በአንለይ ጥላሁን ምትኩ
ብቸኝነት
ራስ ማማጥ
ራስ መዋጥ
– ኅዳር 19 ቀን 1982 ዓ.ም.
…፩…
የጥበብ ሰው አሰፋ ጉያ፣ የተለጠጠን ዓለም የሚሰበስብ፣ ቅጥ ያጣን መልክ (ቁመና) ቅርፅ የሚያስይዝ ባለብርቱ ምናብ ገጣሚ፣ የልብ ወለድ ደራሲና ሠዓሊ ነው፡፡ ‹‹የከንፈር ወዳጅ›› በአመዛኙ ብቸኝነቱ የፈጠረው፣ ቁዘማ (ተብሰልስሎት) የወለደው ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ በግጥሞቹ ምናቡ ወደ ሰማይ ይነጠቃል፣ ምድር ላይ ይወድራል፡፡ ከላይ ሰማይን ጎባባውን – አካል፣ ከሥር አፈርን – እስትንፋስ ሰጥቶ በምናቡ ይቃትታል፡፡ እነሆ:-
አትመተር … ጅምር – የለህ
አትሰፈር … መጠን – የለህ
አትደረስ … ድንበር – የለህ
በማለት የትየለሌነቱን ያሰርፃል፣ ይተክላል፡፡ በእርግጥ የህሊናን መዋለል፣ የልቦናን አለመርጋት በጊዜ ዥዋዥዌ ቀንብቦ በሰማይ ጥላ ሥር ሲዳኝ የባይተዋርነት ስሜት ያጠላል፡፡ ስለሆነም የባዶነት ተቃርኖን እጅግ ተራቀቀበትና ተቀኘ፡፡
ግዙፍ – አካል… እልፉ – ዓለም
ድንበር-የለህ … ቋሚ – ቀለም
ጠዋት ፈካ … ቀኑን ጠየም
ማታ ቀላ … ሌቱን ጨለም
እዚህ ላይ ‹‹ሰማዩ!›› ከጊዜ ጋር ያበረ ይመስል ቅርፅና መልኩን እየለዋወጠ አልጨበጥ ማለቱ ምናቡን እንዲቧጥጥ አስገደደው ገጣሚውን ይቀትራል፡፡ የስሜቱ አለመጨበጥ፣ የህልሙ አለመቋጠር ያንገበግበዋል፡፡ አብዝቶ ይመሰጣል፣ ይቃትታል፡፡ እነሆ:- …ሐሳብ …ብቻ …ሐ…ሳ…ብ…
ብላሽ!…ብላሽ – ሐሳብ
የለው ድምር የለው ብዜት
መሀን – ሐሳብ ባዶ ውጤት፡፡
ባለቅኔው አሰፋ፣ ሐሳብ አርግዞ በጠና ምጥ የሚገላገል የኪነ ጥበብ ሰው ነው፡፡ አወላለዱ በግጥምም በሥዕልም የሆነባቸው ጊዜያት በርካታ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ለአብነት ያህል እንጥቀስ፡፡
ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው ሁለት ግጥሞች ማለትም ‹‹ተጠየቅ? አንተ ሰማይ!›› (ገጽ 23 እስከ 25) እና ‹‹ብላሽ – ሐሳብ›› (ገጽ 14) የተፀነሱትም ሆነ የተጻፉት ‹‹በተመሳሳይ›› ስሜት ወይም ተብሰልስሎት ወቅት መሆኑን የሚጠቁም ጽሑፍ በ‹‹ሰምና ወርቅ›› በ2012 ዓ.ም. ከታተመው የደራሲው መጽሐፍ ላይ እናገኛለን፡፡ እነሆ:-… በየትም ሥፍራና የየዕለት ክስተት በሆነባት፣ ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ ከበዛባትና ከተንሰራፋባት ከዚች ትንሽ ዓለም ውስጥ ሰው ሆኜ ከተፈጠርኩ ‹እንዴት የራሴንና የዘመኔን ጥያቄ መመለስ አቃተኝ?› ብዬ ራሴን ደጋግሜ ጠየቅኩ፡፡
