በል ንፈስ፣ በል ንፈስ፣ አንተ ሞገደኛ፤ የክረምት ወጨፎ
ምንም እንኳን ባትሆን የዚያን ያህል ክፉ
ምሥጋና እንደካደ እንደሰው ልጅ ጥፉ፣
እስተዚህም ባይሆን የጥርስህ ስለቱ፣
ሆኖም ብትሰወር ምንም ባትታይ፣
ስትንፋስህ ጭምር ባልጎ የለም ወይ፡፡
ሆያ ሆዬ በሉ! ሆያ ሆዬ በሉ!
ለዛፍ ለቅጠሉ፣
የሸፍጥ ከሆነ አብዛኛው ሽርክና፣
አብዛኛው ፍቅርም ተራ ድንቁርና፣
ለዛፍ ለቅጠሉ፣ ሆያ ሆዬ በሏ!
የዚች ዓለም ኑሮ፤ አቤት መጣፈጧ፡፡
አንተ መራራ ሰማይ በል ብረድ፤ በል ቀዝቅዝ፣
ንክሻህም ቢሆን የማያደነዝዝ
የረሱት ውለታ እንደሚዘነጋ፣
ምንም ቢሆንልህ ውሆች ብታናጋ፣
አነዳደፍህም እስተዚህ አይወጋ
እንደረሱት ወዳጅ የማይኖረው ዋጋ
ሆያ ሆዬ በሉ! ሆያ ሆዬ በሉ፣
ለዛፍ ለቅጠሉ፣
የሽፍጥ ከሆነ አብዛኛው ሽርክና፣
አብዛኛው ፍቅርም ተራ ድንቁርና፣
ለዛፍ ለቅጠሉ፣ ሆያ ሆዬ በሏ!
የዚች ዓለም ኑሮ፤ አቤት መጣፈጧ፡፡
ከዊሊያም ሼክስፒር/ስድ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