Sunday, July 21, 2024

የተጠናቀቀው ዓመት የፖለቲካ ውጥንቅጦች በጨረፍታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓመቱ ሕወሓት ባደረገው የሰላም ጥሪ ነበር የተጀመረው፡፡ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ዳግም የተቀሰቀሰው ሦስተኛው ዙር ጦርነት ሕወሓት ከባድ ምት እንዲያርፍበት ያደረገ ነበር፡፡ በመከላከያ ሠራዊት የሚመራው የኢትዮጵያ ጥምር ኃይል በአንዴ ብዙ የትግራይ ክልል አካባቢዎችን ወደመያዝ ተሸጋገረ፡፡ ሕወሓት በከበባ ውስጥ ወደቀ፣ ጥምር ኃይሉም መቀሌ ደጃፍ ደረሰ ሲባል ግን ሕወሓት የእንደራደር ጥያቄ ማቅረቡ መስከረም ሲገባ ተሰማ፡፡

መስከረም ሲጠባ ይፋ የሆነው የሐምሌና የነሐሴ ወራት የዋጋ ግሽበት ሪፖርት ጥሩ ዜና ይዞ አልነበረም የመጣው፡፡ በተለይም ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ግሽበት ሐምሌ ከነበረበት 30.4 በመቶ፣ በነሐሴ ወደ 31.5 ማደጉ ነበር የተነገረው፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ማለትም ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችን ጨምሮ ወደ 35.5 ማሻቀቡ ተመላክቶ ነበር፡፡ አኃዙ በ2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሚመዘገበውን ፈታኝ የኑሮ ሁኔታ ጠቋሚ ነበር፡፡

የ2015 ዓ.ም. መስከረም ስለጦርነትና ስለኑሮ ማሻቀብ ብቻ ሳይሆን፣ ስለሰላምም በርካታ በጎ ተስፋ ሲሰማበት ያለፈ ወር ነበር፡፡ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ነበሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በሰላም ለመቋጨት የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ቀድመው የጠቆሙት፡፡ ይህ የሰላም ተስፋ ደግሞ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ መስከረም 30 ለሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ባቀረቡት ንግግር የሚጨበጥ ተስፋ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ከሕወሓት የእንደራደር ጥሪ ተቀባይነት ማግኘት በተጨማሪ በኦነግ ሸኔ በወለጋ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች መጨመር እንዲሁም በአማራ ክልል ከፋኖ አመራሮች እስራት ጋር በተገናኘ የተነሳው ተቃውሞ ሁሉ ትኩስ የዜና ርዕስ ሆነው ነው ጥቅምት ወር የገባው፡፡

የተጠናቀቀው ዓመት የፖለቲካ ውጥንቅጦች በጨረፍታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በደቡብ አፍሪካ ቪክቶሪያ ከተማ የሰላም ስምምነቱ ሲፈጸም

የምርጫ ቦርድ የብልፅግና ጠቅላላ ጉባዔ ተመራጭም አስመራጭም ሆኖ መሰየሙ ተገቢነት የለውም ሲል ያወጣው ሪፖርት፣ የመስከረም ፖለቲካ አንዱ ማጣፈጫ ነበር፡፡ በጋምቤላ ክልል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት መድረሱ አስገርሞ ያለፈ ጉዳይ ነበር፡፡

በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ ሸቀጥ የሚያስመጡ የውጭ ምንዛሪ ምንጮቻቸውን ያሳውቁ መባሉ በኢኮኖሚ ጉዳይ አገሪቱ ግራ መጋባት ውስጥ መግባቷን ጠቋሚ ነበር፡፡ የሥራ ግብር ቅናሽ ይደረግበት የሚል ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት መቅረቡ፣ እንዲሁም የውጭ ባንኮች ረቂቅ አዋጅ መቅረቡ ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ዜናዎች ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. የ2023 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ከ5.3 በመቶ እንደማያልፍ መነገሩ ደግሞ አገሪቱ ገና ከሥጋት አለመላቀቋን አመላካች ነበር፡፡

በጥቅምት የጀመረው የሰላም ድርድር ቀጠሮ ዜና ነበር፡፡ የሰላም ንግግር እንጂ ድርድር አይደለም የሚል ሙግት ቢነሳም፣ ሰላም ሰላም የሚሸት ዜና መሰማቱ በራሱ በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ተስፋ ያሳደረ ነበር፡፡