በየዕለቱ ጥያቄው እያብሰለሰለኝ፣ በሒደት አንዳች ነገር በውስጤ ይሰማኝ ጀመር፡፡ ከወዳጅ አይዋሱት፣ ከአዋቂ አይጠይቁት ነገር ሆነና የብቸኝነት ስቃይ ተናነቀኝ ጀመር፡፡ በቃላት አይከትቡት፣ በድምፅ አያንጎራጉሩት ሆነብኝ፡፡ ብቸኝነት፣ ራስ ማማጥ-ራስ መዋጥ ሆነብኝ፡፡
…እነሆ ፥ ምጡ ጀመረ፡፡ አንዳች ነገር ሊወለድ ነው፡፡ በረታብኝ፣ ጠናብኝ፣ በቃ ማማጥ፣ ማማጥ፣ ማማጥ ብቻ… ሆነ፡፡ (ገጽ 147) የጥበብ ሰዎች በውስጣቸው የቋጠሩትን ስሜትና ሐሳብ አርግዘው ለወራት ብሎም ለዓመታት የሚዘልቁ ስለመሆናቸው ተጨባጭ ማስረጃ ይሆነናል፣ ጋሽ አሰፋ፡፡
ወደ ተነሳንበት ነጥብ እንመለስና ተጨማሪ ማስረጃ እንጥቀስ፡፡ ‹‹ከግንቦት 16 ቀን 1975 ዓ.ም. ጀምሮ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በውስጤ ተጭረው እስከ መስከረም 1976 ዓ.ም. መገባደጃ ድረስ ሳያሰልስ ውስጤን ሲያተራምሱ ከረሙ፡፡›› (ገጽ 147)
ደራሲው በውስጡ ተሰማኝ ያለውን ሀቅ የተረዳው ዘግይቶ ነው፡፡ እሱ ‹‹በግንቦት 16 ቀን 1975 ዓ.ም. ጀምሮ›› እንደሆነ ቢነግረንም… ነገር ግን ቀድሞውኑ ግራ መጋባት፣ ቁጭትና የብቸኝነት ስሜት ያጠላበት ግጥም መቀኘቱን ልብ ያለው አይመስልም፡፡ ለዚህ ማስረጃዬ ‹‹ብላሽ-ሐሳብ››ን (በየካቲት 13 ቀን 1975 ዓ.ም.) መድረሱ ነው፡፡
ይበልጥ ግልጽ ይሆን ዘንድ ‹‹የዘመኑ ጣር›› በሚል ርዕስ ከሰፈሩትና እኔም ከላይ በተከታታይ ከጠቀስኳቸው አንቀጾች በተከታይነት የሰፈረውን እነሆ:- ‹‹ʽየችግር እንብርት… የድህነት ምስል… የድህነት አውታሮች… የድሆች መንደር… የችግር ስብስብ…’ ላይ ያተኮሩ ብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ሐሳቦች… መልስ አልባ ጥያቄዎች… ተግተለተሉብኝ፡፡ ውጥርጥር፣ ትክዝክዝ… ዝም ብዬ ወደአልታወቀ ሥፍራ ማቅናት… መሄድ፣ መጓዝ …መጓዝ …በሐሳብ ጭልጥ፣ ጭልጥልጥ ብዬ መንጎድ… ሆነ ክራሞቴ፡፡›› (ገጽ 147)
ገጣሚው ይህን ስሜቱን ‹‹የዘመኑ ጣር›› ብሎ የሚጠራው ሲሆን የመነጠል፣ የብቸኝነትና የሕመሙ ማስገሪያ የሚሆኑ ግጥሞች ተቀኝቷል፡፡ ማስታወሻ አስፍሯል (ሰምና ወርቅ ገጽ 147-152 ልብ ይሏል)፡፡ ቡርሹንም ገርቷል፡፡ ስለሆነም ‹‹የዘመኑ ጣር›› የተሰኘው የሞዛይክ (በቆዳ ቁርጥራጭ የተሠራ) ሥዕል የስሜቱ ወይም የምናቡ ማረፊያ ቢመስልም ቅሉ ከስድስት ዓመታት በኋላም ቢሆን ‹‹ብቸኝነት››ን በስንኝ ቋጥሯል፡፡ ይህ ሁኔታ በሌሎች ሥዕሎችና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ መካከል ጥብቅ ትስስር ስለመኖሩ ጠቋሚ በመሆኑ ለተጨማሪ ጥናት ይጋብዛል፡፡
….፪….
