Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትልቁንም ትንሹንም የነካካው ሙስና በአዲሱ ዓመት መፅዳት አለበት

በኢትዮጵያ ሥር እየሰደዱ ካሉ እጅግ አሳሳቢ እየሆኑ ካሉ ቀውሶች መካከል አንዱ ሙስና ነው፡፡ ‹‹አገልጋይና ተገልጋይ የሚግባቡበት በገንዘብ ብቻ ነው›› ሲባል ያማል፡፡ ኅብረተሰቡ ስንት የተቸገረባቸው ጉዳዮች እያሉበት በሄደበት ቦታ ሁሉ ደረሰኝ የሌለው ክፍያዎች በእጅጉ አማረውታል፡፡ 

አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም እጅ መንሻ የማይጠየቅበት ቦታ እየጠፋ መጥቷል፡፡ በዜግነታችን ብቻ ማግኘት የሚገባንን አገልግሎት ሳይቀር ጉቦ ካልከፈልን ማግኘት ከባድ ሆኗል፡፡ ለሙስና በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው የተባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ደግሞ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በርካታ ባለ ጉዳዮችን የሚያስተናግዱ ወረዳና ክፍለ ከተሞች ያሉ አገልግሎቶች ለማግኘት በቀላል ጉቦ የሚጠየቅባቸው ሆነዋል፡፡ 

ለመታወቂያ፣ ለልደት ካርድ፣ ያገባና ያላገባ ሠርተፍኬት ለመጠየቅ ሳይቀር ጉቦ የሚጠየቅባቸው ቢሮዎች ብዙ ናቸው፡፡ ትንሹም ትልቁም ተሿሚ እንደ ደረጃው ከተገልጋይ የሆነ ነገር ለማግኘት ዓይኑን ያጉረጠርጣል፡፡ ትንሹን ነገር በማካበድ ተገልጋይ ደንብሮ ከሕግ ውጪ ያልተገባ ክፍያ እንዲከፍል ያስገድዱታል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉቦ እንዲከፍል የሚጠየቅ ተገልጋይ ካመነታ ጉዳዩን የሚፈጸምለት አይደለም፡፡

በተለይ መሬት ነክ የሆኑ ምንም ዓይነት ጉዳዮች ያለ ጉቦ አይፈጸሙም፡፡ ከመሬት ጋር በተያያዙ ተገልጋዮች የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ሁሉ እጅ መንሻ በግልጽ ይጠየቅባቸዋል፡፡ ቦታ በመለካት መረጃ አሰባስቦ መምጣትና ሪፖርት ማቅረብ ያለበት መሐንዲስ፣ ይህንን ተጽፎ የተሰጠውን ደመወዝ ለሚከፈለው ሥራ፣ ባለ ጉዳዩ በእጁ የሆነ ነገር ካላስጨበጠው ንቅንቅ አይልም፡፡ ጉምሩክ አካባቢም በሥውር ጉቦ የሚበላበት ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ብልሹ ሠራተኞች በየቦታው እየዞሩ፣ ‹‹ይህንን አላደረክም›› እያሉ ለመንግሥት መግባት የነበረበትን ቅጣት እነሱ ተደራድረው ወደ ኪሳቸው ይከታሉ፡፡ 

በአጠቃላይ በሙስና ስማቸው በተደጋጋሚ በሚነሱ ቢሮዎች ተገልጋዮች ለጉዳዩ ማስፈጸሚያ የሚጠየቀውን ገንዘብ ማዘጋጀት ካልቻሉ ጉዳያቸውን በቶሎ መጨረስ አይችሉም፡፡ ወይም በሰበብ በአስባቡ እንከን እየፈለጉ ጉዳዩን እንዳይፈጸም ሊያደርጉም ይችላሉ፡፡ ሙስና የሌለበት ቦታ የለም፡፡ ዛሬ እኮ የተበላሸ የኤሌክትሪክ መስመርን ለማስቀጠል ደንበኞች ጉርሻ መስጠት ካልቻሉ ለቀናት በጨለማ ውስጥ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የአካባቢው ሰዎች ገንዘብ አዋጥተው ጉቦ መክፈል የጠፋ አንፖላቸውን ያበራሉ፡፡ የተቆረጠ ውኃን ለማስቀጠልም ቢሆን መስመሩን መልሶ አገልግሎት ለማስጀመር ተቋሙ በደረሰኝ ከሚያስከፍለው እጅግ የተጋነነ ዋጋ ሌላ መስመሩን እንዲቀጥሉ የሚላኩ ሠራተኞች በግላቸው የሻይ ካልተሰጣቸው ነገሮችን ሊያበለሻሹ እንደሚችሉ ሁሉ እያየን ነው፡፡ 

መንጃ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስና ለመሰል አገልግሎቶች ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ለያዘው ሠራተኛ ‹‹የተለመደ›› የተባለውን ክፍያ ካልከፈሉ ጉዳያቸውን ማስጨረስ ያለመቻላቸውም ነገር አዲስ ዜና አይደለም፡፡ 

የባንክ የብድር ጥያቄዎችም ቢሆኑ በአግባቡ ምላሽ የሚሰጣቸው ብድር ፈቃጁ ለሥራ ኃላፊ ከብድሩ ላይ የተወሰነ ነገር መልቀቅ እንደሚኖርበት ይጠበቃል፡፡ የአገልጋይና ተገልጋይነት መንፈስ ከመበለሻሸት አልፎ የበለጠ መስመር እየሳተ ለመሆኑ ማሳያው አንድን ጉዳይ ለማስጨረስ ቀድሞ ጎቦ ለመስጠት ፈቃደኛ የሚሆኑ ተገልጋዮች ቁጥር መበራከቱ ነው፡፡ ጉዳያቸውን በገንዘብ ለመጨረስ ራሳቸውን ያለማመዱ ዜጎች እየተበራከቱ መሄዱ ደግሞ ጤነኛ የተባለውንም አገልጋይ እንዲበላሽ እያደረገ ነው፡፡ የሥራ ባህልንም እያበላሸ ነው፡፡ 