በጥቅምት 2015 ዓ.ም. የተገባደደው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል በተፈረመ የሰላም ስምምነት ነበር፡፡ የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት በዓመቱ ከተሰሙ ትልልቅ ዜናዎች ግንባር ቀደሙ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ ነገር ግን ጥቅምት ሌሎችም ጆሮ ገብ ወሬዎች ያጣ ወር አልነበረም፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በዚሁ ወር በፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፣ ‹‹አስፈጻሚ አካላት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ማክበር ካልቻሉ ሥርዓት ተሰብሯል ማለት ነው፤›› ሲሉ ጠንካራ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንቷ በኋላ ከሥራ ለመልቀቃቸው ንግግሩ ቀድሞ ፍንጭ የሚሰጥ ሊባል የሚችል ነበር፡፡

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች በኦሮሚያ ክልል ባሉ ኬላዎች እንዳያልፉ መከልከሉ፣ የጥቅምት ወርን የወጠረ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነበር፡፡ ኦነግ ሸኔ በወለጋና በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚያደርገው ጥቃትና የንፁኃን ግድያ አይሎ የቀጠለበት ወርም ነበር፡፡ የኦነግ ሸኔ ጥቃት ሥጋት ከኦሮሚያ አልፎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባምባሲ አካባቢም ተሻግሮ ነበር፡፡

ከኦነግ ሸኔ ጥቃት በተደራቢ ከሱዳን የተነሱ ኃይሎች በመተማ በኩል ጥቃት አደረሱ የሚል ዜናም በዚሁ ሰሞን ይደመጥ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የቀውስ ወሬ ገና ካልበረደው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር ተደርቦ፣ እየተሰማ ያለውን የዕርቀ ሰላም ዜና እንዳያደበዝዘው ሲሠጋ ነበር የሰነበተው፡፡

ጥቅምት 12 በመላ አገሪቱ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የተወገዘበት ሰላማዊ ሠልፍ ተካሄዶ ነበር፡፡ በታዋቂ አፍሪካዊያን የሰላም መማክርት መፈጠሩና የሰላም ድርድሩን ሊመራው ነው መባሉ ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ከሕወሓት ጋር የሚደረገው ድርድር የተቆረጠለት ቀን እየተቃረበ ሲመጣ፣ መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብር ሁኔታ ድርድር እንዲያደርግ የሚያሳስቡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በርክተው ነበር፡፡

ጥቅምት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የኮሌራ ወረርሽኝ ተከሰተ የሚል ወሬ የተሰማበት ነበር፡፡ ኮሌራ ዓመቱን ሄድ መለስ እያለ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከሰተ መባሉ በቀጣይ ጊዜያትም ቀጥሎ ነበር፡፡ በሌላ በኩል እንስሳትን በከፍተኛ ቁጥር የገደለና ሰዎችንም በከፋ ደረጃ ለጉዳት የዳረገ የድርቅ አደጋ በቦረና አካባቢ፣ እንዲሁም በተለያዩ የሶማሌ ክልል ዞኖች አጋጠመ መባሉ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ ቀውስ ተጋላጭነት ያሰፋ ነበር፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወደ ትግራይ ለዕርዳታ አቅርቦት የሚሆን ኮሪዶር ተፈጠረ መባሉ የሰብዓዊ ቀውሱ አንድ ማስታገሻ አገኘ እንዲባል ያደረገ ነበር፡፡

የአንድ እንቁላል ዋጋ ወደ 15 ብር ማሻቀብ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር እየባሰበት መሄዱን ገና በጥቅምት የጠቆመ ነበር፡፡ በቀጣይ ወራት ይኸው ችግር ብሶበት በቲማቲም፣ በሽንኩርትና በድንች፣ እንዲሁም በመጨረሻ በእንጀራና በዳቦ ዋጋዎች ላይ እየተፈራረቀ ሲመጣ መታየቱ አልቀረም፡፡

እ.ኤ.አ. የ2023 የኢትዮጵያ የምንዛሪ ክምችት ከ18 ቀናት የማያልፍ ነው የሚል ሪፖርት መሰማቱ አንድ ሥጋት ነበር፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናት በውጭ አገሮች ያደረጉት ጉዞ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ እንድታገኝ ለማስቻል ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱ የኢኮኖሚ ሥጋቱን አክብዶት ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የአገሪቱ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፍትሕ አደባባይ በተደጋጋሚ እየቀረበ ውግዘትና ጫና መደራረቡ፣ በሁሉም መንገድ አጣብቂኝ ውስጥ የወደቀች ይመስል ነበር፡፡

በሰላም ስምምነቱ ዋዜማ የፋኖና ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱ፣ አገሪቱ ወደ ሌላ ዙር ቀውስ ልትሸጋገር ትችላለች የሚል ፍንጭ የሰጠ አጋጣሚ ነበር፡፡

መስከረምና ጥቅምትን በድርድር፣ የሰላም ንግግርና የሰላም ስምምነት አጀንዳዎች ያሟሸው፣ በ2015 ዓ.ም. ከኅዳር ጀምሮ ግን ብዙ ነገሮችን አግበስብሶ ያመጣ ዓመት ነበር፡፡

በ2015 ዓ.ም. የማያቀባብር ጉዳይ ሆኖ ያለፈው የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ ገና በጠዋቱ በጥቅምት ለ2015/16 ዓ.ም. የምርት ዘመን አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ጨረታ ስለመውጣቱ በሰፊው ተነዛ፡፡ በኅዳር ወር ደግሞ ይኼው ግዥ ተፈጸመበት የተባለ ማዳበሪያ መጓጓዝ ስለመጀመሩ ብዙ ተለፈፈ፡፡ በመጋቢት ወር የአቅርቦት ሥጋት አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ሌላ ዙር ዘመቻ ተካሄደ፡፡

በ2015 ዓ.ም. የበልግ ወቅት ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ሁኔታ የተሻለ ዝናብ መዝነቡ ተነገረ፡፡ በልግ አልፎ የመኸር ወቅት ዋነኞቹ ሰብል መዝሪያ ወራት ሰኔና ሐምሌ መጡ፡፡ በስተመጨረሻ ገበሬው ማዳበሪያ አጣሁ ብሎ ለተቃውሞ አደባባይ ሲወጣ ነበር የታየው፡፡

በጦርነትና በግጭት እጅግ ምርታማ የሚባሉ አካባቢዎች ዘንድሮ ጦም ማደራቸው በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በማዳበሪያ አቅርቦት ችግር የዘንድሮ መኸር ውጤታማ የምርት ዘመን እንደማይሆን እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የመጪው ዓመት የኢትዮጵያን ክራሞት ከወዲሁ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በሰላም ስምምነቱ ማግሥት በተከተሉት ወራት በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በተሻለ ሁኔታ ይመጣል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው በተከታታይ ወራት ተከታታይ ውዝግቦች በየዓይነቱ መከሰት ቀጠሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ መዝሙር ካልተዘመረ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ካልተሰቀለ በሚል የተነሳው ውዝግብ የትምህርት ዘርፉ የመጀመሪያው ቀውስ ሊባል ይችላል፡፡ በስተኋላ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መግቢያና ከዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናዎችን ታከው የተፈጠሩ ችግሮች፣ የትምህርት ዘርፉ አወዛጋቢ እንደሆነ ዓመቱን እንዲያሳልፍ አድርጎታል፡፡

በደቡብ ክልል በተለይ በጉራጌ ዞን የክልልነት የመዋቅር ጥያቄን ተንተርሶ የተነሳው ውዝግብ፣ አካባቢውን በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲወድቅ አድርጎት ነበር፡፡

መንግሥት በሙስና ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ቃል የገባበት ዓመት ነበር 2015 ዓ.ም.፡፡ የሙስና ጉዳይ ለተወሰኑ ወራት በከፍተኛ ደረጃ ሲራገብ ቆየ፡፡ በተወሰነ ደረጃ የባለሥልጣናት እስራት መሰማትም ቀጠለ፡፡ በሒደት ግን የሙስና ዘመቻው ጉዳይ የአንድ ሰሞን አጀንዳ ብቻ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡

መንግሥት በተለያዩ ወራት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ከሕዝብ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ እንዲገባ አድርገውት ነበር፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመዳኘት የሄደበት ርቀት፣ አገሪቱን ለከባድ አደጋ ሊያጋልጥ የሚችል ሆኖ ነበር የከረመው፡፡

በአንዳንድ የእምነቱ አባቶች የጳጳሳት ሹመት መደረጉና የኦሮሚያ ሲኖዶስ ፈጥረናል መባሉ፣ በቤተ ክርስቲያኗና በብዙ ተከታዮቿ ከባድ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ግጭት እስከ ማምራት የደረሰ ሲሆን፣ የእምነቱ አባቶች አስተዋይነትና ብልህነት ታክሎበት ጉዳዩ በዕርቅ ባያልቅ ኖሮ ችግሩ መንግሥትን ቅርቃር ውስጥ ሊከት በቻለ ነበር ተብሎ በብዙዎች ዘንድ እምነት ፈጥሮ ነበር፡፡

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀውስ ታለፈ ሲባል ደግሞ በሸገር ከተማ ምሥረታ ማግሥት የተካሄደው በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሕገወጥ ግንባታ የማፍረስ ዘመቻ ሌላ ዙር ጣጣ ይዞ ነበር የመጣው፡፡ በሕገወጥ ግንባታ ማፍረስ ስም መስጊዶች መፍረሳቸው ሕዝበ ሙስሊሙን ክፉኛ አስቆጣ፡፡ ቁጣው በፍጥነት ወደ ተቃውሞ ተሸጋግሮ በሒደት ግጭት ወደ መፍጠር ገባ፡፡ አሁንም የእምነቱ አባቶች በወሰዱት አስተዋይ ዕርምጃ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ የመነጋገር ዕድል በመፈጠሩ በእርቅ ጉዳዩ ዕልባት ማግኘት መቻሉ ብዙዎችን በወቅቱ አነጋግሯል፡

በ2015 ዓ.ም. ነበር ትልቁ የደቡብ ክልል የከሰመውና ኢትዮጵያ ሁለት አዳዲስ ክልሎችን ለማግኘት የበቃችው፡፡ በዓመቱ ብዙ ይሠራሉ ተብለው የተጠበቁት እነ መዓዛ አሸናፊና ብርቱካን ሚደቅሳ በበቃኝ ፖለቲካን ተሰናብተዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ፖለቲካን ብቻ ሳይሆን ይህችን ዓለምም የተሰናበቱ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ የቀድሞ ጤና ሚኒስትር ከበደ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ የጂን ባንክ መሥራች መላኩ ወረደ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ የብዝኃ ሀብት ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደ ማርያም፣ እንዲሁም ሠዓሊ አብዱራህማን መሐመድ የመሳሰሉ ትልልቅ ሰዎች በሞት ተለይተዋል፡፡

የአማራ ክልል ብልፅግና ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላና አጃቢዎቻቸው መገደልን ግን መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ሲሆን ነበር የታየው፡፡ በልዩ ኃይልና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ትጥቅ ማስፈታት አጀንዳ በአማራ ክልል ቀውስ ያጋጠመው መንግሥት፣ ግድያውን ተከትሎ በክልሉ ጠንካራ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ እንዳንደረደረው ይነገራል፡፡

በሒደት ይህ የመንግሥትና የአማራ ክልል ታጣቂዎች ውዝግብ ወደ ከባድ ውጊያ ተሸጋግሯል፡፡ ሁኔታው አሁንም ድረስ ውሉ ያልለየለት ሲሆን ግጭቱ ገና አለማባራቱ ነው የሚነገረው፡፡

አማራ ክልልን ወደ ጦርነት የከተተው ችግር ምንነትም ሆነ መፍትሔው እስካሁን በቅጡ የታሰበበት አይመስልም፡፡ ክልሉ በአዲስ መልክ የአስተዳደር ባለሥልጣናት ሹመት ተደርጎለታል፡፡ በአምስት ዓመታት ለስድስተኛ ጊዜ የርዕሰ መስተዳድር ሹመት ያገኘው አማራ ክልል፣ ከባድ ቀውስ እንዳለ ነው የሚነገረው፡፡ ይህን ቀውስ ከማባባስ በዘለለ ተቀምጦ ለችግሮች መፍትሔ ለማበጀት የሚደረግ ሙከራ አለመታየቱ ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለሚከታተሉ ሁሉ ከድጡ ወደ ማጡ የሚያሰኝ ነበር፡፡

የብሪክስ አባልነት ጥያቄዋ ኢትዮጵያ ምላሽ ቢያገኝም በ2015 ዓ.ም. ከእነ ነባር ችግሮቿ ነው ያዘገመችው፡፡ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ዛሬም ትኩስ እሳት ሆኖ እየተፋጀ ይገኛል፡፡ የኦነግ ሸኔ ጭፍጨፋ፣ ዕገታና ጥቃት በድርድር ዕልባት ያገኛል ቢባልም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የሱዳን ቀውስ በቅርብ ርቀት አገሪቱን ተጎራብቷል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን በጉያዋ ያለ ብዙ ችግር ሳትፈታ የወደብ ጥያቄ ሲወዘውዛት ነው ዓመቱን ያሳለፈችው፡፡ በ2016 ዓ.ም. ወዴት ታዘግም ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -