Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየፕሬስ ነፃነትና የጋዜጠኛ ጥበቃ በሌለበት ምንድነው የሚሠራው?

የፕሬስ ነፃነትና የጋዜጠኛ ጥበቃ በሌለበት ምንድነው የሚሠራው?

ቀን:

ጳውሎስ ኞኞ አንዳንዴ የራሱን አጀንዳ ይፈጥራል፡፡ እናም አንዴ ‹‹የጳውሎስ ኑዛዜ›› በሚል ርእስ በደራስያን እና ጋዜጠኞች ይደርስ የነበረው የሳንሱር ሰቆቃ ዳግም እንዳይፈጠር ከወቅቱ የሕግ ባለሙያ ጋር የሞገተበትን ጽሑፍ አወጣ፡፡  ጋዜጠኛው ስለሚደርስበት አፈናና የመብት ረገጣ ያብራራው ሕጉና ነባራዊ ሁኔታው በእንዴት ያለ መልኩ እየተጣረሰ መሆኑን በምሳሌ በማስረዳትም ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ መርስዔ ሐዘን አበበ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ በዓሉ ግርማና ሌሎችም ጋዜጣዋ ላይ በሰፊው ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ለሙያዊ ነፃነታቸው ተሟግተዋል፡፡

ሁሌም የሚያነሳቸው ጭብጦች የጋራ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሊከሰት የሚችለውን ቅራኔ የሚያጠብቡ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ የማኅበራዊ መስተጋብርም እንዲጠበቅ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ሥልጣን እንዲይዝ ይመኝለት የነበረው ወታደራዊ አገዛዝ ደርግ የሙያው መመኪያ አልሆነለትም፡፡ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በዛ፡፡ ከብዕር ፍልሚያ በዘለለ አካላዊ ጉዳት ሁሉ ይደርስ ጀመር፡፡ እናም ሚያዝያ 3 ቀን 1967 ዓ.ም. ‹‹ሌላው ኑዛዜ›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ይዞ መጣ፡፡ በዚህ ጽሑፉ ደግሞ በጋዜጠኛው ላይ የተደረገው የጥቃት ዘመቻ አስጊ መሆኑን ገልጾ ለህልውናው ሲል የቀድሞው ዓይነት በድፍረት የተሞላበት የእውነት ሥራ ላለመሥራት መወሰኑን የሚረዳ ነው፡፡

 ጋዜጠኛው በእሳት የተጠበሰ መሆኑን በማመልከትም የፕሬስ ነፃነትና የጋዜጠኛ ጥበቃ በሌለበት ለሕዝብ በእውነት ማገልገሉ እንደማያዋጣም በመጠቆም ‹‹እኔ የለሁበትም›› ዓይነት ኑዛዜውን አስነብቦ ጨመተ፡፡ እንዲህ አለ፡-

‹‹በጋዜጣው በኩል ለውጥ ያገኘን መስሎን ለመሥራት ተዘጋጅተን ነበር፡፡ ብዙው ሠራዊት (ሕዝብ) የመሥሪያ ቤቱ አስተዳደር እንዲሻሻል፣ ደመወዝ እንዲጨመርለት ሲጠይቅ፣ እኛ በሁለቱም መንገድ አልጠየቅንም፡፡ ምክንያቱም እንሥራ ብለን ነበር፡፡ የሚሆን መስሎን በተሰጠን ነፃነት መጠን ለመሥራት ጀመርን፡፡ ግን የምንዘልቀው አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ያገኘውን አግኝቶ ግማሹም ተስፋውን ተመክቶ በየጓዳው ሲገባ፣ እኛ ግን እሳት ውስጥ ገባን፡፡ ‘ድሮ እንዲህ ይደረግ ነበር’ ብለን የድሮውን ስናወራ ከድሮዎቹ ደጋፊዎች ከአቅም በላይ የሆነ ዛቻ ይደርሰን ጀመር፡፡ ለሌባ መጠበቂያ ጥይት መግዛት እንከለከል የነበረው ሰዎች እያለን፣ ለሌሎች ግን ብዙ መትረየሶች ይፈቀዱ እንደነበር እናውቃለንና ዛቻው እያስፈራን ሄደ፡፡

አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችም በድሮው ጭቆና ከነበሩበት ስንል ‘ለምን ተነክተን?’ በሚል አሁንም በሥልጣን ላይ ያለው ሠራዊት ያንኑ የመሰለ ዛቻ ይዝት ጀመር፡፡ እነኝህም መትረየሶች እንዳሏቸው እናውቃለን፡፡ ‹‹ሥራ ማቆም አግባብ አይደለም›› ስንልም ሥራ አቋሚው ወገን መድረሻ ያሳጣን ጀመር፡፡ ይኼኛው ወገን እንኳ መትረየስ ባይኖረውም ያለው በሽጉጥ፣ የሌለው በድንጋይ ሊያባቃን ነው፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት እንዲህ ያለ ጉድለት አለበት ተብሎ በማስረጃ ለምናቀርበው ወሬም መሥሪያ ቤቱ ቡራ ከረዩ ይል ጀመር፡፡ ሁሉም ራሱን ንጹሕ አስመስሎ ለመታየት በሚፈልግበት በአሁኑ ጊዜ እኛ እሳት ውስጥ ገባን፡፡ ሁሉም ንጹሕና ወንጀል ያልሠራ ከሆነ ማንን ጎትተን ልናመጣ ነው?

የጋለው ምጣድ ሳይበርድ ሁሉም እንጀራውን ለማብሰል ይራወጣል፡፡ ሹሙም በሹም ላይ ሹመት ለማግኘት ‘ንጹሕ ነው በሉልኝ’ ይለናል፡፡ ‘እንቢ’ ስንል ያው የተለመደ ዛቻ ብቻ ሆነ፡፡ እስካሁን እንዳለን አለን፡፡ ጥበቃ እንዲደረግልን ከፍተኛ ባለሥልጣን ድረስ አመልክተናል፡፡ የአንዱ ሕይወት ለአንዱ ቀልድ ነውና ተሳስቀው ተለያዩ፣ እኛ ግን አልሳቅንም፡፡ የመጠቃቃቱ ጉዳይ አሁን ተጀምሯል፡፡ ጋዜጠኞችን በየሜዳው መስደብና መደብደብ ተጀምሯል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በወሰድነውም የመከላከል እርምጃ ጥሩ ውጤት አምጥተናል፡፡ …እኛ እንደ ማንም ቤተሰብ ያለን ሰዎች ነን፡፡ ማንም እንደሚያደርገው ደመወዛችንን አስጨምረን ተቀምጠን መብላት እንችላለን፡፡  ተሰጠ የሚባለውም የጋዜጣ ነፃነት በዚህ ሁኔታ የሚያመራና ብናጠፋም ሳንከሰስ፣ በየትም ቦታ እንደ አበደ ውሻ ራስ ራሳችንን የምንባል ከሆነ፣ ነፃነቱ በአፍንጫችን ይውጣ! እንደ ማንም ከማንም ሳንጣላ በሰላም ከሁሉም ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንችል ነን፡፡ ብዛት ያለው ሠራዊት ሊጠቃ አይችልም፡፡ እኛ ግን በቀላሉ መታፈስ ወይንም ደማችንን ለማፍሰስ የምንገኝ ነን፡፡ ሁሉም ከዳር ሆኖ በእኛ በጋዜጣ ሰዎች ላይ ይፈርዳል እንጂ እንደኛ ሆኖ አንድም ጣቱን ሊያጠልቅባት የሞከረ የለም፡፡

  • ደረጀ ትዕዛዙ ‹‹ጳውሎስ ኞኞ›› (2006)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...