካላት ኢንቨስትመንት በቂ እንዳልሆነ ተጠቆመ

ለመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የአጋር አካላት ኢንቨስትመንት በቂ እንዳልሆነ ተጠቆመ

ቀን:

የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ለሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽነት መሠረታዊና ቁልፍ ተግባር ቢሆንም፣ የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ ያተኮረውና ለሦስት ቀናት የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲጀመር ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ ክብካቤው የሚፈልገውን ያህል አገልግሎት መስጠት የተሳነው ለጋሾች ለዘርፉ የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት መጠን በበቂ ሁኔታ ባለማደጉ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ተንሰራፍቶ ለብዙ ሺሕ ሰው ሞትና ከፍተኛ የሆነ የጤና ሥጋት ሆኖ የነበረው ኮቪድ-19 በአንድ በኩል ጠቃሚ ትምህርትና በቂ ዝግጁነትን ቢያስጨብጥም፣ በአንፃሩ ደግሞ በመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ እጅግ የከፋ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ ማለፉን ሚኒስትሯ ገለጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራበትና የለጋሽ አገሮች ኢንቨስትመንት ቢያድግ እንደ ኮቪድ ያሉ የጤና ችግሮችና ወረርሽኞች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ በቀላሉ መከላከል ይቻል እንደነበርም አውስተዋል፡፡

ስለሆነም የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤ በተፈለገውና በበቂ ሁኔታ ኢንቨስት ከተደረገ የኅብረተሰቡ የጤና ሥጋቶች ሲከሰቱ ቶሎ ምላሽ መስጠት የሚችል የማይበገር የጤና ምላሽ ለመገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጉባዔው የተዘጋጀው በሁሉም አገሮች ጥራቱንና ፍትሐዊነትን የተላበሰ የመጀመርያ ጤና ክብካቤን ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ ነው፤›› ያሉት የጤና ሚኒስትሯ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የውጭ ድጋፍን ብቻ ሳይጠብቁ የአገር በቀል ፋይናንስን በመጠቀም የክብካቤውን ተደራሽነት ለማስፋፋት ብሎም ለማጠናከር ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በውሳኔ ሰጪነትና በጤና ዕቅድ ተግባራዊነት ላይ የየአካባቢው ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ከጤና ሚኒስትር ሊያ (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በበይነ መረብ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የመጀመርያ ደረጃ ጤና ክብካቤን በትክክል ከሥራ እንዲውል ካደረጉ ሕዝቡ የሚፈልገው የጤና አገልግሎት 90 ከመቶ ያህል እንደሚሳካለት ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የሕዝቡ በሕይወት የመኖር ዕድሜው በ2022 ዓ.ም. በሦስት ነጥብ ሰባት ዓመት ከፍ ይላል ተብሎ መገመቱን ገልጸው፣ ለዚህም ዕውን መሆን የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ጠንካራ የሆነ አገር በቀል ፋይናንስ መኖር ወሳኝ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ለማበልፀግና ተደራሽነቱንም ለማስፋት ለምታካሂደው እንቅስቃሴ ስኬታማነት፣ የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በጉባዔው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የጤና ክብካቤ አገልግሎትን ለሁሉም ኅብረተሰብ ለማዳረስ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለተግባራዊነቱም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አማካይነት በገጠር ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎትን በማዳረስ ላይ መሆኑንና ይህ ዓይነቱም አካሄድ ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በስካይ ላይት ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ የተከናወነውን ይህንኑ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ያዘጋጁት የጤና ሚኒስቴርና ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ፕራይመሪ ሔልዝ ኬር ሲሆኑ፣ አስፈላጊውን የፋይናንስ ወጪ የሸፈነው ደግሞ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የብሉምበርግ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...