የዚህ ዓመት ጉዞ ሊያበቃ 2015 አለፈ፣ 2016 ተተካ ብለን ልናውጅ የቀረን አንዲት ቀን፣ ያቺውም በአራተኛው ዓመት የመጣችው 6ኛ ጳጉሜን ብቻ ናት፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት የአዘቦት ዓመት (ባለ 365 ቀኖች) ሲሆኑ፣ የዘንድሮዋ ግን የሠግር ዓመት ሆና ልታልፍ 24 ሰዓታት ብቻ ቀርተዋታል፡፡ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በሚያስተሳስር መልኩ መጠርያዋ ዕንቁጣጣሽ ይባላል፡፡ ምድሪቱ ዕንቁ የሆነ አበባን ስለምታበቅል፣ በአደይ አበባ ስለምትደምቅ ዕንቁጣጣሽ እንኳን ደህና መጣሽ ይባልላታል፡፡ ሕዝቡም የአዲስ ዓመት መነሻ የሆነችውን ርዕሰ ዓውደ ዓመት መስከረም 1 ቀንን ሲቀበል፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኩልም ከመንፈሳዊ ይዘት አኳያ ተጨማሪ ስያሜ በመስጠት ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይከበራል፡፡ በዓሉን በድግስ ለመቀበል ኅብረተሰቡ በየገበያው እየዞረ የሚያስፈልገውን መሸመቱን እንደሁሌው ቀጥሎበታል፡፡ ፎቶዎቹ አንዱን ጓዝ ያሳያሉ፡፡
- ፎቶ ፋይል