ባየር ላይ መብረሩ
ፍሬ እየለቀሙ… የትም እያደሩ
ሲያሻ እየዘመሩ
የትም እየዞሩ
አሰኘው መኖሩ፡፡
ገጣሚው፣ ከሰማይ በታች ያሉ ጉዳዮችን በሙሉ ያሽሟጥጥባቸዋል፡፡ በተቃርኖ ቁሞ ‹‹ከፀሐይ በላይ (አዲስ ነገር)›› በሚል ርዕስ በከተበው ግጥሙ ‹‹ከፀሐይ በታች፣ አዲስ ነገር የለም›› የሚለውን አባባል ሽሮታል፡፡ ከእያንዳንዱ ህልውና ጀርባ የሆነ ኃይል (ሥውር ምስጢር) እንዳለ አስረግጦ ይገልጻል፡፡ እነሆ:-
ለዘመናት ብትነጂ
በጨረርሽ ብትቀጂ
በቃጠሎሽ ብትነጂ
ሕግጋቱ – የተፈጥሮ
ካንቺም አለ ተሰውሮ
ገጣሚው ይህን ሥውር ኃይል (ሥውር ሚዛን) በሌላኛው ‹‹ሚዛን የለሽ ሚዛን›› ግጥሙ ምናቡን ለጥጦ ይሞግተናል፡፡ የተቃርኖ ምልከታን ህፀፅ አጉልቶ፣ ጥርጣሬን ያፀድቃል፡፡ ያም ሆኖ ትኩረቱ ሰውና ሰው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሰውን ህልውና በተለያየ ሚዛን አጮልቆ ይመለከታል፡፡
ውፍረት – በቅጥነት…
ክብደት በቅለት … ተመዘኑ፤
ልስላሴ በሻካራ…
ሙቀትም በቅዝቃዜ… ተወሰኑ፤
እያለ ይቀጥልና በመጨረሻ ላይ ቀጥለው በሰፈሩት ስንኞች አማካይነት መሠረት ነቅናቂ ጥያቄዎች ያነሳና ይሞግታል፡፡
ሚዛኑስ በምን ሚዛን ተከወነ?
ውጤቱስ በማን ተበየነ?
በማለት መጠራጠርን ያፀድቃል፡፡ ነባሩን አመለካከት ያጠይቃል፡፡ በተጨማሪም በ‹‹ወፉ ሰው›› ግጥሙ አማካይነት ሰውነትን ያስሳል፡፡ ፍላጎቱና ተፈጥሯዊ ማንነቱ ሲምታቱ… ከዛም ሰው መሆን ምርጫም ግዴታም ሆኖ ተገልጧል፡፡ ምናባችን ውስጥ ወለል ያለ ቤት ይሠራል፡፡ ዞረን ዞረን ምርጫችን ሰውነት ይሆናል፡፡
…ቢሆንም…
…ባይሆንም…
ሰው መሆን ተሻለው፡፡
በሚል ተተርጉሟል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ጉዳዩ መሆን ወይም አለመሆን ነው›› እንዲሉ በምርጫህ ህልምህን ትቋጥራለህ ወይም ትጥላለህ፡፡ ከፈቃድ ጋር ተዋደህ፣ ተጋምደህ በጥልቅ ምልከታ ራስህንና አካባቢህን (ዙሪያህን) ከመዘንከው የተሻልክ መሆንህ ጎልቶ፣ ነጥሮ ይታይሃል – ያለ ይመስለኛል፡፡ ሰውነትን ማፅደቂያ፣ መትከያ ስንኞች ናቸው፡፡ ያልተዛነፈ ምሰሶ ይተክላሉ፡፡ ቀታሪ ነው፡፡ ሁሉም ነገር መሆን የቻለው መሆን ስላለበት ነው – የሚለውን በአጽንኦት ይጠቁማል፡፡ የሁሉም ምንጭ ሰው ሆኖ መገኘት ነውና ያጀግናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መመረጣችሁንና መጠራታችሁን ታፀኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ›› መባሉን ማስታወሱ የግጥሙን መልከ ብዙነት ያፀናል፡፡ ለዚህም ይመስላል ‹‹ሥነ ጽሑፍ አንድም ብዙም የሆነ ጥበብ ነው›› የሚባለው፡፡
ከዚህም አንፃር ግጥም የልዕለ ተፈጥሮን ረድኤት መግለጫ ጥበብ ነው፡፡ ቀታሪነቱ የላቀን ጉዳይ በላቀ ቋንቋ ወይም መንገድ የሚያቀርብ መሆኑ ላይ ነው (ግጥም ቀታሪ ጥበብ ነውና)፡፡ ግጥሙ በመጀመርያዎቹ ሁለት አንጓዎች በፅኑ መሠረት ላይ ቆሞ የሰውን ልጅ የነፃነት እሴቶች ፅኑነት በማሰስ አስረጅ ስንኞችን በማስከተል በስሜት ይገሰግሳል፡፡ ሆኖም ጉዞው በምክንያት ተረትቶ ምኞት ይድበሰበሳል፡፡ ጥፋትን (ሞት እንበለው ይሆን) አምርሮ ይሸሻል፡፡ ነፃነትን በምናብ መዳፍ አፈፍ ለማድረግ መውተርተሩ ከንቱ ይሆናል፡፡ የሰውን ልጅ ውስንነቶች አጉልቷል፡፡ በሌላ ፅንፍም ሰውነትን አልቋል፡፡ አፅድቋል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ካንቴሜር ‹‹በግጥሞቼ እስቃለሁ-በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አዝናለሁ›› ማለታቸው፡፡ ቀታሪ ነው፡፡
ገጣሚው ሰውነትን (ሰው መሆንን) ካላቀባቸው ግጥሞች መካከል ‹‹ወፉ ሰው›› እና ‹‹ፈረሱ ሰው›› ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተመጋጋቢ፣ ሠልፈኛ ስንኞችንና ጭብጦችን የያዙ ናቸው፡፡ ሌላው መነሳት ያለበት ድንቅ ግጥም ‹‹ተናገር አንተ አፈር›› ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሥነ ግጥም ታሪክ ታትመው ካነበብናቸው የተለየና አዲስ ጭብጥ (ምልከታ) ያስተዋወቀ በመሆኑ ገጣሚውን ልዩ ቦታ ያሰጠዋል፡፡ ‹‹ተናገር አንተ አፈር›› ዘይቤያዊ አገላለጽ ነው፣ እንቶኔ ዘይቤ፡፡ ‹‹አፈርን›› በማወያየት፣ በመለመን እንዲሁም ‹‹በጥያቄ ድምፀት›› ያናግረዋል-ተራኪው፡፡ ኧረ ያፋጥጠዋል ማለት ይቀላል፡፡ ‹‹ምነው አፈር-ላፈር-ባፈር መፋጀቱ›› በማለት፡፡ በርግጥ የግጥሙ ርዕስ እንቶኔ ቢሆንም ስንኞቹ የተዋቀሩት በተምሳሌት ዘይቤ ነው፡፡ ሰውን ባፈር በመመሰል፡፡ እሱ አይወደኝ መከራው አይለቀኝ-እንዲሉ፡፡ ያም ሆኖ ተጨማሪ ዘይቤያዊ አገላለጽ የተሸከመነው፣ ምፀት ዘይቤ፡፡ ስላቁ በፈጣሪው ላይ ይመስላል፡፡ ሞቶ ተቀብሯልና (በልጁ) ክብሩን ለማግኘት በሞት መርከብ ላይ አዳሜ ለመሳፈር ይራኮትልሃል፡፡ ያው አፈር-ፈጣሪን፣ አገርን (ቤትን)፣ የተሸከምነውን ሥጋ፣ ከንቱነትን… ይወክላል፡፡ እንዲሁም አፈር መድኃኒትም (ፈውስ) ነው፡፡ ክብርና ሞገሱ ካንተው – ምነው ጥድፊያው? የሚል ይመስላል፡፡
ስለሆነም ‹‹ካንተው – ከሆነ ፍጥረቱ›› ሲል የሰው (የፍጥረት ሁሉ) ምንጩ አንተ ከሆንህ… እንዳለው እንረዳለን፡፡ ‹‹ያዳም – የሰው ልጅ ግኝቱ›› ሲል ደግሞ ያ የጥንቱ አዳም (የሰው መገኛ) መሠረቱ -አንተ ከሆንክ መነሻውም መድረሻውም ‹‹ምነው አንተ ለሰው፣ ሰውም ላንተ መፋጀቱ›› እንዳለ እንገነዘባለን፣ ሽሙጥ (ምፀት) መሆኑ ነው፡፡
ግጥሙ ቀርነት የለውም፡፡ አይጎረብጥም፡፡ እንቡጥ አመልማሎ ነው –እያደር ይፈካል፡፡ አፈር ብለው አያፈሱህ÷እህል ብለው አያፍሱህ- ሆነና ነገሩ የመረረ የባይተዋርነት ጥላ የሸፈነው ስሜት አዝሏል፡፡ ቀታሪ ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ››ን ያስታውሰናል፡፡ እንዲያውም የግጥሙን የመጨረሻ ስንኝ ደጋግመን ስናኝከው ‹‹ምነው ሞት —ለሞት—በሞት መፋጀቱ›› በሚል ተተክቶ ያቃጭልብናል፡፡ ሞትም ይሙት — ዓይነት ነገር፡፡
… ፫ …
በመቀነት ቀሚሷን ሸንሽና
በአልቦ በአሸንክታ ብተከሽና
‹‹ሃባቢሌ…›› እያለች…
ረገዳ እየረገደች… ታየች! በዓውደ ዓመት ተሽሞንሙና፡፡
…..
‹‹የከንፈር ወዳጅ›› ትውፊት ላይ የተመሠረተች ሆና ልጅነቱን ወደኋላ ተመልሶ በጠራ ምናብ ቁልጭ አድርጎ የከተበበት ድንቅ ግጥም ናት፡፡ በርካታ ጭብጦች ያዘለች ቢሆንም ለእኔ ግን በክፍል አንድ ላይ ‹‹የዘመኑ ጣር›› ሥር የሰፈሩ ጥልቅ ስሜቶችን አፈፍ ያደረገበትና ድህነትን፣ የኑሮን ውጣ ውረድ እንዲሁም ያለመውን ጉዳይ ማሳካቱን ቀድሞ የመተረበት ትንቢታዊ ሥራው ነው ባይ ነኝ፡፡
በመጨረሻም ገጣሚው በመጽሐፉ ውስጥ ባካተታቸው ግጥሞች አማካይነት ስለተፈጥሮ፣ ስለባህሪ፣ ስለማኅበራዊ ፍትሕ፣ ስለውበት፣ ስለፍቅርና ስለኪነት አብዝቶ የተመሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ እኔ እንዲህ ለማንበብ ሞከርኩ እናንተስ? እስኪ ወደ መጽሐፉ እንዝለቅ… (ነሐሴ 2015)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