ሙስና ቱባ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ የሚነካኩበት ነው፡፡ የጉቦ አሰጣጡም ‹‹እየዘመነና እየረቀቀም›› ነው፡፡ ጉዳይ ለማስጨረሻ የሚሰጥ ጉቦ በውጭ ምንዛሪና በውጭ አካውንት የሚቀመጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

ተለቅ ተለቅ ያሉ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ትልልቅ ባለሥልጣናት የሚሰጣቸውን ጉቦ በብር አይቀበሉም እየተባለ ነው፡፡ አንድ ተገልጋይ የሚፈልገውን አገልግሎት ወይም ጥቅም ላስኘለት ተሿሚ ወይም ፈፃሚ የሚከፈለውን ጉቦ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለ አካውንቱ እንዲገባለት ያደርጋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ብልግና ጎልቶ የሚታው በውጭ ኩባንያዎች ጭምር የሚፈጸም ነው፡፡ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍና ትልልቅ የመንግሥት ግዥዎች ጨረታ አካባቢ ይህ ብልግና ገዝፎ ይታያል፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሙስና ዕድገት ተገንዝቦ እውነተኛ ሕጋዊ ዕርምጃ  ባለመወሰዱ፣ የውጭ ኩባንያዎችም ሳይቀሩ በሌብነት ላይ ተሰማርተው የአገር ሀብት ያላግባብ እንዲባክን እየተደረገ ነው፡፡ ዛሬ ከኢትዮጵያ ተዘረፈ የሚባለው ወርቅ በውጭ ዜጎች ላይ ተሳበበ እንጂ፣ ሕገወጥ ተግባሩን የሚፈጸም ተግባር በሆኑ ሾመኞች ጭምር መሆኑ አይካድም፡፡ 

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ከመንግሥት የተሰወረ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለማስወገድ በተደጋጋሚ ሲዛትም ሰምተናል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት ቱባ ከምንላቸው ተሿሚዎች ሳይቀር ስንሰማው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡

ዜጎች በአገልግሎት አሰጣጥ የመማረራቸውን ያህል አደባባይ ወጥተው ብሶት ማሰማት እየፈራ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት እነዚን ሌቦች ሲቀጣ የማይታይ፣ ይህንን ጉዳይ ለማስፈጸም ይህንን ያህል ተጠየቅሁ ብሎ ቢያጋልጥ ጉዳዩ እንደማይፈጸምለት ስለሚገነዘብ ነው፡፡ 

ሙስና የዚህች አገር አሳሳቢ ችግር ስለመሆኑ መንግሥት የተረዳውን ያህል ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ አቅም ያጣበት ምክንያት ግራ ያጋባል፡፡ ማን ያውቃል ሙስናን ለመዋጋት ጠረጴዛ እየደበደበ የሚናገረው ራሱ እጁ ያለበት ሆኖ፣ ነገሮች እዚያው ተድበስብሰው እንዲቀሩ ተደርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም በመሆኑ በማናለብኝነት ወንጀሉ እንዲንሰራፋ ሆኗል፡፡ 

ስለዚህ አሁን የደረስንበት የሙስና ችግር ትልቁንም ትንሹንም ያነካካ የኅብረተሰቡንም አንደበት ሸብቦ መቀጠል ስለሌለበት፣ በአዲሱ ዓመት ይህንን የአገር ነቀርሳ ለመከላከል ሁሉም የሚረባረብበት ይሁን፡፡ ጉዳይ ያለ ጉቦ እንደማይፈጸም እየሰማ ያለውን ትውልድ ትክክለኛና ሕጋዊነትን እንዲማር ለማድረግ፣ መንግሥት በተለይ ጨዋ ባለሥልጣናት ሊታገዙ ይገባል፡፡ በአቋራጭ መበልፀግ ምን ያህል አደጋ እንዳለውና በሕግና በአግባቡ ሠርቶ ማደግና መበልፀግ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ 

ሙስና የአገር ትልቅ ነቀርሳ ነው፣ ጉዳቱም ብዙ ነው፡፡ ሕገወጥ አሠራሮች እንዲስፋፉ ከማድረጉም በላይ አገርን በንፅህና ለማገልገል የሚሹ አገልጋዮችን በመበረዝ አጠቃላይ ሕግና ሥርዓትን የሚፋልስ ነው፡፡ መንግሥት የትኛውንም ፖሊሲዎችንና ዕቅዶቹን ማሳካት የሚችለው በየቢሮው የተወሸቁትን በሙስና የተጨማለቁ ፈጻሚዎችን ካፀዳ ብቻ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን ለማሳደግም ሆነ ዛሬ የዜጎች አንገብጋቢ የሆነው የዋጋ ንረት ሳይቀር መፍትሔ የሚያገኘው ሙስና ላይ ሲዘመት ብቻ ነው፡፡ ሙስናን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳን እንዲቀንስ ማድረግ የአዲሱ ዓመት አንዱና ዋነኛው ሥራ መሆን አለበት፡፡ መልካም አዲስ ዓመት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት